በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?

የእንጀራ ልጆች ባሉበት ቤተሰብ ውስጥ ከሌሎች ጋር ጥሩ ግንኙነት መመሥረት

የእንጀራ ልጆች ባሉበት ቤተሰብ ውስጥ ከሌሎች ጋር ጥሩ ግንኙነት መመሥረት

ማርጋሬት፣ * በአውስትራሊያ የምትኖር የእንጀራ እናት፦ “የባለቤቴ የቀድሞ ሚስት ልጆቹ እኔን እንዳይታዘዙኝ ትነግራቸዋለች፤ ‘ጥርሳችሁን ቦርሹ’ እንደሚሉ ያሉ ቀላል ትእዛዞችን እንኳ እሺ እንዳይሉ ትመክራቸዋለች።” ማርጋሬት፣ የቤተሰቡ ግንኙነት እንዲሻክር በሚደረገው እንዲህ ያለ ጥረት ምክንያት ትዳሯ ችግር ውስጥ እንደገባ ይሰማታል።

የእንጀራ ልጆች ባሉበት ቤተሰብ ውስጥ፣ አብዛኛውን ጊዜ ተፈታታኝ የሆኑ ችግሮች መከሰታቸው አይቀርም። * አብዛኞቹ የእንጀራ ወላጆች፣ ልጆቹ ከወላጃቸው ጋር የሚገናኙበትን ጊዜ፣ ተግሣጽ መስጠትን፣ የገንዘብ ድጋፍ ማድረግንና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በተመለከተ ከልጆቹ ወላጅ ጋር መነጋገር የሚጠይቅ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል። የቤተሰቡ ወዳጅ ዘመዶችም ከአዲሶቹ የቤተሰቡ አባላት ጋር መላመድ ይከብዳቸው ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ምክር የእንጀራ ልጆች ያሏቸው ቤተሰቦችን ሊጠቅም የሚችለው እንዴት እንደሆነ እንመልከት።

ዝምድና 1፦ የልጁ ሌላኛው ወላጅ

በናሚቢያ የምትኖር ጁዲት የተባለች የእንጀራ እናት እንዲህ ብላለች፦ “የእንጀራ ልጆቼ እናት፣ እኔ የአባታቸው ሚስት እንጂ እናታቸው ልሆን እንደማልችል እንዲሁም እኔና ባለቤቴ የምንወልዳቸው ልጆች ከእነሱ ጋር ምንም ዝምድና እንደሌላቸው ነግራቸው ነበር። የእንጀራ ልጆቼን እንደራሴ ልጆች አድርጌ እወዳቸው ስለነበር የተናገረችው ነገር በጣም ጎዳኝ።”

የእንጀራ ወላጅ ከልጆቹ ወላጅ ጋር ያለው ግንኙነት በቤተሰቡ ውስጥ ክፍፍል ሊፈጥርና ነገሮችን ሊያከብድ እንደሚችል  አንዳንድ ባለሙያዎች ይናገራሉ። አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ዓይነት ችግር የሚያጋጥመው በእንጀራ እናት እና በልጆቹ እናት መካከል ነው። ታዲያ ምን ማድረግ ይቻላል?

ቁልፉ፦ ምክንያታዊ የሆነ ገደብ አብጁ። ልጅህ * ከቀድሞ የትዳር ጓደኛህ ጋር ሙሉ በሙሉ እንዳይገናኝ ጥረት የምታደርግ ከሆነ ስሜቱ ሊጎዳ ይችላል። * ለአንድ ልጅ፣ ‘የወለዱት’ ወላጆቹ በሕይወቱ ውስጥ ትልቅ ቦታ እንደሚኖራቸው ጥርጥር የለውም። (ምሳሌ 23:22, 25) በሌላ በኩል ደግሞ የቀድሞ የትዳር ጓደኛህ በቤትህ ውስጥ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንድታሳድር የምትፈቅድ ከሆነ አዲሷ የትዳር ጓደኛህ ተስፋ ልትቆርጥ ወይም ልትናደድ ትችላለች። በተቻለ መጠን ከቀድሞ ባለቤትህ ጋር ለመተባበር ጥረት ማድረግ ቢኖርብህም ትዳርህን ለመጠበቅ ስትል ምክንያታዊ ገደቦችን በማበጀት ሚዛናዊ መሆን አለብህ።

