በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሕይወት ታሪክ

ከአምላክና ከእናቴ ጋር ሰላም መፍጠር

ከአምላክና ከእናቴ ጋር ሰላም መፍጠር

“የቀድሞ አባቶችሽን የማታመልኪው ደግሞ ለምንድን ነው? ሕይወት ያገኘሽው ከእነሱ እንደሆነ አታውቂም? ታዲያ ለዚህ አታመሰግኛቸውም? ለዘመናት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን ባሕል እንዴት አሽቀንጥረሽ ትጥዪዋለሽ? የቀድሞ አባቶቻችንን አላከብርም ካልሽ አምልኳችን ከንቱ ነው ማለትሽ ነው።” እናቴ ይህን ካለችኝ በኋላ ስቅስቅ ብላ አለቀሰች።

እናቴ እንደዚህ ተናግራኝ አታውቅም። ደግሞም መጽሐፍ ቅዱስ እንዳጠና ሁኔታዎችን ያመቻቸችው እሷ ነበረች፤ እርግጥ ይህን ያደረገችው እሷ ማጥናት ስላልፈለገችና የይሖዋ ምሥክሮቹን ላለማሳዘን ስትል ነው። ሁልጊዜም እናቴን እታዘዛት ስለነበር አሁን ትእዛዟን መጣስ በጣም ከበደኝ። ይሖዋን ማስደሰት ከፈለግኩ ግን ይህን ማድረግ ነበረብኝ። ይሖዋ ኃይል ባይሰጠኝ ኖሮ ልፈጽመው የማልችለው ነገር ነበር።

ክርስቲያን መሆን

በጃፓን እንደሚኖሩት አብዛኞቹ ሰዎች ሁሉ እኛም የቡድሂዝም እምነት ተከታዮች ነበርን። ይሁንና ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ለሁለት ወር ካጠናሁ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት መሆኑን ተገነዘብኩ። በሰማይ የሚኖር አባት እንዳለኝ ስማር ስለ እሱ ለማወቅ ጓጓሁ። እየተማርኩ ያለሁትን ነገር ከእናቴ ጋር መወያየት ያስደስተን ነበር። እሁድ እሁድ በመንግሥት አዳራሽ በሚደረገው ስብሰባ ላይ መገኘት ጀመርኩ። ስለ እውነት ያለኝ እውቀት እየጨመረ ሲሄድ በቡድሂዝም የአምልኮ ሥርዓቶች ከዚህ በኋላ እንደማልካፈል ለእናቴ ነገርኳት። ይህን ስላት አመለካከቷ በድንገት ተለወጠ። “በቤተሰባችን ውስጥ የቀድሞ አባቶቻችንን የማይወድ ሰው መኖሩ ለቤተሰቡ ውርደት ነው” አለችኝ። መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናቴንና በስብሰባዎች ላይ መገኘቴን እንዳቆም አዘዘችኝ። እናቴ ይህን ትላለች ብዬ ፈጽሞ አላሰብኩም! ሌላ ሰው መሰለችኝ።

አባቴም ከእናቴ ጋር ወገነ። ኤፌሶን ምዕራፍ 6 እንደሚናገረው ይሖዋ ወላጆቼን እንድታዘዝ ይፈልጋል። መጀመሪያ ላይ፣ እነሱ የሚሉትን ካደረግኩ ውሎ አድሮ እነሱም የእኔን ሐሳብ እንደሚሰሙና በቤተሰባችን ውስጥ ሰላም እንደሚሰፍን አስቤ ነበር። በዚህ ላይ ደግሞ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለመግባት የምወስደው ፈተና እየተቃረበ በመሆኑ ለፈተናው መዘጋጀት ነበረብኝ። ስለዚህ ለሦስት ወር እነሱ ያሉትን ለማድረግ ተስማማሁ፤ ይህ ጊዜ ሲያልቅ ግን እንደገና ስብሰባ መሄድ እንደምጀምር ለይሖዋ ቃል ገባሁ።

ሆኖም ውሳኔዬ በሁለት ምክንያቶች የተነሳ ስህተት ነበር። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ይሖዋን ለማገልገል ያለኝ ፍላጎት በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ እንደማይለወጥ ተሰምቶኝ ነበር። ይሁንና በመንፈሳዊ እየተራብኩ ስለነበር ከይሖዋ እየራቅሁ ሄድኩ። በሁለተኛ ደረጃ፣ እናቴና አባቴ የእኔን ሐሳብ ለመስማት ፈቃደኛ ከመሆን ይልቅ ከእውነተኛው አምልኮ ጋር የተያያዘ ማንኛውንም ነገር እንዳቆም ይበልጥ ጫና ያሳድሩብኝ ጀመር።

