በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“አምላክ ፈውስ ማግኘት እንድንችል ረድቶናል”

“አምላክ ፈውስ ማግኘት እንድንችል ረድቶናል”

ናታልያ ከዘጠኝ ዓመት ልጇ ከአስላን ጋር ዛሪና ደግሞ ከአሥራ ሁለት ዓመት ልጇ ከአንዠሊካ ጋር ጎን ለጎን ኩርምት ብለው ተቀምጠዋል። ከ1,000 የሚበልጡ ሌሎች ልጆችና ትላልቅ ሰዎችም ከባድ መሣሪያ በታጠቁ ሰዎች እየተጠበቁ እዚያው ተቀምጠዋል።

ረቡዕ መስከረም 1, 2004 ቀን በአላንያ፣ ሩሲያ በሚገኝ ቤስላን በተባለች ትንሽ ከተማ ውስጥ ባለ ትምህርት ቤት የሚማሩ ልጆችና ወላጆቻቸው የመጀመሪያውን የትምህርት ቀን አስመልክቶ በሚደረገው ፕሮግራም ላይ ለመካፈል ተሰብስበው ነበር። በዚህ ጊዜ ጠመንጃ ያነገቡ ሰዎችና አጥፍቶ ጠፊዎች ወደ ሰማይ እየተኮሱና እየጮኹ ድንገት ዘው ብለው መካከላቸው ገቡ። ከ30 የሚበልጡት ታጣቂዎች በድንጋጤ የተዋጡትን ልጆችና ወላጆች ወደ ትምህርት ቤቱ ጂምናዚየም እንዲገቡ ካደረጉ በኋላ ዙሪያውን በፈንጂ አጠሩት።

ታጋቾቹ የነበሩበት ሁኔታ

ለሦስት ቀናት የቆየው የታጣቂዎቹና የጸጥታ ኃይሎቹ ፍጥጫ የጀመረው በዚህ መንገድ ነበር። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ታጠና የነበረችው ናታልያ “የዚያን ያህል የጸለይኩበት ጊዜ የለም” ብላለች።

የበጋ ወራት ስለነበረ ጂምናዚየሙ ከመታፈኑ የተነሳ በጣም ይሞቅ ነበር። ከሁለተኛው ቀን ጠዋት ጀምሮ ታጣቂዎቹ ላገቷቸው ሰዎች ምግብና ውኃ መስጠት አቆሙ፤ በሦስተኛው ቀን ማለትም ዓርብ ዕለት አንዳንድ ታጋቾች ሽንት እስከ መጠጣትና ልጆቹ ለአስተማሪዎቻቸው ያመጡትን አበባ እስከ መብላት ደርሰው ነበር። ናታልያ እንዲህ ብላለች፦ “አጠገባችን የተቀመጠ ልጅ እጄ ላይ አንድ ቅጠል አስቀመጠልኝ። እኔም ለሁለት ቆረጥኩትና ግማሹን ለአንዠሊካ፣ ግማሹን ደግሞ ለአስላን ሰጠኋቸው።”

ከዚያም በሦስተኛው ቀን የሆነ ሰዓት ላይ ሁከት ተፈጠረ። ናታልያ “በፍንዳታው የተነሳ ወደቅኩ። አየሩ በጭስ ተሞላ፤ ከዚያም ተኩስ ተጀመረ” በማለት ተናግራለች። ወታደሮቹና አሸባሪዎቹ እየተታኮሱ ሳለ ናታልያና አስላን መሬት ለመሬት እየተንከባለሉ ወጡ። አላን የተባለ አንድ ኦሴሽያዊ ጎትቶ ስላወጣቸው በሕይወት መትረፍ ቻሉ። ሌሎች በርካታ ሰዎች ግን ማምለጥ ሳይችሉ ቀሩ።