ለወላጆች የቀረበ ጠቃሚ ምክር

  • ከቀድሞ የትዳር ጓደኛህ ጋር ስትገናኝ በተቻለ መጠን ከልጆቻችሁ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ለማድረግ እንጂ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ላለመወያየት ጥረት አድርግ። ለምሳሌ ያህል፣ ከቀድሞ ባለቤትህ ጋር በስልክ መነጋገር ካለባችሁ አንድ የተወሰነ ሰዓት ላይ ብቻ እንድትደውል በዘዴ ልትጠይቃት ትችላለህ። ይህ ደግሞ የቀድሞ ባለቤትህ በፈለገችው ጊዜ ወይም ከመሸ በኋላ እንዳትደውል ያደርጋታል።

  • እናት ከሆንሽና ልጆችሽ የሚኖሩት ከአባታቸው ጋር ከሆነ ስልክ በመደወል፣ ደብዳቤ በመጻፍ፣ የስልክ ወይም የኢ-ሜይል መልእክት በመላክ ከልጆችሽ ጋር ያለሽ ግንኙነት እንዳይቋረጥ ማድረግ ትችያለሽ። (ዘዳግም 6:6, 7) እንዲያውም አንዳንዶች በኢንተርኔት ቪዲዮ ከልጆቻቸው ጋር እየተያዩ ይነጋገራሉ። እንዲህ በማድረግ ልጆችሽ ስለሚያስፈልጓቸውና ስለሚያጋጥሟቸው ነገሮች መረዳት እንዲሁም ጥሩ ምክር መስጠት ትችያለሽ፤ በዚህ ረገድ የምታደርጊው ጥረት ከምታስቢው በላይ ሊሳካልሽ ይችላል።

ለእንጀራ እናቶች የቀረበ ጠቃሚ ምክር

  • የልጆቹን እናት ቦታ መንጠቅ እንደማትፈልጊ በማሳየት የእሷን ስሜት ‘ለመረዳት’ ሞክሪ። (1 ጴጥሮስ 3:8) ስለ ልጆቹ እንቅስቃሴ እንድታውቅ አድርጊ፤ ብዙውን ጊዜ የልጆቹን ጥሩ ጎን ብትነግሪያት የተሻለ ነው። (ምሳሌ 16:24) አስፈላጊ ከሆነ ምክር ጠይቂያት፤ እንዲሁም ለምታደርገው ትብብር አመስግኚያት።

  • እናታቸው ባለችበት እሷን የሚያስቀኑ የፍቅር መግለጫዎችን ለልጆቹ ከማሳየት ተቆጠቢ። ቤቨርሊ የተባለች በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖር አንዲት እንጀራ እናት እንዲህ ብላለች፦ “ትናንሾቹ የእንጀራ ልጆቼ እኔን ‘እማዬ’ ብለው መጥራት እንደሚፈልጉ ነገሩኝ። ቤት ውስጥ እንዲህ ብለው ሊጠሩኝ እንደሚችሉ ሆኖም ከእናታቸው ከጄን ወይም ከእሷ ቤተሰቦች ጋር ሲሆኑ በዚህ መንገድ እንዳይጠሩኝ ተስማማን። ከዚያ በኋላ እኔና ጄን ይበልጥ መግባባት ጀመርን። እንዲያውም የትምህርት ቤት ጨዋታ ወይም ሽርሽር ሲኖር ከጄን ጋር ሆነን ልጆቹን እናዘጋጃቸዋለን።”

