በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው

ብዙ ሰዎች ፈጣሪ መኖሩን እንዲያምኑ ያደረጋቸው ምንድን ነው?

ሕይወት በራሱ ተአምር ነው

ከ3,000 ዓመታት በፊት አንድ ገጣሚ “ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁ” በማለት ጽፎ ነበር። (መዝሙር 139:14) አንድ ሕፃን በእናቱ ማሕፀን ውስጥ ከአንዲት ቅንጣት ሴል ተነስቶ እድገት የሚያደርግበትን መንገድ ስታስብ አትደነቅም? ብዙ ሰዎች፣ ሕይወት ያላቸው ነገሮች እንዲገኙ ያደረገው ፈጣሪ እንደሆነ ያምናሉ።መዝሙር 139:13-17ን እና ዕብራውያን 3:4ን አንብብ።

አጽናፈ ዓለምን የፈጠረውና ምድርን ለመኖሪያነት ምቹ አድርጎ ያዘጋጀው አካል ሕይወት ያላቸው ነገሮችንም ፈጥሯል። (መዝሙር 36:9) ከዚህም በተጨማሪ ፈጣሪ ለሰው ልጆች ስለ ራሱ ተናግሯል።ኢሳይያስ 45:18ን አንብብ።

ሰዎች የመጡት ከእንስሳት ነው?

አካላችን በብዙ መንገድ ከእንስሳት አካል ጋር ይመሳሰላል። ይህ የሆነው ግን ፈጣሪ ሰዎችንም ሆነ እንስሳትን የፈጠረው በምድር ላይ እንዲኖሩ አስቦ ስለሆነ ነው። ፈጣሪ የመጀመሪያውን ሰው የፈጠረው ከእንስሳ ሳይሆን ከአፈር ነው።ዘፍጥረት 1:24ን እና 2:7ን አንብብ።

ሰዎች ከእንስሳት የሚለዩባቸው ሁለት ዋና ዋና መንገዶች አሉ። አንደኛ፣ ሰዎች ፈጣሪያቸውን የማወቅ፣ የመውደድና የማክበር ችሎታ አላቸው። ሁለተኛው ደግሞ ሰዎች የተፈጠሩት ለዘላለም እንዲኖሩ ሲሆን እንስሳት የተፈጠሩት ግን ለዘላለም እንዲኖሩ አይደለም። አሁን ግን ሁሉም ሰዎች ይሞታሉ፤ ምክንያቱም ሁሉም የተገኙት የፈጣሪን መመሪያ ለመቀበል እምቢተኛ ከሆነው ከመጀመሪያው ሰው ነው።ዘፍጥረት 1:27ን እና 2:15-17ን አንብብ።