በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ንድፍ አውጪ አለው?

የተስፈንጣሪው ሸረሪት ብዥ ያለ እይታ

የተስፈንጣሪው ሸረሪት ብዥ ያለ እይታ

ተስፈንጣሪው ሸረሪት (ጃምፒንግ ስፓይደር) የሚዘለውን ርቀት በትክክል ለማስላት የሚያስችል ለየት ያለ እይታ አለው። ሸረሪቱ ይህን የሚያደርገው እንዴት ነው?

እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ ይህ ሸረሪት ዘሎ የሚያርፍበት ነገር ምን ያህል እንደሚርቅ ለመለካት ሁለቱ ዋነኛ ዓይኖቹ ያላቸውን ልዩ ችሎታ ይጠቀማል፤ የእነዚህ ዓይኖች ሬቲና ንብርብር ሆኖ የተሠራ ነው። ንብርብር ከሆኑት ክፍሎች አንደኛው አረንጓዴ ቀለምን ጥርት አድርጎ የሚቀበል ሲሆን ሌላኛው ክፍል ደግሞ ብዥ አድርጎ ይቀበላል። ምስሉ በጣም ብዥ ያለ መሆኑ ሸረሪቱ የሚያየው ነገር በጣም ቅርብ መሆኑን ለማወቅ ያስችለዋል። ይህ ደግሞ የሚዘልበትን ርቀት በትክክል ለማስላትና የሚያድነውን ነገር ለመያዝ ያስችለዋል።

ተመራማሪዎች ይህ ሸረሪት የሚጠቀምበትን ዘዴ በመቅዳት የአንድን ነገር ርቀት በትክክል መለካት የሚችሉ ባለ ሦስት ጎንዮሽ (3-D) ካሜራዎችን አልፎ ተርፎም ሮቦቶችን ለመሥራት አስበዋል። ሳይንስናው የተባለው በኢንተርኔት ላይ የሚገኝ የዜና አውታር እንደገለጸው ከሆነ “ግማሽ ሴንቲ ሜትር ርዝመትና ከዝንብ አንጎል ያነሰ አንጎል ያላቸው እንስሳት፣ ውስብስብ የሆኑ የእይታ መረጃዎችን ተቀብለው በዚያ መሠረት እርምጃ መውሰድ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ” ለማሳየት የተስፈንጣሪው ሸረሪት እይታ “ግሩም ምሳሌ” ነው።

ታዲያ ምን ይመስልሃል? ተስፈንጣሪው ሸረሪት የሚጠቀምበት ብዥ ያለ እይታ በዝግመተ ለውጥ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?