በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ኢየሱስ መሐላን ያወገዘው በየትኛው የአይሁዳውያን ልማድ የተነሳ ነው?

በሙሴ ሕግ መሠረት፣ መማል ተገቢ የሚሆንባቸው ጊዜያት ነበሩ። በኢየሱስ ዘመን የነበሩ አይሁዳውያን ግን በትንሽ በትልቁ የመማል ልማድ ተጠናውቷቸው ነበር። እንዲህ የሚያደርጉት የተናገሩት ነገር ይበልጥ ተአማኒነት እንዲኖረው ለማድረግ ሲሉ ነበር፤ ሆኖም ኢየሱስ ከአንዴም ሁለት ጊዜ ይህን ልማድ አውግዞ ተናግሯል። ኢየሱስ “ቃላችሁ ‘አዎ’ ከሆነ አዎ ይሁን፤ ‘አይደለም’ ከሆነ አይደለም ይሁን” በማለት አስተምሯል።—ማቴ. 5:33-37፤ 23:16-22

ቲኦሎጂካል ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ኒው ቴስታመንት እንደገለጸው “አይሁዳውያን የሚናገሩትን ነገር ሁሉ በመሐላ የማረጋገጥ ልማድ” ምን ያህል ተጠናውቷቸው እንደነበር በታልሙድ ላይ ከሰፈረው ሐሳብ ማየት ይቻላል፤ ታልሙድ እንደ ጽኑ መሐላ የሚቆጠሩትንና የማይቆጠሩትን መሐላዎች አንድ በአንድ ይዘረዝራል።

እንዲህ ያለውን መሐላን ያላግባብ የመጠቀም ልማድ ያወገዘው ኢየሱስ ብቻ አልነበረም። ለምሳሌ ያህል፣ አይሁዳዊው ታሪክ ጸሐፊ ፍላቪየስ ጆሴፈስ አንድን የአይሁድ ኑፋቄ ቡድን አስመልክቶ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “[የዚህ ኑፋቄ ቡድን አባላት] መሐላ መፈጸምን በሐሰት ከመመሥከር የከፋ እንደሆነ አድርገው ስለሚቆጥሩ ከመማል ይቆጠቡ ነበር። ምክንያቱም በአምላክ ስም ካልማለ በቀር ሊታመን የማይችል ሰው ቀድሞውኑም ቢሆን የተወገዘ ነው የሚል አመለካከት አላቸው።” በተጨማሪም የሲራክ ጥበብ ወይም ኤክሊዚያስቲከስ በመባል የሚታወቀው የአይሁዳውያን አዋልድ ጽሑፍ (23:11) “መማል የሚወድ ሰው የለየለት ሕገ ወጥ ሰው ነው” በማለት ይናገራል። ከዚህ ማየት እንደሚቻለው፣ ኢየሱስ ያወገዘው በረባ ባልረባው የመማል ልማድን ነው። አንድ ሰው ሁልጊዜ እውነቱን የሚናገር ከሆነ የሚናገረው ነገር ይበልጥ ተአማኒነት እንዲኖረው ለማድረግ ሲል መማል አያስፈልገውም።