ጥቃቱ ያስከተለው መዘዝ

በሁከቱ መሃል የሞተችው አንዠሊካ

አንዠሊካን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ልጆችና አዋቂዎች ሞቱ። በቤስላን አካባቢ ለሳምንታት ያህል ለቅሶና ዋይታ ሲሰማ ቆየ። የናታልያ መኖሪያ የሚገኘው ከትምህርት ቤቱ ትይዩ ነበር፤ አዲስ ትምህርት ቤት በአቅራቢያው ከተሠራ በኋላም እንኳ አስላን ወደ ትምህርት ቤቱ ለመሄድ ፈቃደኛ አልሆነም። ለመጫወት እንኳ ከቤት መውጣት ፈራ። ናታልያ “ፍርሃቱን ለማስወገድ እንዲረዳው ይሖዋን ተማጸንን” ብላለች። ከጊዜ በኋላ ወደ ትምህርት ቤት ለመሄድ የሚያስችለውን ድፍረት አገኘ።

ለናታልያ ፈተና የሆነባት በመንግሥት አዳራሽ በሚደረጉት ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “ብዙ ሰዎች በተሰበሰቡበት ቦታ ላይ ስገኝ ሕንጻው በድንገት ጥቃት የሚሰነዘርበት ይመስለኛል። ምንም ነገር እንዳይደርስ እጸልያለሁ። ከጊዜ በኋላ ግን ወደ ስብሰባ መሄድ አቆምኩ። እኛ በሕይወት ስንተርፍ ሕይወታቸውን ያጡ ብዙ ሰዎች እንዳሉ ማወቄም በጣም ይረብሸኝ ነበር።”

ፈውስ ማግኘት ቻልኩ

ናታልያ “ሳያቋርጡ የረዱኝን የጉባኤው አባላት አመሰግናቸዋለሁ። ታትያና የምትባል የይሖዋ ምሥክር በየሦስት ቀኑ ሳታሰልስ መጥታ ትጠይቀኝ ነበር። ከጊዜ በኋላ ደግሞ ኡልያና የምትባል መጽሐፍ ቅዱስን በደንብ የምታውቅ የይሖዋ ምሥክር ይዛ መጣች፤ ኡልያና ደግና ዘዴኛ ከመሆኗም ሌላ ለስላሳ አንደበት ያላት ነበረች። ላደረግኩት ጥረት ታመሰግነኝና በደንብ ታዳምጠኝ ነበር።

“አሁን ምሬትም ሆነ ፍርሃት ሳይሰማኝ ስለዚያ ቀን ማውራት ችያለሁ”

“ኡልያና ሐዋርያው ጳውሎስ በ2 ቆሮንቶስ 1:9 ላይ የተናገረውን ሐሳብ አነበበችልኝ። ጳውሎስ በእስያ ብዙ መከራ ካሳለፈ በኋላ ‘የሞት ፍርድ ተፈርዶብናል የሚል ስሜት አድሮብን ነበር’ ብሏል። በተጨማሪም በኢሳይያስ 40:31 ላይ የሚገኘውን ‘ይሖዋን ተስፋ የሚያደርጉ ግን ኃይላቸው ይታደሳል። እንደ ንስር በክንፍ ወደ ላይ ይወጣሉ’ የሚለውን ሐሳብ አነበበችልኝ። እንደነዚህ ያሉት ጥቅሶችና ኡልያናም ሆነች ሌሎች ሳያቋርጡ ይሰጡኝ የነበረው ስሜታዊ ድጋፍ አበርትቶኝ ከልጆቼ ጋር በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመርኩ። ያም ሆኖ መንግሥት አዳራሽ ውስጥ ስሆን አሁንም ድረስ ይጨንቀኛል።”

ዛሪና ከጊዜ በኋላ የይሖዋ ምሥክር ሆነች፤ ልጇን አንዠሊካን በአምላክ መንግሥት በሚተዳደረው የተዋበና ሰላም የሰፈነበት ምድር ከሞት ተነስታ የምትቀበልበትን ጊዜ በናፍቆት ትጠባበቃለች። (ማቴዎስ 6:9, 10፤ የሐዋርያት ሥራ 24:15) ናታልያና ልጆቿ በ2009 ተጠመቁ። አሁንም የሚኖሩት በጂምናዚየሙ ፍርስራሽ አጠገብ ቢሆንም ጭንቀታቸው ቀለል ብሎላቸዋል። ናታልያ “አሁን ምሬትም ሆነ ፍርሃት ሳይሰማኝ ስለዚያ ቀን ማውራት ችያለሁ። አምላክ ፈውስ ማግኘት እንድንችል ረድቶናል” ብላለች።