በልጆቻችሁ ላይ በጎ ተጽዕኖ ለማሳደር የምታደርጉት ጥረት ከምታስቡት በላይ ሊሳካላችሁ ይችላል

ወላጆችና የእንጀራ ወላጆች ጥሩ ግንኙነት እንዲኖራቸው የሚረዳ ምክር

    ትሕትናና አክብሮት ሰላም ያሰፍናል

  • በልጆቹ ፊት ስለ ወላጃቸው ወይም ስለ እንጀራ ወላጃቸው ምንም ዓይነት አሉታዊ ነገር አታውሩ። እንዲህ ዓይነት ንግግር ለመናገር በቀላሉ ትፈተኑ ይሆናል፤ ሆኖም በንግግራችሁ የልጆቹ ስሜት ክፉኛ ሊጎዳ ይችላል። በተጨማሪም የተናገራችሁት ነገር መቼ እና እንዴት ወደ ሌሎች ጆሮ ሊደርስ እንደሚችል አታውቁም። (መክብብ 10:20) አንድ ልጅ፣ ወላጁ ወይም የእንጀራ ወላጁ ስለ እናንተ መጥፎ ነገር እንደተናገረ ቢነግራችሁ  እንኳ ለልጁ ስሜት ተጠንቀቁ። ምናልባትም እንዲህ ያለ መልስ መስጠት ትችሉ ይሆናል፦ “እናትህ እንዲህ ብላ ስትናገር በመስማትህ አዝኛለሁ፤ እናትህ ተናዳብኝ ነበር፤ ሰዎች ደግሞ ሲናደዱ መጥፎ ነገር ሊናገሩ ይችላሉ።”

  • በሁለታችሁም ቤት ውስጥ ተመሳሳይ ደንብና የተግሣጽ አሰጣጥ እንዲኖር አድርጉ። እንዲህ ማድረግ ካልተቻለ ይህ የሆነበትን ምክንያት ለልጆቹ አስረዷቸው፤ ይህን ስታደርጉ ወላጁን የሚያጥላላ ነገር ከመናገር ተቆጠቡ። እስቲ የሚከተለውን ሁኔታ እንመልከት፦

    የእንጀራ እናት፦ ዮናስ፣ እባክህ የቀየርካቸውን ልብሶች አጣጥፈህ አስቀምጥ።

    ዮናስ፦ እማዬ ጋር ስሄድ እኮ እሷ ራሷ ናት የምታጣጥፍልኝ።

    የእንጀራ እናት (በንዴት)፦ የጠቀመችህ መስሎሃል፤ ስንፍና እያስተማረችህ እኮ ነው።

    ከዚህ የተሻለ መልስ መስጠት ትችሉ ይሆን?

    የእንጀራ እናት (በእርጋታ)፦ ሊሆን ይችላል፤ እዚህ ግን እያንዳንዱ ሰው የራሱን ልብስ ማጣጠፍ አለበት።

  • ልጆቹ ከወላጃቸው ጋር ለመገናኘት ቀጠሮ በያዙበት ወቅት ላይ ሌሎች እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ ፕሮግራም አታውጡ። (ማቴዎስ 7:12) መለወጥ የማይቻል ፕሮግራም ካጋጠማችሁ ግን ስለ ዝግጅቱ ለልጆቹ ከማሳወቃችሁ በፊት የሌላውን ወላጅ ፈቃድ ጠይቁ።

እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ የቀድሞ ባለቤትሽን የትዳር ጓደኛ ወይም የባለቤትሽን የቀድሞ ሚስት ስታገኚ እነዚህን እርምጃዎች ለመውሰድ ሞክሪ፦

  1. ዓይን ዓይኗን እያየሽ በፈገግታ ቅረቢያት። እንደተሰላቸሽ የሚያሳይ ነገር እንዳታደርጊ ወይም ፊትሽ ላይ እንዳይነበብ ተጠንቀቂ።

  2. በስሟ ጠርተሽ ሰላምታ ስጪያት። ለምሳሌ፣ “እንዴት ነሽ ትዕግሥት?” ማለት ትችያለሽ።

  3. ሌሎች ሰዎች አብረዋችሁ ካሉ እሷም በጭውውቱ እንድትሳተፍ አድርጊ።

ዝምድና 2፦ ያደጉ የእንጀራ ልጆች

አንዲት ሴት ባለቤቷ ለትላልቅ ልጆቹ እንደሚያዳላና ልጆቹም በደግነት እንደማይዟት ለባለቤቷ ስትነግረው እንደማይሰማት በምሬት መናገሯን ስቴፕ ዋርስ የተባለው መጽሐፍ ገልጿል። ይህች ሴት “ባለቤቴ እንዲህ ሲያደርግ ውስጤ ቅጥል ይላል” ብላለች። ታዲያ ከትላልቅ የእንጀራ ልጆችሽ ጋር ጥሩ ግንኙነት በመመሥረት ትዳርሽን መታደግ የምትችዪው እንዴት ነው?

