በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ንድፍ አውጪ አለው?

የሰሃራው ብርማ ጉንዳን ሙቀት የሚከላከልበት መንገድ

የሰሃራው ብርማ ጉንዳን ሙቀት የሚከላከልበት መንገድ

የሰሃራው ብርማ ጉንዳን (ካታግሊፊስ ቦምቢሲና) ሙቀትን የመቋቋም ከፍተኛ ችሎታ ካላቸው በየብስ የሚኖሩ ፍጥረታት መካከል አንዱ ነው። ጉንዳኑን የሚመገቡ እንስሳት በጠራራው የሰሃራ ፀሐይ ምክንያት ጥላ ለመፈለግ በሚገደዱበት ወቅት ይህ ጉንዳን ለአጭር ጊዜ ከጉድጓዱ በመውጣት ምግብ ይፈልጋል፤ ከሚመገባቸው ነገሮች መካከል በከባድ ሙቀት የተነሳ የሞቱ ነፍሳት ይገኙበታል።

[50] μm

እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ ብርማው ጉንዳን ሙቀት እንዲከላከል ከሚረዱት ነገሮች መካከል ሰውነቱ ከላይና ከጎን በኩል ፀጉር ያለው መሆኑ እንዲሁም ከታች በኩል ፀጉር አልባ መሆኑ ይገኙበታል። ጉንዳኑ አብረቅራቂ መልክ እንዲኖረው የሚያደርጉት እነዚህ ፀጉሮች መሃል ለመሃል ተቆርጠው ሲታዩ የሦስት ማዕዘን ቅርጽ ያለው ቱቦ ይመስላሉ። ከላይ በኩል ያሉት ሁለቱ የፀጉሩ ጎኖች ከላይ እስከ ታች በዓይን በማይታዩ ወጣ ገባዎች የተሸፈኑ ሲሆን ሦስተኛው ጎን ግን ልሙጥ ነው። የጉንዳኑ ፀጉር እንዲህ ያለ ንድፍ ያለው መሆኑ ሁለት ጥቅሞች አሉት። አንደኛ ፀጉሮቹ ከፀሐይ የሚመነጨውን በዓይን የማይታይ የሙቀት ጨረር አንጸባርቀው መመለስ እንዲችሉ ይረዳቸዋል። ሁለተኛ ጉንዳኑ ከአካባቢው የወሰደውን ሙቀት ማስወገድ እንዲችል ይረዳዋል። ፀጉር አልባ የሆነው የጉንዳኑ የታችኛው ክፍል ደግሞ ከበረሃማው መሬት የሚመጣውን በዓይን የማይታይ የሙቀት ጨረር አንጸባርቆ ይመልሳል። *

[10] μm

የሰሃራው ብርማ ጉንዳን ያለው ሙቀት የመከላከል ችሎታ የሰውነቱ ሙቀት ከ53.6 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ እንዳይበልጥ ይከላከልለታል፤ የሰውነቱ የሙቀት መጠን ከዚያ ካለፈ ጉንዳኑ በሕይወት መቆየት አይችልም። ተመራማሪዎች ይህ ትንሽ ፍጥረት ያለውን ችሎታ በመኮረጅ ያለማቀዝቀዣ መሣሪያዎች እርዳታ በራሳቸው የሚያቀዘቅዙ መሣሪያዎችን ለመሥራት ጥረት እያደረጉ ነው።

ታዲያ ምን ይመስልሃል? የሰሃራው ብርማ ጉንዳን ያለው ሙቀት የመከላከል ችሎታ በዝግመተ ለውጥ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?

^ አን.4 ጉንዳኑ ሙቀትን እንዲከላከል ከሚረዱት ሌሎች ነገሮች መካከል በሰውነቱ ውስጥ ያሉት ፕሮቲኖች ኃይለኛ ሙቀት ቢኖርም በቀላሉ ወደ አሚኖ አሲድነት የማይቀየሩ መሆኑ፣ ረጃጅም እግሮቹ ሰውነቱ ትኩስ ከሆነው አሸዋ ከፍ እንዲልና በፍጥነት እንዲሮጥ የሚረዱት መሆኑ እንዲሁም አቅጣጫ የማወቅ ችሎታው በፍጥነት ወደ ጉድጓዱ እንዲመለስ የሚረዳው መሆኑ ይገኙበታል።