ያገኘሁት እርዳታና የደረሰብኝ ተቃውሞ

የቤተሰብ ተቃውሞ እያጋጠማቸው ያሉ ብዙ ክርስቲያኖች በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ አግኝቼ ነበር። እነሱም ይሖዋ እንደሚያበረታኝ ማረጋገጫ ሰጡኝ። (ማቴ. 10:34-37) ቤተሰቤ መዳን እንዲችል እኔ ትልቅ ሚና እንደምጫወት አበክረው ነገሩኝ። በይሖዋ መታመን እፈልግ ነበር፤ ስለዚህ አጥብቄ መጸለይ ጀመርኩ።

ቤተሰቤ ተቃውሞ የሚያደርስብኝ በተለያየ መንገድ ነበር። እናቴ ትለምነኝ እንዲሁም ልታሳምነኝ ትሞክር ነበር። እንዲህ ስታደርግ መልስ አልሰጣትም። ምክንያቱም መናገር ስጀምር ብዙውን ጊዜ ሁለታችንም የየራሳችን ሐሳብ ትክክል መሆኑን ለማሳመን ስለምንጥር እንጨቃጨቃለን። አሁን ሳስበው ግን የእናቴን ስሜትና የምታምንባቸውን ነገሮች እንደማከብርላት ብገልጽላት ኖሮ ሁኔታዎች ሊረጋጉ ይችሉ እንደነበር ይሰማኛል። ወላጆቼ ከቤት እንዳልወጣ ለማድረግ ሲሉ የቤት ውስጥ ሥራዎችን ያበዙብኝ ጀመር። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ቤት እንዳልገባ በሩን ይቆልፉብኝ አሊያም ምግብ ይከለክሉኝ ነበር።

እናቴ በዚህ ረገድ እንዲረዷት ሌሎችን መጠየቅ ጀመረች። ለትምህርት ቤት አስተማሪዬ ጉዳዩን ብትነግረውም እሱ ጣልቃ መግባት አልፈለገም። በተጨማሪም ወደ ሥራ ቦታዋ ይዛኝ በመሄድ አለቃዋ፣ ሁሉም ሃይማኖቶች ከንቱ መሆናቸውን እንዲያሳምነኝ ለማድረግ ሞከረች። ለተለያዩ ዘመዶቻችንም ስልክ በመደወል እንዲረዷት እያለቀሰች ለመነቻቸው። እንዲህ ማድረጓ በጣም አበሳጨኝ፤ የጉባኤ ሽማግሌዎች ግን እናቴ ሳታውቀው ለእነዚህ ሰዎች ሁሉ ምሥክርነት እየሰጠች መሆኑን እንዳስብ ያበረታቱኝ ነበር።

ከዚያ ደግሞ ዩኒቨርሲቲ የመግባት ጉዳይ ተነሳ። ወላጆቼ በሕይወቴ ጥሩ ጅምር እንዲኖረኝ ሊረዱኝ ይፈልጉ ነበር። ዓላማቸው ጥሩ ሥራ እንዳገኝ ነበር። እኔም ሆንኩ ወላጆቼ በጉዳዩ ላይ ስሜታዊ ሆነን ስለነበር ተረጋግተን መነጋገር አልቻልንም፤ በመሆኑም ለእናቴና ለአባቴ ግቤን ለማስረዳት ደብዳቤዎች ጻፍኩላቸው። አባቴ በቁጣ ገንፍሎ “ሥራ አገኛለሁ የምትዪ ከሆነ ነገውኑ ማግኘት አለብሽ፤ አለዚያ ከቤት ትባረሪያለሽ” በማለት አስፈራራኝ። እኔም ስለ ጉዳዩ ወደ ይሖዋ ጸለይኩ። በማግስቱ አገልግሎት ላይ እያለሁ ሁለት የተለያዩ እህቶች ልጆቻቸውን ትምህርት እንዳስጠናላቸው ጠየቁኝ። አባቴ በዚህ ስላልተደሰተ እኔን ማናገሩን ጨርሶ አቆመ፤ እንዲያውም ቤት ውስጥ እንዳለሁ አድርጎ አይቆጥረኝም ነበር። እናቴም የይሖዋ ምሥክር ከምሆን ዓመፀኛ ልጅ ብሆን እንደምትመርጥ ነገረችኝ።

