በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም

የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም

“መጀመሪያ ላይ ሙሉ በሙሉ ተስፋ ቆርጠን ነበር። በአካባቢያችን በተከሰተው የመሬት መንሸራተትና ጎርፍ ምክንያት ንብረታችን ሁሉ ወድሞ ነበር።”—አንድሩ፣ ሴራ ሊዮን

“አውሎ ነፋሱ ካቆመ በኋላ ወደ ቤታችን ተመለስን። ምንም የተረፈ ነገር አልነበረም። በድንጋጤ ክው ብለን ቀረን። ልጄ ተንበርክካ ማልቀስ ጀመረች።”—ዴቪድ፣ ቨርጅን ደሴቶች

አንተም የተፈጥሮ አደጋ አጋጥሞህ የሚያውቅ ከሆነ ተመሳሳይ ሁኔታ ያጋጠማቸው ሰዎች የሚሰማቸውን ስሜት መረዳት አይከብድህ ይሆናል፤ እነዚህ ሰዎች በድንጋጤ ሊዋጡ፣ የተከሰተውን ነገር መቀበል ሊከብዳቸው፣ ግራ ሊጋቡ፣ ሊጨነቁ አልፎ ተርፎም በቅዠት ሊሠቃዩ ይችላሉ። የተፈጥሮ አደጋ የደረሰባቸው በርካታ ሰዎች ተስፋ ከመቁረጣቸው የተነሳ በሕይወት የመኖር ፍላጎታቸው ሊሟጠጥ ይችላል።

በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ያለህን ሁሉ ስታጣ ሁኔታው ከአቅምህ በላይ እንደሆነ ሊሰማህ ይችላል። አልፎ ተርፎም በሕይወት መኖርህ ምንም ዋጋ እንደሌለው ይሰማህ ይሆናል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወት ዋጋ እንዳለው ይገልጻል፤ በተጨማሪም ወደፊት የተሻለ ጊዜ ይመጣል ብለህ ተስፋ እንድታደርግ የሚያስችል አሳማኝ ማስረጃ ይዟል።

የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ማወቅ ተስፋን ያለመልማል

መክብብ 7:8 “የአንድ ነገር ፍጻሜ ከጅማሬው ይሻላል” ይላል። የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥምህ፣ መጀመሪያ ላይ ሁሉም ነገር ጭልምልም ይልብህ ይሆናል። ወደ ቀድሞ ሕይወትህ ለመመለስ በትዕግሥት ጥረት ማድረግህን ስትቀጥል ግን ሁኔታዎች እየተሻሻሉ ሊሄዱ ይችላሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ “የለቅሶ ድምፅም ሆነ የጭንቅ ጩኸት [የማይሰማበት]” ጊዜ እንደሚመጣ ይናገራል። (ኢሳይያስ 65:19) በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ምድር ወደ ገነትነት ስትለወጥ ይህ ትንቢት ፍጻሜውን ያገኛል። (መዝሙር 37:11, 29) በዚያን ጊዜ የተፈጥሮ አደጋ የሚባል ነገር አይኖርም። በተጨማሪም አደጋው ያስከተላቸው መጥፎ ትዝታዎችም ሆኑ አካላዊ ጠባሳዎች ለዘላለም ይወገዳሉ፤ ምክንያቱም ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ “የቀድሞዎቹ ነገሮች አይታሰቡም፤ ወደ ልብም አይገቡም” በማለት ቃል ገብቷል።—ኢሳይያስ 65:17

እስቲ አስበው፦ ፈጣሪ “የተሻለ ሕይወትንና ተስፋን” ሊሰጥህ ዝግጅት አድርጓል፤ ወደፊት፣ ፍጹም በሆነው አገዛዙ ሥር ሰላም የሰፈነበት ሕይወት ይሰጥሃል። (ኤርምያስ 29:11) ታዲያ ይህን እውነት ማወቅህ ተስፋህን ሊያለመልመው ይችላል? በመጀመሪያው ርዕስ ላይ የተጠቀሰችው ሳሊ እንዲህ ብላለች፦ “የአምላክ መንግሥት ወደፊት የሚያመጣልንን አስደሳች ነገሮች ማሰባችን፣ የደረሱብንን አሳዛኝ ነገሮች ወደኋላ ትተን ወደፊት እንድንራመድ ይረዳናል።”

ታዲያ የአምላክ መንግሥት በቅርቡ ለሰው ልጆች ስለሚያመጣቸው በረከቶች ለምን አትማርም? እንዲህ ማድረግህ በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ሕይወትህ ቢመሰቃቀልም ብሩህ አመለካከት ይዘህ እንድትቀጥል እንዲሁም ከአደጋ ነፃ የምንሆንበትን ጊዜ በጉጉት እንድትጠባበቅ ያስችልሃል። መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጣቸውን ምክሮች ተግባራዊ ማድረግህ በዛሬው ጊዜም እንኳ ከተፈጥሮ አደጋ ጋር ተያይዘው የሚመጡትን ችግሮች መቋቋም እንድትችል ይረዳሃል። እስቲ ከእነዚህ ምክሮች መካከል አንዳንዶቹን ተመልከት።