ቁልፉ፦ የሌሎችን ስሜት የምትረጂ ሁኚ። መጽሐፍ ቅዱስ “እያንዳንዱ ሰው ዘወትር የራሱን ጥቅም ሳይሆን የሌላውን ሰው ጥቅም ይፈልግ” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 10:24) የሌላውን ሰው ስሜት ለመረዳት እና ራስሽን በእነሱ ቦታ ለማስቀመጥ ጥረት አድርጊ። የእንጀራ ልጆችሽ ቢያድጉም የአባታቸውን ፍቅር እንደሚያጡ ሊሰጉ ይችላሉ። ወይም ደግሞ ከእንጀራ እናታቸው ጋር ጥሩ ግንኙነት ቢኖራቸው ለእናታቸው ያላቸውን ታማኝነት እንዳጓደሉ ሊሰማቸው ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ባለቤትሽ፣ ልጆቹን ከተናገራቸው እንደሚርቁት ይሰማው ይሆናል።

ከእንጀራ ልጆችሽ ጋር በአንድ ጊዜ ጥሩ ግንኙነት እንዲኖራችሁ ከመጠበቅ ይልቅ በመካከላችሁ ያለው ዝምድና ቀስ እያለ እንዲያድግ ጥረት አድርጊ። በጥቅሉ ሲታይ አንድ ሰው እንዲወደን ለማስገደድ ወይም ለመጫን መሞከር ጥበብ አይደለም። (ማሕልየ መሓልይ 8:4) በመሆኑም ከእንጀራ ልጆችሽ ጋር ባለሽ ግንኙነት ረገድ የምትጠብቂው ነገር ምክንያታዊ ይሁን።

ተገቢ ያልሆነ ነገር ተደርጎብሽ ቢሆን እንኳ የተሰማሽን ወይም ወደ አእምሮሽ የመጣውን ሁሉ አትናገሪ። (ምሳሌ 29:11) በተለይ አንደበትሽን መቆጣጠር ከባድ ሲሆንብሽ የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊት “እግዚአብሔር ሆይ፤ ለአፌ ጠባቂ አድርግ፤ የከንፈሮቼንም መዝጊያ ጠብቅ” በማለት ያቀረበው ዓይነት ጸሎት መጸለይሽ ሊጠቅምሽ ይችላል።—መዝሙር 141:3

ልጆቹ ባደጉበት ቤት ለመኖር ከወሰናችሁ ልጆቹ ከቤቱ ጋር በተያያዘ ብዙ ትዝታ እንዳላቸው አትርሺ። ስለዚህ በቤቱ ውስጥ፣  በተለይም በልጆቹ ክፍሎች ውስጥ ትልቅ ለውጥ ለማድረግ አትሞክሪ። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሌላ ቤት መቀየር የተሻለ ሊሆን ይችላል።

እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ ትላልቅ የእንጀራ ልጆችሽ በጣም ካስቸገሩሽ ወይም ለአንቺ አክብሮት ከሌላቸው ስሜትሽን ለባለቤትሽ ንገሪው፤ እንዲሁም ባለቤትሽ ሐሳቡን ሲገልጽ በደንብ አዳምጪው። ልጆቹን እንዲቀጣቸውም አትጫኚው። ከዚህ ይልቅ ከባለቤትሽ ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖራችሁ ጥረት አድርጊ። አንቺና ባለቤትሽ ስለ ጉዳዩ ‘በሐሳብ መስማማት’ ከቻላችሁ ሁኔታውን ለማሻሻል አብራችሁ መሥራት ትችላላችሁ።—2 ቆሮንቶስ 13:11

በቤተሰቡ ውስጥ ላሉ ለሁሉም ልጆች ፍቅር ለማሳየት ጥረት አድርጉ

ዝምድና 3፦ ወዳጅ ዘመዶች

ሜሪየን የተባለች በካናዳ የምትኖር አንዲት የእንጀራ እናት እንዲህ ብላለች፦ “ወላጆቼ ብዙ ጊዜ ለልጄ ስጦታ የሚሰጡት ሲሆን ለባለቤቴ ልጆች ግን ይህን አያደርጉም። እኛም ለልጆቹ ስጦታ በመስጠት እንዳይሰማቸው ለማድረግ እንሞክራለን፤ ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ለማድረግ አቅማችን አይፈቅድም።”

