በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለምን ሞቼ አልገላገልም?

ለምን ሞቼ አልገላገልም?

የወጣቶች ጥያቄ

ለምን ሞቼ አልገላገልም?

በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወጣቶች ሕይወታቸውን ለማጥፋት ሙከራ ያደርጋሉ፤ ከእነዚህ መካከል በሺዎች የሚቆጠሩት ራሳቸውን ይገድላሉ። ራሳቸውን የሚያጠፉ በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ “የንቁ!” መጽሔት አዘጋጆች ይህንን ርዕስ ማንሳቱ አስፈላጊ እንደሆነ ተሰምቷቸዋል።

“ጌታ ሆይ፣ እባክህ ግደለኝ፤ ከመኖር ይልቅ መሞት ይሻለኛል።” እንዲህ በማለት የተናገረው ማን ነበር? በአምላክ የማያምን ወይም አምላክን የተወ ሰው? ወይስ አምላክ የተወው ሰው? አልነበረም። ከላይ ያለውን ሐሳብ የተናገረው ለአምላክ ያደረ ሰው የነበረው ዮናስ ሲሆን በወቅቱ በጣም ተበሳጭቶ ነበር። * (ዮናስ 4:3 የ1980 ትርጉም) ዮናስ ራሱን ለመግደል ሙከራ አድርጎ እንደነበር የሚገልጽ ሐሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አናገኝም። ያም ሆኖ በጣም ተስፋ ቆርጦ በነበረበት ወቅት ያቀረበው ይህ ጥያቄ አንድ አስፈላጊ እውነታ ያስገነዝበናል:- አንዳንድ ጊዜ የአምላክ አገልጋዮችም እንኳ በከፍተኛ ጭንቀት ሊዋጡ ይችላሉ።—መዝሙር 34:19

አንዳንድ ወጣቶች ከፍተኛ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ስለሚሰማቸው በሕይወት መቀጠል ትርጉም የለሽ ይሆንባቸዋል። እነዚህ ወጣቶች የ16 ዓመቷ ላውራ * የነበራት ዓይነት ስሜት አላቸው፤ ላውራ እንዲህ ብላለች:- “ለበርካታ ዓመታት በተደጋጋሚ ጊዜ በሚያስቸግረኝ የመንፈስ ጭንቀት ስሠቃይ ቆይቻለሁ። ብዙ ጊዜ ራሴን ለመግደል አስባለሁ።” አንድ ሰው ራሱን መግደል እንደሚፈልግ ሲገልጽ ብትሰማ አሊያም አንተ ራስህ እንዲህ ዓይነት ስሜት ቢኖርህ ምን ማድረግ ትችላለህ? በመጀመሪያ እንዲህ ላለው ሐሳብ መነሻ ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮች ምን እንደሆኑ እንመልከት።

ተስፋ እንዲቆርጡ የሚያደርጋቸው ምንድን ነው?

አንድ ሰው ራሱን ለመግደል እንዲያስብ የሚያደርገው ምን ሊሆን ይችላል? በርካታ ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል። አንደኛ ነገር፣ የምንኖረው ‘በሚያስጨንቅ ጊዜ’ ውስጥ በመሆኑ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ በርካታ ወጣቶች በሕይወታቸው ውስጥ የሚደርስባቸውን ተጽዕኖ መቋቋም ይከብዳቸዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ከዚህም በላይ የሰው ልጆች ፍጹማን አለመሆናቸው አንዳንዶች ከራሳቸውም ሆነ በሕይወታቸው ውስጥ ከሚያጋጥሟቸው ነገሮች ጋር በተያያዘ አፍራሽ በሆኑ ሐሳቦች ላይ እንዲያውጠነጥኑ ያደርጋቸዋል። (ሮሜ 7:22-24) አንዳንድ ጊዜ ወጣቶች ራሳቸውን ለመግደል እንዲያስቡ የሚያደርጋቸው ሌሎች የሚያደርሱባቸው በደል ይሆናል። አሊያም ደግሞ የጤንነት ችግር ለዚህ አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይችላል። በአንድ ግምታዊ ሐሳብ መሠረት በአንድ አገር ውስጥ ሕይወታቸውን ካጠፉት ሰዎች መካከል ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት በአእምሮ ሕመም ይሠቃዩ ነበር። *

