በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የስኬሊ ፉት ቀንድ አውጣ ዛጎል

የስኬሊ ፉት ቀንድ አውጣ ዛጎል

ንድፍ አውጪ አለው?

የስኬሊ ፉት ቀንድ አውጣ ዛጎል

● እስከ አሁን በተፈጥሮ ውስጥ ከታዩት እጅግ ጠንካራ ዛጎሎች አንዱ ነው። ይህ ዛጎል፣ ስኬሊ ፉት እየተባለ የሚጠራው ቀንድ አውጣ ሽፋን ሲሆን ቀንድ አውጣው የሚኖረው በሕንድ ውቅያኖስ ውስጥ ነው፤ ይህ ቀንድ አውጣ 2,400 ሜትር በሚደርስ ጥልቀት ላይ የሚፈጠረውን የውኃ ግፊት መቋቋም ይችላል። ከዚህም በላይ ይህ ባለ ዛጎል ፍጥረት የውኃውን አሲድነት መቋቋም ይችላል፤ እንዲሁም በውቅያኖስ ውስጥ በመሬት ስንጥቆች በኩል የሚፈልቀው ፍል ውኃና የሙቀቱ መጠን መለዋወጥ በዚህ ትንሽ ፍጥረት ላይ ምንም ጉዳት አያስከትሉበትም። የቀንድ አውጣው ዛጎል ከሌሎች ፍጥረታት ጥቃትም ይከላከልለታል።

እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ የስኬሊ ፉት ቀንድ አውጣ ዛጎል የተነባበሩ ሦስት ክፍሎች አሉት። የላይኛው ክፍል ከአይረን ሰልፋይድ የተሠራ ነው፤ ሁለተኛው በሌሎች የቀንድ አውጣ ዝርያዎች ላይ ከሚገኘው የፕሮቲን ሽፋን ጋር ይመሳሰላል፤ ሦስተኛው ደግሞ ኧራግናይት ከተባለ የካልሲየም ማዕድን የተሠራ ነው። ስኬሊ ፉት ቀንድ አውጣ የተነባበረ ሽፋን ስላለው ሸርጣኖች በጠንካራ ጥፍሮቻቸው ዛጎሉን ሊሰብሩት ቢሞክሩም አይሳካላቸውም። አንዳንድ ጊዜ ሸርጣኑ ቀንድ አውጣውን ለቀናት ይዞት ሲታገል ቢቆይም ዛጎሉ አይሰበርለትም።

ዲስከቨር የተባለው መጽሔት እንደገለጸው ተመራማሪዎች፣ ጫፉ ላይ አልማዝ ባለው መሣሪያ በመጠቀም የቀንድ አውጣውን ዛጎል ለመሰንጠቅ ሲሞክሩ መሣሪያው የሚፈጥረውን ኃይል ‘የዛጎሉ የላይኛው ክፍል አምቆ በመያዝ ወደ ውስጥ እንዳያልፍ እንደሚያደርገው’ ተገንዝበዋል። “ስንጥቅ የሚፈጠረው ከአይረን ሰልፋይድ በተሠራው ክፍል ላይ ብቻ ነው። ይህ ‘በጣም ረቂቅ የሆነ ስንጥቅ’ ኃይሉን አምቆ የሚይዘው ከመሆኑም በላይ ትላልቅ ስንጥቆች እንዳይፈጠሩ ይከላከላል።” ዛጎሉ ጥቃት ሲሰነዘርበት የሚፈጠረውን ኃይል የዛጎሉ መካከለኛ ክፍልም አምቆ ይይዘዋል።

ተመራማሪዎች የስኬሊ ፉት ቀንድ አውጣን ዛጎል አሠራር ኮርጀው ይበልጥ ጠንካራ የሆኑ የራስ ቁሮችንና የጥይት መከላከያ ሰደርያዎችን እንዲሁም የመርከብና የአውሮፕላን የውጨኛ ክፍሎችን ለመሥራት ያስባሉ። ይህ የምርምር ውጤት “በተደጋጋሚ ጊዜ የበረዶ ዓለት የሚገጫቸው በአርክቲክ የሚገኙ የነዳጅ ቧንቧዎች እንኳ የበለጠ ጥንካሬ እንዲኖራቸው ለማድረግ ሊረዳ ይችላል” በማለት ዲስከቨር ዘግቧል።

ታዲያ ምን ይመስልሃል? የስኬሊ ፉት ቀንድ አውጣ ዛጎል እንዲሁ በአጋጣሚ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሠንጠረዥ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

መሰንጠቂያ

ውጨኛው ክፍል

መካከለኛው ክፍል

ውስጠኛው ክፍል

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Courtesy Anders Warén