በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የማመልከውን አምላክ ማወቅ ቻልኩ

የማመልከውን አምላክ ማወቅ ቻልኩ

የመፈወስ ኃይል እንዳለው የሚነገርለት አንድ የጴንጤቆስጤ ቤተ ክርስቲያን ወንጌላዊ ሊጎበኘን መጣ። ወንጌላዊው ልክ ሲነካኝ ራሴን ስቼ ወደቅሁ ወይም “መንፈስ ጣለኝ።” ስነቃ እፈልገው የነበረውን ነገር ይኸውም የመፈወስ ኃይል እንዳገኘሁ ተሰማኝ። ይሁንና እንዲህ ያለ ሁኔታ ሊያጋጥመኝ የቻለው እንዴት ነው? ይህ ሁኔታስ በሕይወቴ ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድሯል? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ከመስጠቴ በፊት እስቲ ስለ ቀድሞ ሕይወቴ ላውጋችሁ።

ታኅሣሥ 10, 1968 በኢሎኮስ ኖርቲ፣ ፊሊፒንስ ተወለድኩ፤ በቤተሰባችን ውስጥ ካሉት አሥር ልጆች መካከል እኔ ሰባተኛ ነበርኩ። በፊሊፒንስ እንደሚኖሩት አብዛኞቹ ሰዎች ሁሉ እኛም ከልጅነታችን ጀምሮ የካቶሊክ እምነት ተከታዮች ነበርን። በ1986 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ያጠናቀቅሁ ሲሆን ነርስ የመሆን ፍላጎት ነበረኝ። ይሁንና ከባድ ሕመም ስላደረብኝ ይህን ሕልሜን እውን ማድረግ አልቻልኩም። እንዲያውም በጠና በመታመሜ የምሞት መስሎኝ ነበር። በጭንቀት ተውጬ ስለነበር እንዲረዳኝ አምላክን ተማጸንኩት፤ ከሕመሜ እንዳገግም ከረዳኝ ሕይወቴን በሙሉ እንደማገለግለው ቃል ገባሁ።

ከበሽታዬ ለማገገም ረጅም ጊዜ ቢፈጅብኝም ለአምላክ የተሳልኩትን ስእለት አልረሳሁም። በመሆኑም ሰኔ 1991 ወደ አንድ የጴንጤቆስጤ ቤተ ክርስቲያን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ገባሁ። የምንማረው ትምህርት “የመንፈስ ቅዱስን ነፃ ስጦታ” እንደሚያስገኝልን ይገለጽ ነበር። እኔም የመፈወስ ኃይል እንዲኖረኝ እፈልግ ነበር። ትምህርት ቤቱ፣ ይህን ኃይል ማግኘት የሚቻለው በጾምና በጸሎት እንደሆነ ያስተምራል። በአንድ ወቅት፣ እንዲህ ዓይነት “ስጦታ” እንዳለኝ ለማስመሰል ስለፈለግሁ አብረውኝ ከሚማሩት ልጆች አንዷ በጸሎት ወቅት ድምፅ አውጥታ ስትጸልይ ተደብቄ አዳመጥኳት። ጸሎቷን ልትጨርስ ስትል ተንበርክኬ እጸልይ ወደነበረበት ቦታ ቶሎ ብዬ ተመለስኩ። በኋላ ላይ፣ ምን ብላ እንደጸለየች ለልጅቷ በትክክል ስነግራት “የመንፈስ ቅዱስን ነፃ ስጦታ” እንደተቀበልኩ ተሰማት።

ይሁንና በትምህርት ቤቱ እየተማርኩም ብዙ ጥያቄዎች ነበሩኝ። ለምሳሌ ያህል፣ ማቴዎስ 6:9 “አባታችን” እንዲሁም “ስምህ” የሚል ሐሳብ ይዟል። “ኢየሱስ እዚህ ላይ የጠቀሰው አባት ማን ነው?” እንዲሁም “መቀደስ ያለበት የማን ስም ነው?” እያልኩ እጠይቅ ነበር። አስተማሪዎቼ የሚሰጡኝ መልስ ግን በአብዛኛው የተድበሰበሰ ከመሆኑም ሌላ አጥጋቢ አልነበረም። ስለ ሥላሴ ትምህርት የሚያነሱልኝ ሲሆን ይህ ትምህርት ምስጢራዊ እንደሆነ ይገልጹ ነበር። ሐሳቡ ግራ የሚያጋባ ቢሆንብኝም ፓስተር ለመሆን የጀመርኩትን ትምህርት መከታተሌን አላቆምኩም።

ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ሰማሁ

የይሖዋ ምሥክሮች እምነት ከሁሉም የሐሰት ሃይማኖቶች የከፋ እንደሆነ በትምህርት ቤቱ ውስጥ እንማር ነበር። እንዲሁም ፀረ ክርስቶስ እንደሆኑ ይነገረን ነበር። በመሆኑም ለዚህ ሃይማኖት ከፍተኛ ጥላቻ አደረብኝ።

የሁለተኛ ዓመት ተማሪ እያለሁ ትምህርት ቤት ሲዘጋ ወላጆቼን ለመጠየቅ ወደ ቤት ሄድኩ። ካርመን የተባለችው ታላቅ እህቴ ይህን ስትሰማ ወደ ቤት መጣች። ካርመን የተጠመቀች የይሖዋ ምሥክር ስትሆን አምላክን በሙሉ ጊዜዋ ታገለግል ነበር። ካርመን ስለ አምላክ ልታስተምረኝ ስትሞክር “እኔ የማገለግለውን አምላክ አውቀዋለሁ!” በማለት በቁጣ አንባረቅኩባት። ልክ ልኳን ነግሬ ያባረርኳት ሲሆን ከዚያ በኋላም እንዳታነጋግረኝ ፊት ነሳኋት።

ወደ ትምህርት ቤቱ ከተመለስኩ በኋላ ካርመን በሥላሴ ማመን ይገባሃልን? * የሚለውን ብሮሹር ላከችልኝ። ወዲያውኑ ብሮሹሩን ጭምድድድ አድርጌ እሳት ውስጥ ወረወርኩት። ንዴቴ ገና አልበረደልኝም ነበር።

ፓስተር መሆን

ፓስተር ሆኜ ስመረቅ

በትምህርት ቤቱ በነበርኩበት ወቅት አንዳንዶች የእኔን እምነት እንዲከተሉ ማድረግ ችዬ ነበር። በተለይ ደግሞ እናቴና ወንድሜ እንደ እኔው የጴንጤቆስጤ እምነት ተከታይ እንዲሆኑ ማድረግ በመቻሌ ኩራት ተሰምቶኝ ነበር።

መጋቢት 1994 ከጴንጤቆስጤ ቤተ ክርስቲያን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ተመረቅሁ። በመግቢያው ላይ እንደጠቀስኩት በወቅቱ አንድ ጎብኚ ወንጌላዊ ተገኝቶ ነበር። ይህ ሰው የመፈወስ ስጦታ እንዳለው ስላመንን ተመራቂዎቹ በሙሉ ከእሱ ጋር ለመሆን ፈልገን ነበር። ከእሱ ጋር መድረኩ ላይ ወጥተን ባንዱ የሚጫወተውን ዜማ በመከተል እንጨፍርና እናጨበጭብ ነበር። ከዚያም ወንጌላዊው የነካቸው በሙሉ “መንፈስ እየጣላቸው” * መውደቅ ጀመሩ። እኔም ወንጌላዊው ሲነካኝ ራሴን ስቼ ወደቅሁ። ስነቃ ፍርሃት ቢያድርብኝም የመፈወስ ኃይል እንዳገኘሁ ስለተሰማኝ ደስ አለኝ።

ከዚያ ብዙም ሳይቆይ፣ ኃይለኛ ትኩሳት የነበራትን አንዲት የታመመች ልጅ ለመፈወስ በዚህ ኃይል ተጠቀምሁ። ለልጅቷ ስጸልይላት ወዲያውኑ ላብ አጠመቃት፤ ከዚያም ትኩሳቱ ለቀቃት። እኔም ለአምላክ የገባሁትን ቃል በመጨረሻ መፈጸም እንደቻልኩ ተሰማኝ። የሚገርመው ግን ውስጤ ባዶ ነበር። አንድ አምላክ ብቻ እንዳለ ባምንም ማንነቱን በትክክል ማወቅ እንዳልቻልኩ ይሰማኝ ነበር። ቤተ ክርስቲያኗ ከምታስተምራቸው ትምህርቶች በአብዛኞቹ ላይ የነበረኝ ጥርጣሬ አእምሮዬን ይበጠብጠኝ ነበር።