መከራ የማያጋጥመው ሰው እንደሌለ አይካድም። መጽሐፍ ቅዱስ “ፍጥረት ሁሉ በምጥ ጊዜ እንዳለው ሥቃይ በመቃተት ላይ እንደሚገኝ” ይናገራል። (ሮሜ 8:22) ይህ ደግሞ ወጣቶችንም ይጨምራል። ወጣቶች ቀጥሎ እንደተገለጹት ባሉ መጥፎ ሁኔታዎች በጥልቅ ሊጎዱ ይችላሉ:-

▪ የዘመድ፣ የጓደኛ አሊያም የቤት እንስሳ ሞት

▪ በቤተሰብ መካከል የሚፈጠር ግጭት

▪ በትምህርት መውደቅ

▪ ከፍቅረኛ ጋር መለያየት

▪ በደል (አካላዊ ጥቃት ወይም በጾታ መነወር)

እርግጥ ነው፣ ውሎ አድሮ ሁሉም ወጣቶች ከላይ ከተገለጹት ሁኔታዎች አንዳንዶቹ ሊያጋጥሟቸው ይችላሉ። ታዲያ አንዳንድ ወጣቶች ከሌሎቹ በተሻለ እነዚህን ሁኔታዎች መቋቋም የሚችሉት ለምንድን ነው? ተስፋ ቆርጠው ራሳቸውን ለመግደል የሚሞክሩ ወጣቶች ማንም ሊረዳቸው እንደማይችልና ያጋጠማቸው ችግር መፍትሔ እንደሌለው እንደሚሰማቸው ምሑራን ይናገራሉ። በሌላ አባባል እነዚህ ወጣቶች ያሉበትን ሁኔታ ለማስተካከል ምንም ማድረግ እንደማይችሉ ያምናሉ፤ የተስፋ ጭላንጭልም አይታያቸውም። ዶክተር ካትሊን ማኮይ ለንቁ! መጽሔት እንደገለጹት “አብዛኛውን ጊዜ እነዚህ ወጣቶች መሞት አይፈልጉም። እነሱ የሚሹት ከሥቃያቸው መገላገል ነው።”

ችግሩ መፍትሔ የለውም?

አንድ ሰው ‘ከሥቃዩ ለመገላገል’ ሲል ራሱን መግደል እንደሚፈልግ ሲናገር ሰምተህ ይሆናል። እንዲህ ያለ ሁኔታ ካጋጠመህ ምን ማድረግ ትችላለህ?

አንድ ጓደኛህ መሞት እስኪመኝ ድረስ በጣም ከተጨነቀ እርዳታ እንዲያገኝ ከፍተኛ ጥረት አድርግ። ይህ ሰው ስለ ጉዳዩ ለማንም እንድትናገር ባይፈልግም እንኳ አንተ ኃላፊነት ለሚሰማው ሰው ስለ ሁኔታው ተናገር። ጓደኝነታችን ይበላሻል ብለህ አትስጋ። ጉዳዩን ለሌሎች በመናገር ‘ለክፉ ቀን የተወለደ’ እውነተኛ “ወዳጅ” መሆንህን ታሳያለህ። (ምሳሌ 17:17) እንዲህ በማድረግህ የዚያን ሰው ሕይወት ልታድን ትችል ይሆናል!

አንተ ራስህ ሕይወትህን ለማጥፋት የምታስብ ከሆነስ? ዶክተር ማኮይ እንዲህ ብለዋል:- “እርዳታ ለማግኘት ጥረት አድርግ። ምን እንደሚሰማህ ተናገር። ለሚያስብልህ፣ በቁም ነገር ለሚመለከትህና ለሚያዳምጥህ እንዲሁም በሕይወትህ ውስጥ ትልቅ ቦታ ያላቸው ሌሎች ሰዎች እንዲሰሙህ ማድረግ ለሚችል ሰው ስሜትህን ግለጽ፤ ለወላጆችህ፣ ለዘመድህ፣ ለጓደኛህ፣ ለአስተማሪህ ወይም ለአንድ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ መናገር ትችላለህ።”

