በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

“በ2011 መጀመሪያ ላይ በመላው ዓለም 5.4 ቢሊዮን የሚያህሉ የሞባይል ስልክ ደንበኞች ነበሩ።”—ዩ ኤን ክሮኒክል፣ ዩናይትድ ስቴትስ

ባለፉት አሥር ዓመታት 780,000 የሚያህሉ ሰዎች በአደጋ ምክንያት ሞተዋል፤ በአጠቃላይ በአደጋ ምክንያት ከሞቱት ሰዎች መካከል 60 በመቶ ገደማ የሚሆኑት ሕይወታቸውን ያጡት በመሬት መንቀጥቀጥ ሳቢያ ነው።—ዘ ላንሴት፣ ብሪታንያ

“ባለፉት 20 ዓመታት 800,000 የሚያህሉ ሩሲያውያን ራሳቸውን አጥፍተዋል።”—ሩሲስካያ ጋዝዬታ፣ ሩሲያ

ፍቺ በተከለከለበት በፊሊፒንስ፣ ሕጋዊ ጋብቻ ሳይኖራቸው እንዲሁ አብረው የሚኖሩ ከ15 እስከ 49 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሴቶች ቁጥር “ከ1993 እስከ 2008 ባሉት ዓመታት ከእጥፍ በላይ ጨምሯል።”—ዘ ፊሊፒን ስታር፣ ፊሊፒንስ

ከጆርጅያ ሪፑብሊክ ነዋሪዎች መካከል “79.2 በመቶ የሚሆኑት . . . ከአጫሾች በሚወጣ የሲጋራ ጭስ ሳቢያ ለሚደርስ የጤና ችግር ተጋልጠዋል።” በዋና ከተማው በተብሊሲ “87.7 በመቶ የሚሆኑት ሕፃናት” በዚህ ችግር ይጠቃሉ።—ታቡላ፣ ጆርጂያ

የሕክምና ቱሪዝም በእስያ

በተለያየ የዓለም ክፍል የሚኖሩ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ሰዎች ጥራት ያለውና በአብዛኛው በአገራቸው ከሚከፍሉት ገንዘብ በጣም ባነሰ ዋጋ የሚሰጥ ሕክምና ለመከታተል ሲሉ ወደ ውጭ አገሮች ይጓዛሉ። ቢዝነስ ወርልድ እንደዘገበው በየዓመቱ ወደ ፊሊፒንስ “ለሕክምና የሚመጡ ቱሪስቶች” ቁጥር በ2015 አንድ ሚሊዮን እንደሚደርስ ይጠበቃል፤ በ2020 ደግሞ ተመሳሳይ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ወደ ደቡብ ኮሪያ እንደሚመጡ ይጠበቃል። ሕንድ፣ ማሌዥያ፣ ሲንጋፖርና ታይላንድም በዚህ ረገድ ታዋቂ መዳረሻዎች ናቸው። ወደ እነዚህ አገሮች የሚመጡት ሰዎች የልብ ወይም የአጥንትና የመገጣጠሚያ በሽታን የመሰሉ ከባድ ሕመሞችን ለመታከም የሚሄዱ ምዕራባውያን ብቻ አይደሉም። በቅርቡ ባለጠጋ የሆኑ በርካታ ቻይናውያንም “መምሰል የሚፈልጓቸውን ታዋቂ ሰዎች” ፎቶግራፍ ይዘው የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ወደሚያደርጉ ባለሙያዎች መጉረፍ እንደጀመሩ አንድ ሪፖርት ተናግሯል።

በአንድ ጊዜ ብዙ ነገሮችን የሚያከናውኑ ሰዎች ውጤታማ አይደሉም

አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በመምጣታቸው ብዙ ጊዜ ሠራተኞች ውስብስብ የሆኑ በርካታ ሥራዎችን በአንድ ጊዜ ለማከናወን ብሎም የተለያዩ ጥያቄዎችን በፍጥነት ለማስተናገድ ይገደዳሉ። ይሁን እንጂ “በአንድ ጊዜ ብዙ ነገሮችን የሚያከናውኑ ሠራተኞች በሥራቸው ውጤታማ [እንዳልሆኑ]” በስታንፎርድ ዩኒቨርስቲ ውስጥ በሰዎችና ቴክኖሎጂ ባፈራቸው የመገናኛ መሣሪያዎች መካከል ስለሚኖረው ግንኙነት የሚያጠና ቤተ ሙከራ ዳይሬክተር የሆኑት ክሊፈርድ ናስ ተናግረዋል። በአንድ ጊዜ ብዙ ተግባሮችን የሚያከናውኑ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ውጥረት እንደሚገጥማቸው፣ አላስፈላጊ ነገሮች በቀላሉ ትኩረታቸውን እንደሚከፋፍሉባቸው፣ ጠለቅ ብሎ ማሰብ እንደሚሳናቸውና በዚህም ምክንያት አስፈላጊ የሆኑ ዝርዝር ጉዳዮችን እንደሚስቱ ተዘግቧል። በመሆኑም ናስ የሚከተለውን ሐሳብ አቅርበዋል፦ “አንድ ነገር ማድረግ ስትጀምር ለ20 ደቂቃ ያህል ያንን ሥራ እንጂ ሌላ ምንም ነገር አታድርግ። ይህም በአንድ ነገር ላይ የማተኮር እንዲሁም በጥልቀት የማሰብ ችሎታ እንድታዳብር ያሠለጥንሃል።”