ቁልፉ፦ ለአዲሱ ቤተሰብሽ ቅድሚያ ስጪ። ለአዲሱ ቤተሰብሽ ትኩረት የመስጠት ኃላፊነት እንዳለብሽ ለዘመዶችሽ እና ለጓደኞችሽ ንገሪያቸው። (1 ጢሞቴዎስ 5:8) ዘመዶችሽ ወይም ጓደኞችሽ አዲሶቹን የቤተሰብሽን አባላት በአንድ ጊዜ እንዲወዷቸው መጠበቅ ባይኖርብሽም አክብሮት እንዲያሳዩዋቸው እንዲሁም መድልዎ እንዳይፈጽሙባቸው ንገሪያቸው። ለእንጀራ ልጆችሽ ትኩረት ካልሰጧቸው ወይም በደግነት ካልያዟቸው ስሜታቸው ሊጎዳ እንደሚችል አስረጂያቸው።

የቀድሞ ባለቤትሽ ወላጆች ከልጆችሽ ጋር ያላቸው ግንኙነት እንዲቀጥል አድርጊ። ሱዛን የተባለች በእንግሊዝ የምትኖር አንዲት እናት እንዲህ ብላለች፦ “ባለቤቴ ከሞተ ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ እንደገና አገባሁ፤ የቀድሞ ባለቤቴ ወላጆች አዲሱን የትዳር ጓደኛዬን መቀበል ከብዷቸው ነበር። ከእነሱ ጋር ይበልጥ ጊዜ ማሳለፋችን፣ ልጆቹ ስልክ እንዲደውሉላቸው ማድረጋችንና ለሚያደርጉልን ነገር ማመስገናችን ሁኔታዎች እየተሻሻሉ እንዲሄዱ አድርገዋል።”

እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ ከወዳጅ ዘመዶቻችሁ መካከል ጥሩ ግንኙነት የሌላችሁ ከማን ጋር እንደሆነ ለማሰብ ሞክሩ፤ ከዚያም ሁኔታውን ለማሻሻል ምን ማድረግ እንደምትችሉ ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ተወያዩ።

ቤተሰባችሁ የእንጀራ ልጆች ያሉበት ከሆነ የሚከሰቱት ችግሮች ተፈታታኝ ሊሆኑባችሁ ይችላሉ። የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት አድርጉ፤ እንዲህ የምታደርጉ ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስ “ቤት በጥበብ ይሠራል፤ በማስተዋልም ይጸናል” ሲል የተናገረው ሐሳብ ለእናንተም ቤተሰብ ይሠራል።—ምሳሌ 24:3

^ አን.3 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.4 ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሙ ሌሎች ተፈታታኝ ሁኔታዎችን እንዴት መወጣት እንደሚቻል ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች በተዘጋጀው የሚያዝያ 2012 ንቁ! መጽሔት ላይ “የእንጀራ ልጆችን ማሳደግ—ስኬታማ መሆን የሚቻለው እንዴት ነው?” የሚለውን ተከታታይ ርዕስ ተመልከት።

^ አን.8 እርግጥ ነው፣ የቀድሞ የትዳር ጓደኛህ በልጆቹ ላይ ጥቃት የምትፈጽም ወይም የልጆችህ ደኅንነት አደጋ ላይ እንዲወድቅ የምታደርግ ከሆነ ለቤተሰቡ ደኅንነት ሲባል ጥብቅ የሆኑ ገደቦችን ማውጣት ሊያስፈልግ ይችላል።

^ አን.8 ለአጻጻፍ እንዲያመች ሲባል በዚህ ርዕስ ውስጥ የእንጀራ ወላጅ ስላለበት ቤተሰብ ስንናገር የእንጀራ እናትን የምንጠቅስ ቢሆንም የቀረቡት ነጥቦች የእንጀራ አባት ላለበት ቤተሰብም ይሠራሉ።

ራሳችሁን እንዲህ እያላችሁ ጠይቁ፦

  • ከባለቤቴ የቀድሞ የትዳር ጓደኛ ጋር ያለኝን ግንኙነት ማሻሻል የምችለው እንዴት ነው?

  • ዘመዶቻችንና ጓደኞቻችን ባለማወቅ እንኳ ቤተሰባችንን እንዳይጎዱ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?