ኃይለኛ ትኩሳት የነበራትን አንዲት የታመመች ልጅ ለመፈወስ በዚህ ኃይል ተጠቀምሁ

አመለካከቴን እንድቀይር ያደረጉኝ ነገሮች

ከእነዚህ ሁኔታዎች በኋላ ለይሖዋ ምሥክሮች ያለኝ ጥላቻ ይበልጥ እየተባባሰ መጣ። የይሖዋ ምሥክሮችን ጽሑፎች ሳገኝ አቃጥል ነበር። በዚህ መሃል አንድ ያልታሰበ ሁኔታ ተፈጠረ። እናቴ ከእንግዲህ የእኛን ሃይማኖት መከተል እንደማትፈልግ ሳውቅ በጣም ደነገጥኩ። እናቴ ከካርመን ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀምራ ነበር! በመሆኑም በእህቴ በጣም ተበሳጨሁ።

አንድ ቀን፣ የእናቴ ቤት ውስጥ ንቁ! መጽሔት አገኘሁ። ሌላ ጊዜ ቢሆን ወዲያውኑ አቃጥለው ነበር። ይሁንና እናቴ ስታነበው ስለነበረው ነገር የማወቅ ጉጉት ስላደረብኝ ጽሑፉን ማገላበጥ ጀመርኩ። መጽሔቱን ሳነብ፣ ቤተ ክርስቲያን በምታስተምረው ነገር አጥብቆ ያምን ስለነበረ አንድ ግለሰብ የሚናገር ርዕስ ትኩረቴን ሳበው። ይህ ሰው የይሖዋ ምሥክሮች የሚያዘጋጇቸውን ጽሑፎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እያጣቀሰ ማንበብ ሲጀምር ስለ ሥላሴ፣ ስለ ገሃነመ እሳትና ስለ ነፍስ አለመሞት የሚናገሩት ትምህርቶች በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ የተመሠረቱ እንዳልሆኑ አመነ። ያነበብኩት ነገር ልቤን ነካው። እነዚህ እኔም ለማወቅ የምፈልጋቸው ነገሮች ነበሩ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የመረዳት ጉጉት አደረብኝ።

የአልኮልና የዕፅ ሱሰኛ ስለነበረና መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናቱ በሕይወቱ ውስጥ ትልቅ ለውጥ ስላደረገ አንድ ግለሰብ የሚናገር ሌላ የሕይወት ታሪክ በንቁ! መጽሔት ላይ ካነበብኩ በኋላ ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ጽሑፎችን ማንበብ ጀመርኩ። በዚህ መሃል፣ ለዘላለም ጸንቶ የሚኖረው መለኮታዊው ስም * የሚለውን ብሮሹር አገኘሁ። ይህን ብሮሹር ሳነብ የአምላክ ስም ይሖዋ እንደሆነ አወቅሁ። ብቻውን እውነተኛ ስለሆነው አምላክ እውነቱን ማወቄ በጣም አስደሰተኝ!—ዘዳግም 4:39 NW፤ ኤርምያስ 10:10 NW

ብቻውን እውነተኛ ስለሆነው አምላክ እውነቱን ማወቄ በጣም አስደሰተኝ!

የይሖዋ ምሥክሮችን ጽሑፎች በድብቅ ማንበቤን የቀጠልኩ ሲሆን ሌሎች በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን መረዳት ቻልኩ። ለምሳሌ ያህል፣ በጴንጤቆስጤ ቤተ ክርስቲያን ትምህርት ቤት ውስጥ ኢየሱስ፣ ሁሉን ቻይ አምላክ እንደሆነ ተምሬ ነበር፤ አሁን ግን ኢየሱስ “የሕያው አምላክ ልጅ” እንደሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ ተማርኩ።—ማቴዎስ 16:15, 16