ችግርህን ለሌላ ሰው አውጥተህ በመናገርህ ትጠቀማለህ እንጂ የምትጎዳው ነገር የለም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰ አንድ ምሳሌ እንመልከት። ጻድቅ የነበረው ኢዮብ በአንድ ወቅት “ሕይወቴን እጅግ ጠላሁ” ብሎ ነበር። በመቀጠል ግን “ማጕረምረሜን ያለ ገደብ እለቃለሁ፤ በነፍሴም ምሬት እናገራለሁ” ብሏል። (ኢዮብ 10:1) ኢዮብ በጣም ተስፋ ስለቆረጠ ስለ ሥቃዩ ማውራት አስፈልጎት ነበር። አንተም ለአንድ የጎለመሰ ጓደኛህ ስሜትህን አውጥተህ በመናገር እፎይታ ማግኘት ትችል ይሆናል።

በጭንቀት የተዋጡ ክርስቲያኖች ከጉባኤ ሽማግሌዎችም እርዳታ ማግኘት ይችላሉ። (ያዕቆብ 5:14, 15) እርግጥ ነው፣ ችግርህን አውጥተህ መናገርህ ችግሩን ያስወግደዋል ማለት አይደለም። ያም ሆኖ እንዲህ ማድረግህ ሁኔታውን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ እንድትመለከተው ይረዳህ ይሆናል፤ እንዲሁም የምትተማመንበት ጓደኛህ የሚሰጥህ ድጋፍ ለችግሩ መፍትሔ እንድታገኝ ሊረዳህ ይችላል።

ሁኔታዎች ይለወጣሉ

የሚያስጨንቅ ሁኔታ ሲያጋጥምህ አንድ ነገር አስታውስ:- ሁኔታው ምንም ተስፋ የሌለው ቢመስልም ውሎ አድሮ ነገሮች መለወጣቸው አይቀርም። በሕይወቱ በርካታ መከራዎች የተፈራረቁበት መዝሙራዊው ዳዊት “ከመቃተቴ የተነሣ ዝያለሁ፤ ሌሊቱን ሁሉ በልቅሶ ዐልጋዬን አርሳለሁ፤ መኝታዬንም በእንባዬ አሾቃለሁ” በማለት ጸልዮአል። (መዝሙር 6:6) ሆኖም በሌላ መዝሙር ላይ “ዋይታዬን ወደ ሽብሸባ ለወጥህልኝ” ብሏል።—መዝሙር 30:11

ዳዊት በሕይወት ውስጥ ችግሮች መከሰታቸው እንደማይቀርና ከጊዜ በኋላም እንደሚወገዱ ከተሞክሮ ያውቅ ነበር። እርግጥ ነው፣ አንዳንዶቹ ችግሮች በወቅቱ ከአቅምህ በላይ እንደሆኑ ሊሰማህ ይችላል። ያም ቢሆን ታጋሽ መሆን ያስፈልጋል። አብዛኛውን ጊዜ ሁኔታዎች ይስተካከላሉ። አንዳንድ ጊዜ ችግሮቹ ልታስበው በማትችለው መንገድ ይቃለሉ ይሆናል። በሌላ ጊዜ ደግሞ ከዚህ በፊት አስበህበት በማታውቀው ሁኔታ ችግሩን መቋቋም የምትችልበት መንገድ ታገኝ ይሆናል። ያም ሆነ ይህ የሚያስጨንቁህ ችግሮች ሁልጊዜ በዚያ ሁኔታ አይቀጥሉም።2 ቆሮንቶስ 4:17

ጸሎት ያለው ጥቅም

ስሜትህን አውጥተህ ለሰዎች መግለጽህ ጠቃሚ እንደሆነ አይካድም፤ በዚህ ረገድ ከሁሉ የበለጠ ጥቅም የምታገኘው ወደ አምላክ በመጸለይ ነው። አንተም እንደ ዳዊት እንዲህ ብለህ መጸለይ ትችላለህ:- “እግዚአብሔር ሆይ፤ መርምረኝ፤ ልቤንም ዕወቅ፤ ፈትነኝ፤ ሐሳቤንም ዕወቅ፤ የክፋት መንገድ በውስጤ ቢኖር እይ፤ በዘላለምም መንገድ ምራኝ።”—መዝሙር 139:23, 24