ይሖዋ አመለካከቴን እንዳስተካክልና ምን ማድረግ እንዳለብኝ እንዳውቅ ረድቶኛል

የወላጆቼን ትእዛዝ የዚህን ያህል አለማክበሬ ይሖዋ የሚቀበለው ነገር ስለመሆኑ አንዳንድ ጊዜ ጥያቄ ይፈጠርብኝ ነበር። ሆኖም ስለ ይሖዋ ፍቅር በሚናገሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ላይ ማሰላሰሌና አጥብቄ መጸለዬ፣ ስለሚደርስብኝ ተቃውሞ አዎንታዊ አመለካከት እንዳዳብር እንዲሁም ወላጆቼ ይህን የሚያደርጉበት አንዱ ምክንያት ለእኔ ያላቸው አሳቢነት መሆኑን እንድገነዘብ ረድቶኛል። ይሖዋ አመለካከቴን እንዳስተካክልና ምን ማድረግ እንዳለብኝ እንዳውቅ ረድቶኛል። ከዚህም በላይ ብዙ ባገለገልኩ መጠን አገልግሎትን ይበልጥ እየወደድኩት መጣሁ። በመሆኑም አቅኚነትን ግቤ አደረግኩት።

አቅኚ ሆኖ ማገልገል

አንዳንድ እህቶች አቅኚ መሆን እንደምፈልግ ሲያውቁ ወላጆቼ እስኪረጋጉ ድረስ እንድቆይ ምክር ሰጡኝ። እኔም ጥበብ እንዲሰጠኝ ወደ ይሖዋ ጸለይኩ፣ በጉዳዩ ላይ ምርምር አደረግኩ እንዲሁም አቅኚ ለመሆን የፈለግኩበትን ምክንያት ቆም ብዬ አሰብኩበት፤ ከዚያም የጎለመሱ ወንድሞችንና እህቶችን አማከርኩ። ይህም ፍላጎቴ ከማንም በላይ ይሖዋን ማስደሰት እንደሆነ እንዳስተውል ረዳኝ። ከዚህም በተጨማሪ አቅኚ የመሆን ግቤን ለሌላ ጊዜ ማስተላለፌ የወላጆቼ አመለካከት እንደሚለወጥ ዋስትና ሊሆን አይችልም።

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን በማጠናቅቅበት ዓመት አቅኚ ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ። ለተወሰነ ጊዜ በአቅኚነት ካገለገልኩ በኋላ የምሥራቹ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አካባቢ ለመዛወር ግብ አውጥቼ ነበር። ሆኖም እናቴና አባቴ ከቤት ርቄ እንድኖር አልፈለጉም። በመሆኑም 20 ዓመት እስኪሞላኝ ድረስ ጠበቅኩ። ከዚያም ዘመዶቻችን ባሉበት በደቡባዊ ጃፓን እንድመደብ ቅርንጫፍ ቢሮውን ጠየቅኩ፤ ይህን ያደረግኩት እናቴ እንዳትጨነቅ ብዬ ነው።

እዚያ ምድብ ላይ እያለሁ መጽሐፍ ቅዱስን ያስጠናኋቸው ሰዎች ሲጠመቁ በማየቴ እንደተባረክሁ ይሰማኛል። በዚህ መሃል፣ አገልግሎቴን ማስፋት እንድችል እንግሊዝኛ ተማርኩ። በጉባኤያችን ውስጥ ልዩ አቅኚ የሆኑ ሁለት ወንድሞች ነበሩ። እነዚህ ወንድሞች ያላቸውን ቅንዓትና ሌሎችን እንዴት እንደሚረዱ እመለከት ነበር። በመሆኑም ልዩ አቅኚ የመሆን ግብ አወጣሁ። እዚያ እያለሁ እናቴ ሁለት ጊዜ ከባድ የጤና እክል አጋጥሟት ነበር። በሁለቱም ጊዜያት ወደ ቤት ሄጄ ተንከባክቤያታለሁ። እንዲህ ማድረጌ ያስገረማት ሲሆን አመለካከቷም በተወሰነ መጠን መለወጥ ጀመረ።

የተትረፈረፈ በረከት

ከሰባት ዓመት በኋላ ቀደም ሲል ከጠቀስኳቸው ልዩ አቅኚዎች አንዱ ደብዳቤ ጻፈልኝ። አትሱሺ የተባለው ይህ ወንድም ለትዳር እንደሚፈልገኝ ከገለጸ በኋላ ስለዚህ ጉዳይ ምን እንደሚሰማኝ እንዲሁም ስላለሁበት ሁኔታ ጠየቀኝ። ከአትሱሺ ጋር የፍቅር ግንኙነት ለመመሥረት ፈጽሞ አስቤ አላውቅም፤ ለነገሩ እሱም ለእኔ እንዲህ ዓይነት ስሜት ይኖረዋል ብዬ አላስብም ነበር። ከአንድ ወር በኋላ፣ ከእሱ ጋር ይበልጥ ለመተዋወቅ ፈቃደኛ መሆኔን የሚገልጽ ደብዳቤ ጻፍኩለት። መጠናናት ስንጀምር፣ የምንመሳሰልባቸው ብዙ ነገሮች እንዳሉ ተገነዘብን፤ ሁለታችንም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈል የምንፈልግ ከመሆኑም ሌላ በየትኛውም ምድብ ለማገልገል ፈቃደኞች ነን። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ትዳር መሠረትን። በሠርጋችን ላይ እናቴ፣ አባቴና አንዳንድ ዘመዶቻችን በመገኘታቸው በጣም ተደስቻለሁ!