የአመለካከት ለውጥ ማድረግ

ከካርመን ጋር እንደገና ስንገናኝ ለዘላለም ጸንቶ የሚኖረው መለኮታዊው ስም የሚለው ብሮሹርና ሌሎች ጽሑፎች እንዲኖሩኝ እንደምፈልግ ስነግራት ተገረመች። በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤቱ ውስጥ በርካታ ዓመታት ባሳልፍም እውነትን ከመማር ይልቅ ታውሬ ነበር። አሁን ግን ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማርኳቸው እውነቶች በደስታ እንድፈነድቅ አደረጉኝ። ኢየሱስ “እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነፃ ያወጣችኋል” በማለት የተናገራቸውን ቃላት እውነተኝነት በሕይወቴ ተመለከትሁ። (ዮሐንስ 8:32) እነዚህን እውነቶች በማወቄ ሕይወቴ መለወጥ ጀመረ።

እነዚህን እውነቶች በማወቄ ሕይወቴ መለወጥ ጀመረ

መጀመሪያ ላይ፣ ይሖዋ አምላክን በድብቅ እያመለክሁ ፓስተር ሆኜ መቀጠል እንደምችል ተሰምቶኝ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ግን ቤተ ክርስቲያኗ ከምትከተላቸው ትምህርቶች አብዛኞቹን ማስተማር ከበደኝ። ያም ቢሆን ‘ፓስተር መሆኔን ካቆምኩ በምን እተዳደራለሁ?’ ብዬ እሰጋ ነበር። በዚያ ላይ ደግሞ አንድ ፓስተር፣ የይሖዋ ምሥክር መሆኑ ለቤተ ክርስቲያኗ ምን ያህል አሳፋሪ ሊሆን እንደሚችል አስቡት! በመሆኑም ፓስተር ሆኜ ማስተማሬን ቀጠልኩ፤ ሆኖም የቤተ ክርስቲያኗን የተሳሳቱ ትምህርቶች አላስተምርም ነበር።

ፕሬሽየስ መጽሐፍ ቅዱስን ስታስጠናኝ

ከካርመን ጋር እንደገና ስንገናኝ በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ እንድገኝ ሐሳብ አቀረበችልኝ። በላዋግ ሲቲ ወደሚገኘው ዋናው ቤተ ክርስቲያን አንዳንድ ጊዜ እሄድ ስለነበር በዚያ ከተማ ወዳለው የይሖዋ ምሥክሮች መሰብሰቢያ ይኸውም የመንግሥት አዳራሽ በድብቅ መሄድ ጀመርኩ። በዚያም አልማ ፕሬስዮሳ ቪልያሪን ከተባለችና “ፕሬሽየስ” የሚል ቅጽል ስም ካላት አምላክን በሙሉ ጊዜዋ የምታገለግል የይሖዋ ምሥክር ጋር ተዋወቅሁ። ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ጥሩ አመለካከት ባይኖረኝም መጽሐፍ ቅዱስን ከእሷ ጋር ለማጥናት ተስማማሁ።

እህቴ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለእኔ በምታካፍልበት ጊዜ ከፍተኛ ትዕግሥት አሳይታለች። ፕሬሽየስም ልክ እንደ እሷ በጣም ታጋሽ ነበረች። በቤተ ክርስቲያኑ የተማርኳቸው ነገሮች ትክክል እንዳልሆኑ ላለመቀበል ስል ፕሬሽየስን በቁጣ እናገራት፣ እከራከራት አልፎ ተርፎም አንዳንድ ጊዜ እጮኽባት የነበረ ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስን መረዳት እንድችል ከፍተኛ እገዛ አድርጋልኛለች። ፕሬሽየስም ሆነች ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ያሳዩኝ አሳቢነት፣ ትሕትናና የገርነት መንፈስ ልቤን ነካው። እነዚህ ነገሮች ይሖዋን ለማምለክ እንድነሳሳ አደረጉኝ።