ጸሎት ጭንቀትህን አውጥተህ በመናገር ለጊዜው እፎይታ የምታገኝበት ነገር አይደለም። ከዚህ ይልቅ ‘ልብህን እንድታፈስለት’ ለሚፈልገው በሰማይ ላለው አባትህ ሐሳብህን የምትገልጽበት መንገድ ነው። (መዝሙር 62:8) ስለ አምላክ የሚገልጹትን የሚከተሉትን መሠረታዊ እውነቶች ልብ በል:-

▪ ለጭንቀትህ አስተዋጽኦ ያደረጉትን ነገሮችን በሚገባ ያውቃል።—መዝሙር 103:14

▪ አንተ ራስህን ከምታውቀው በላይ አምላክ ያውቅሃል።—1 ዮሐንስ 3:20

▪ ‘እሱ ስለ አንተ ያስባል።’—1 ጴጥሮስ 5:7

▪ አምላክ፣ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ “እንባን ሁሉ [ከዓይንህ] ያብሳል።”—ራእይ 21:4

ችግሩ ከጤንነት ጋር የተያያዘ ሲሆን

ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው አብዛኛውን ጊዜ ራስን የመግደል ሐሳብ የሚመጣው በጤና ችግር ምክንያት ነው። የአንተም ሁኔታ እንዲህ ከሆነ እርዳታ ከመፈለግ ወደኋላ አትበል። ኢየሱስ የታመሙ ሰዎች ሐኪም እንደሚያስፈልጋቸው ገልጿል። (ማቴዎስ 9:12) ደስ የሚለው ነገር፣ ለአብዛኞቹ የጤና እክሎች ሕክምና ማግኘት ይቻላል። አንተም የሕክምና እርዳታ ማግኘትህ ጥሩ ስሜት እንዲኖርህ ሊያደርግ ይችላል!

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ‘“ታምሜአለሁ” የሚል እንደማይኖር’ የሚገልጽ ተስፋ ይዟል። (ኢሳይያስ 33:24) እስከዚያው ጊዜ ግን በሕይወትህ ውስጥ የሚያጋጥሙህን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለመወጣት የተቻለህን ሁሉ አድርግ። በጀርመን የምትኖረው ሃይዲ ያደረገችው ይህንኑ ነበር። ሃይዲ እንዲህ ብላለች:- “አንዳንድ ጊዜ ከፍተኛ ጭንቀት ስለሚሰማኝ ራሴን ለመግደል እፈልግ ነበር። አሁን ግን በጸሎት በመጽናቴና ሕክምና በማግኘቴ ደህና ነኝ።” አንተም እንዲህ ዓይነት እርምጃ በመውሰድ ተመሳሳይ ውጤት ልታገኝ ትችላለህ! *

በሚቀጥለው ጊዜ “የወጣቶች ጥያቄ” በሚለው አምድ ሥር የሚወጣው ርዕስ ወንድምህ ወይም እህትህ ራሳቸውን ቢያጠፉ የሚሰማህን ስሜት እንዴት መቋቋም እንደምትችል ያብራራል

www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “Young People Ask” በሚል አምድ ሥር ተጨማሪ ርዕሶችን ማግኘት ይቻላል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.4 ርብቃ፣ ሙሴ፣ ኤልያስና ኢዮብም ተመሳሳይ ነገር ተናግረው ነበር።—ዘፍጥረት 25:22፤ 27:46፤ ዘኍልቍ 11:15፤ 1 ነገሥት 19:4፤ ኢዮብ 3:21፤ 14:13

^ አን.5 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.7 የአእምሮ ሕመም ያለባቸው አብዛኞቹ ወጣቶች ራሳቸውን እንደማያጠፉ መገንዘብ ያስፈልጋል።

^ አን.33 የመንፈስ ጭንቀትን ለመቋቋም የሚረዱ ተጨማሪ ሐሳቦችን ለማግኘት በመስከረም 2001 ንቁ! ላይ የወጣውን “በመንፈስ ጭንቀት ለሚሠቃዩ ወጣቶች የሚሆን እርዳታ” እንዲሁም በጥር 8, 2004 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ላይ የሚገኘውን “የስሜት መለዋወጥ የሚያስከትለውን ችግር መረዳት” የሚሉትን ርዕሶች ተመልከት።

ሊታሰቡባቸው የሚገቡ ነጥቦች

▪ ‘ራስን መግደል ችግሮችህን አያስወግዳቸውም፤ ከዚህ ይልቅ ወደ ሌላ ሰው ያስተላልፋቸዋል’ የሚል አነጋገር አለ። ይህ እውነት የሆነው እንዴት ነው?