ኔፓል

ከተጋባን ብዙም ሳይቆይ፣ የዘወትር አቅኚ ሆነን እያገለገልን ሳለ አትሱሺ ተተኪ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኖ ተሾመ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ደግሞ ሌሎች በረከቶች አገኘን። ልዩ አቅኚዎች ሆነን የተሾምን ሲሆን ከዚያም በወረዳ ሥራ በቋሚነት እንድንካፈል ተመደብን። በወረዳችን ውስጥ የሚገኙትን ጉባኤዎች በሙሉ አንድ ጊዜ ከጎበኘን በኋላ ከቅርንጫፍ ቢሮው ስልክ ተደወለልን። ቅርንጫፍ ቢሮው ‘ኔፓል ሄዳችሁ በወረዳ ሥራ ለማገልገል ፈቃደኞች ናችሁ?’ የሚል ጥያቄ አቀረበልን።

በተለያዩ አገሮች ማገልገላችን ስለ ይሖዋ ብዙ አስተምሮኛል

ይህን ያህል ርቄ ስለመሄዴ ወላጆቼ ምን ሊሰማቸው እንደሚችል አሳሰበኝ። በመሆኑም ደወልኩላቸው። ስልኩን ያነሳው አባቴ ሲሆን እሱም “የምትሄጂው ወደ ጥሩ ቦታ ነው” አለኝ። ከዚያ በፊት ባለው ሳምንት አንድ ጓደኛው ስለ ኔፓል የሚናገር መጽሐፍ ሰጥቶት ነበር፤ እንዲያውም አባቴ ኔፓልን ለመጎብኘት እያሰበ ነበር።

ወዳጃዊ መንፈስ ባላቸው የኔፓል ሕዝቦች መካከል በደስታ እያገለገልን ሳለ ሌላ በረከት አገኘን። ባንግላዴሽ እኛ በምንጎበኘው ወረዳ ውስጥ እንደተካተተች ተነገረን፤ ባንግላዴሽ ለኔፓል ቅርብ ብትሆንም በብዙ መንገዶች ትለያለች። በአገልግሎታችን የተለያዩ ሰዎችን እናገኝ ነበር። ከአምስት ዓመት በኋላ ደግሞ እንደገና በጃፓን እንድናገለግል ተመደብን፤ እዚህም በወረዳ ሥራ እየተካፈልን ነው።

በጃፓን፣ በኔፓልና በባንግላዴሽ ማገልገላችን ስለ ይሖዋ ብዙ አስተምሮኛል! በእያንዳንዱ አገር የሚኖሩ ሰዎች የየራሳቸው አስተዳደግና የተለያየ ባሕል አላቸው። እያንዳንዱ ሰው ደግሞ ከሌላው የተለየ ነው። ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ለሰዎች የሚያስብ አምላክ እንደሆነ እንዲሁም እንደሚቀበላቸው፣ እንደሚረዳቸውና እንደሚባርካቸው መመልከት ችያለሁ።

ለእኔ በግሌ ደግሞ ይሖዋ ብዙ በረከት ሰጥቶኛል፤ እሱን እንዳውቀውና እንዳገለግለው ፈቅዶልኛል፤ እንዲሁም ክርስቲያን የሆነ ጥሩ የትዳር ጓደኛ ሰጥቶኛል። አምላክ ትክክለኛ ውሳኔዎችን እንዳደርግ መርቶኛል፤ በአሁኑ ጊዜ ከእሱም ሆነ ከቤተሰቤ ጋር ጥሩ ግንኙነት አለኝ። እኔና እናቴ እንደ ድሮው ጥሩ ጓደኛሞች መሆን በመቻላችን ይሖዋን አመሰግነዋለሁ። ከአምላክና ከእናቴ ጋር ሰላም መፍጠር በመቻሌ በጣም አመስጋኝ ነኝ።

በወረዳ ሥራ መካፈላችን በጣም ያስደስተናል