አምላክን ማስደሰት ከፈለግሁ ፓስተር ሆኜ ማገልገሌን ማቆም እንዳለብኝ ሐምሌ 1995 ተገነዘብኩ። እንዲህ ዓይነት ድምዳሜ ላይ እንድደርስ ያደረገኝ ምንድን ነው? ራእይ 18:4 ስለ ሐሰት ሃይማኖት በምሳሌያዊ መንገድ የሚናገር ሲሆን “ሕዝቤ ሆይ፣ የኃጢአቷ ተባባሪ መሆን የማትፈልጉና የሚደርስባት መቅሰፍት ተካፋይ መሆን የማትፈልጉ ከሆነ ከእሷ ውጡ” ይላል። ታዲያ ፓስተር ሆኜ ማገልገሌን ካቆምኩ በምን ልተዳደር ነው? የአምላክን ፈቃድ ካደረግን እሱ “ፈጽሞ አልተውህም፣ በምንም ዓይነት አልጥልህም” በማለት ቃል እንደገባልን ዕብራውያን 13:5 ላይ ከሚገኘው ሐሳብ መገንዘብ ቻልኩ።

እኔና እናቴ በተጠመቅንበት ቀን

በዚህ ወቅት አባቴና ወንድሜ በጥብቅ ቢቃወሙኝም ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ከመሆኔ ከሁለት ሳምንት በፊት እንደምንም ራሴን አደፋፍሬ ወደ ቤት በመሄድ ፓስተር ሆኜ ሳገለግል እጠቀምባቸው የነበሩ ነገሮችን በሙሉ አቃጠልኩ። ይህን ካደረግሁ በኋላ ቀደም ሲል ተሰጥቶኝ የነበረው ልዩ ኃይል እንደተለየኝ ተገነዘብኩ። ከዚያ ቀደም በምተኛበት ወቅት፣ ሁልጊዜ አንድ ነገር ሲጫነኝ ይሰማኝ ነበር። አሁን ግን ይህ ስሜት ለቀቀኝ። በክፍሌ መስኮት ላይ የማያቸው ጥላ የሚመስሉ ነገሮችም ከዚያ በኋላ አልታዩኝም። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቴ የመፈወስ ኃይልን የመሳሰሉ በዛሬው ጊዜ አሉ የሚባሉ የመንፈስ ስጦታዎች ከአምላክ ሳይሆን ከክፉ መናፍስት የመጡ እንደሆኑ እንድገነዘብ አስችሎኛል። ጳውሎስ ‘ከጥንቆላ ጋኔን’ እንዳላቀቃት አገልጋይ ሁሉ እኔም ከአጋንንት ተጽዕኖ ነፃ በመውጣቴ በጣም ደስተኛ ነኝ።—የሐዋርያት ሥራ 16:16-18

አምላክን በሙሉ ጊዜዬ ማገልገል ጀመርኩ

መስከረም 1996 እኔና እናቴ አንድ ላይ ተጠምቀን የይሖዋ ምሥክሮች ስንሆን የተሰማንን ታላቅ ደስታ መገመት ትችላላችሁ! ከተጠመቅሁ በኋላ አምላክን በሙሉ ጊዜዬ ማገልገል የጀመርኩ ሲሆን ለበርካታ ዓመታት በዚህ አገልግሎት ተካፍያለሁ።

በአሁኑ ወቅት ትዳር መሥርቻለሁ። እኔና ባለቤቴ ሲልቨር የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ለልጃችን ለማስተማር በጋራ ጥረት እያደረግን ነው። አንዳንድ እህቶቼም አብረውን ይሖዋን ያገለግላሉ። አምላክን በትክክል ሳላውቀው በርካታ ዓመታት ማሳለፌ ቢቆጨኝም የማመልከውን አምላክ ማወቅ ስለቻልኩ በጣም ደስተኛ ነኝ።

ከባለቤቴ፣ ከልጃችን እንዲሁም በእውነተኛው አምልኮ አብረውን ከሚካፈሉ ከብዙዎቹ የቤተሰባችን አባላት ጋር

^ አን.10 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ፤ አሁን መታተም አቁሟል።

^ አን.13 በአንዳንድ ሃይማኖቶች ውስጥ አማኞች “መንፈስ” በኃይል ሲወርድባቸው መሬት ላይ እንደሚወድቁ ይታመናል፤ እንዲህ ያለውን ሁኔታ ለመግለጽ “መንፈስ ጣለው” የሚለውን አገላለጽ ይጠቀማሉ።

^ አን.18 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።