▪ በጣም የሚያስጨንቅ ሁኔታ ሲያጋጥምህ ስሜትህን ለማን ማካፈል ትችላለህ?

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ለወላጆች የተሰጠ ማሳሰቢያ

በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች ወጣቶች ራሳቸውን መግደላቸው በጣም የተለመደ ሆኗል። ለምሳሌ ያህል፣ በዩናይትድ ስቴትስ ከ15 እስከ 25 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ለሚገኙ ወጣቶች ሞት ምክንያት ከሆኑት ነገሮች መካከል ሦስተኛውን ደረጃ የያዘው የራስን ሕይወት ማጥፋት ነው። ከ10 እስከ 14 ዓመት ከሆናቸው ወጣቶች መካከል ባለፉት ሁለት አሥርተ ዓመታት ራሳቸውን የገደሉት ቁጥር በእጥፍ ጨምሯል። በተለይ ደግሞ በአእምሮ ሕመም የሚሠቃዩና ከዚህ ቀደም ራሳቸውን የመግደል ሙከራ አድርገው የነበሩ ወጣቶች ከሌሎች የበለጠ እንዲህ ዓይነት እርምጃ የመውሰድ አዝማሚያ ይታይባቸዋል፤ አንዳንድ ወጣቶች ከቤተሰባቸው አባላት መካከል ሕይወቱን ያጠፋ ሰው ካለ ተመሳሳይ እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ። አንድ ወጣት ሕይወቱን የማጥፋት ሐሳብ እንዳለው ከሚጠቁሙት ምልክቶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል:-

▪ ከቤተሰቡም ሆነ ከጓደኞቹ መራቅ

▪ በአመጋገብና በእንቅልፍ ልማዱ ረገድ ለውጥ ማሳየት

▪ በአንድ ወቅት ይወዳቸው በነበሩት እንቅስቃሴዎች አለመደሰት

▪ ጉልህ የሆነ የባሕርይ ለውጥ ማሳየት

▪ አደገኛ ዕፆችን መውሰድ ወይም የአልኮል መጠጦችን ከልክ በላይ መጠጣት

▪ በጣም የሚወዳቸውን ዕቃዎች ለሌሎች መስጠት

▪ ስለ ሞት ማውራት ወይም ከዚያ ጋር በተያያዙ ነገሮች ላይ ትኩረት ማድረግ

ወላጆች እነዚህን ምልክቶች ችላ ማለታቸው ትልቅ ስህተት እንደሆነ ዶክተር ካትሊን ማኮይ ለንቁ! መጽሔት ገልጸዋል። ዶክተሯ እንዲህ ብለዋል:- “ማንም ሰው፣ ልጁ ችግር እንዳለበት ማሰብ አይፈልግም፤ በመሆኑም አንዳንድ ወላጆች ሁኔታውን ለመቀበል ፈቃደኞች አይሆኑም። ‘ዕድሜው ነው’ ወይም ‘ትንሽ ቆይቶ ይተወዋል’ አሊያም ደግሞ ‘እሷ ድሮም ቢሆን ለየት ያለች ናት’ ብለው ያስቡ ይሆናል። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው አስተሳሰብ አደገኛ ነው። የሚያሰጋ ሁኔታ እንዳለ የሚጠቁሙ ምልክቶች በሙሉ በቁም ነገር መታየት ይኖርባቸዋል።”

ልጃችሁ በከባድ የመንፈስ ጭንቀት ወይም በሌላ ዓይነት የአእምሮ ሕመም የሚሠቃይ ከሆነ እርዳታ መጠየቅ ሊያሳፍራችሁ አይገባም። በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኘው ልጃችሁ ራሱን የመግደል ሐሳብ እንዳለው ከጠረጠራችሁ ስለ ጉዳዩ ጠይቁት። ራስን ስለ መግደል ማውራት አንድ ሰው ድርጊቱን እንዲፈጽም ያነሳሳዋል የሚለው አመለካከት የተሳሳተ ነው። እንዲያውም ወላጆች ስለዚህ ጉዳይ ሲያነሱ በርካታ ወጣቶች ሐሳባቸውን መግለጽ ይቀላቸዋል። ስለዚህ ልጃችሁ ራሱን የመግደል ሐሳብ እንዳለው ከገለጸላችሁ ድርጊቱን ለመፈጸም የሚያስችለው እቅድ አውጥቶ እንደሆነ ጠይቁት፤ ጉዳዩን ምን ያህል እንዳሰበበት ለማወቅ ጥረት አድርጉ። ድርጊቱን በዝርዝር እንዳሰበበት ካወቃችሁ በአፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ይኖርባችኋል። *

ልጃችሁ ያጋጠመው የመንፈስ ጭንቀት ያለምንም እርዳታ ከጊዜ በኋላ እንደሚለቀው በማሰብ አትዘናጉ። ጭንቀቱ የለቀቀው ቢመስላችሁ እንኳ ችግሩ መፍትሔ አግኝቷል ብላችሁ አታስቡ። በልጁ ላይ እንዲህ ያለ ሁኔታ መታየቱ በጣም የሚያሰጋ እንደሆነ አንዳንድ ምሑራን ይገልጻሉ። ለምን? ዶክተር ማኮይ እንዲህ ብለዋል:- “በከባድ የመንፈስ ጭንቀት የሚሠቃይ ልጅ ራሱን የመግደል ሐሳብ ቢኖረውም ድርጊቱን ለመፈጸም አቅም ያጣ ይሆናል። ጭንቀቱ ቀለል ሲልለት ግን ራሱን ለመግደል ኃይል ሊያገኝ ይችላል።”

አንዳንድ ወጣቶች በጣም ተስፋ ከመቁረጣቸው የተነሳ የራሳቸውን ሕይወት የሚያጠፉ መሆኑ እጅግ የሚያሳዝን ነው። ወላጆችም ሆኑ የወጣቶች ደህንነት የሚያሳስባቸው ሌሎች ሰዎች በልጆቹ ላይ የሚታዩትን ምልክቶች በንቃት በመከታተልና ተገቢውን እርምጃ በመውሰድ ‘የተጨነቁትን ነፍሳት ማጽናናት’ እንዲሁም ለወጣቶች እንደ መሸሸጊያ መሆን ይችላሉ።—1 ተሰሎንቄ 5:14 NW

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.55 በተለይ ደግሞ፣ በብዛት ከተወሰደ ሊገድል የሚችል መድኃኒት ወይም በቀላሉ ሊገኝ በሚችል ቦታ የተቀመጠ ሽጉጥ ቤት ውስጥ መኖሩ አደጋውን እንደሚያባብሰው ምሑራን ያስጠነቅቃሉ። በአሜሪካ ራስን መግደልን ለማስቀረት የተቋቋመው ድርጅት፣ ሽጉጥን በተመለከተ እንዲህ ይላል:- “ሽጉጥ ያላቸው አብዛኞቹ ሰዎች በቤታቸው ውስጥ መሣሪያ የሚያስቀምጡት ‘ለጥበቃ’ ወይም ‘ራሳቸውን ለመከላከል’ እንደሆነ ቢገልጹም በእነዚህ ሰዎች ቤት ውስጥ በሽጉጥ ከተገደሉት መካከል 83 በመቶ የሚሆኑት ሕይወታቸውን ያጠፉት ራሳቸው ናቸው፤ አብዛኛውን ጊዜ ደግሞ ራሱን የገደለው የሽጉጡ ባለቤት አይደለም።”

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ስሜትህን አውጥተህ በመግለጽህ ከሁሉ የበለጠ ጥቅም የምታገኘው ወደ አምላክ በመጸለይ ነው