በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

ሦስት ጥያቄዎች ሕይወቴን ለወጡት

ሦስት ጥያቄዎች ሕይወቴን ለወጡት
  • የትውልድ ዘመን:1949

  • የትውልድ አገር: ዩናይትድ ስቴትስ

  • የኋላ ታሪክ: የሕይወትን ትርጉም ለማወቅ ትፈልግ የነበረች

የቀድሞ ሕይወቴ፦ ያደግሁት በሰሜናዊ ኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በምትገኝ አንክረም በተባለች አነስተኛ ከተማ ውስጥ ነው። አንክረም በአብዛኛው የወተት ተዋጽኦዎች የሚመረቱባት ከተማ ነበረች። እንዲያውም ከሰዉ ይልቅ የላሞቹ ቁጥር ይበልጥ ነበር።

 

ቤተሰቦቼ በከተማዋ ውስጥ ወደነበረው ብቸኛ ቤተ ክርስቲያን ይሄዱ ነበር። ሁልጊዜ እሁድ ጠዋት፣ አያቴ ጫማዬን ከወለወለልኝ በኋላ ሴት አያቴ የሰጠችኝን ነጭ መጽሐፍ ቅዱስ ይዤ ወደ ሰንበት ትምህርት ቤት እሄድ ነበር። እኔ፣ ወንድሜና እህቴ ጠንክረን እንድንሠራ፣ ጎረቤቶቻችንን እንድናከብርና እንድንረዳ እንዲሁም ላገኘናቸው በረከቶች አመስጋኝ እንድንሆን ተምረን ነበር።

ካደግሁ በኋላ ከቤት የወጣሁ ሲሆን መምህር ሆኜ መሥራት ጀመርኩ። ስለ አምላክና ስለ ሕይወት ብዙ ጥያቄዎች ነበሩኝ። አንዳንዶቹ ተማሪዎቼ ጥሩ ተሰጥኦ ያላቸው ነበሩ። ሌሎቹ ደግሞ ተሰጥኦ ባይኖራቸውም በጣም ጠንክረው ይሠሩ ነበር። አንዳንዶቹ የአካል ጉዳተኞች ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ ጥሩ የአካል ብቃት ነበራቸው። ይህ ሁኔታ ፍትሕ የጎደለው እንደሆነ ይሰማኝ ነበር። እንደ ሌሎቹ ልጆች በአካልም ሆነ በአእምሮ ችሎታ የሌላቸው ተማሪዎቼ ወላጆች “ልጄ እንዲህ የሆነው የአምላክ ፈቃድ ስለሆነ ነው” እንደሚለው ያሉ ሐሳቦችን የሚሰነዝሩበት ጊዜ ነበር። ‘አምላክ፣ አንዳንድ ሕፃናት የአካል ጉድለት ኖሯቸው እንዲወለዱ የሚያደርገው ለምንድን ነው?’ የሚለው ጉዳይ ያሳስበኝ ጀመር። በዚያ ላይ ደግሞ ሕፃናቱ ምንም የሠሩት ስህተት የለም።

በተጨማሪም ‘በሕይወቴ ላከናውነው የሚገባው ትርጉም ያለው ሥራ ምንድን ነው?’ እያልኩ አስብ ነበር። ዕድሜዬ በፍጥነት እየሄደ እንደሆነ ይሰማኝ ነበር። እርግጥ ነው፣ ያደግሁት ጥሩ ቤተሰብ ውስጥ ነው፤ ጥሩ ትምህርት ቤት ገብቼ ተምሬያለሁ፤ የምወደው ሥራም አግኝቻለሁ። ቢሆንም ቀሪውን ሕይወቴን ሳስብ ባዶ እንደሆነ ይሰማኝ ነበር። ተሳካልኝ ብል እንኳ ከዚያ በኋላ የነበረኝ ተስፋ ትዳር መያዝ፣ ጥሩ ቤት መሥራት፣ ልጆች መውለድ፣ ጡረታ እስከምወጣ ድረስ መሥራቴን መቀጠልና ከዚያም በመጨረሻ አርጅቼ ወደ አረጋውያን መጦሪያ ተቋም መግባት ነው። በመሆኑም ‘ሕይወት ማለት ይሄ ብቻ ነው?’ የሚለው ነገር አሳሰበኝ።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው?

አንድ የበጋ ወቅት ላይ ከሥራ ባልደረቦቼ ጋር አውሮፓን ለመጎብኘት ሄድኩ። በጉብኝታችን ወቅት እንደ ዌስትሚኒስተር አቢ፣ ኖትር ዴም ዴ ፓሪስ እና ቫቲካን ወዳሉት እንዲሁም ወደ ሌሎች ትናንሽ አብያተ ክርስቲያናት ሄደን ነበር። በሄድኩበት ሁሉ ጥያቄዎቼን አቀርብ ነበር። ስሎትስበርግ፣ ኒው ዮርክ ወዳለው ቤቴ ከተመለስኩ በኋላም ወደ በርካታ አብያተ ክርስቲያናት ሄጃለሁ። ነገር ግን አንዳቸውም ቢሆኑ አጥጋቢ መልስ ሊሰጡኝ አልቻሉም።

አንድ ቀን፣ የ12 ዓመት ልጅ የሆነች ተማሪዬ ወደ እኔ መጥታ ሦስት ጥያቄዎችን ጠየቀችኝ። አንደኛ፣ የይሖዋ ምሥክር መሆኗን አውቅ እንደሆነ ጠየቀችኝ። እኔም ‘አዎ’ አልኳት። ሁለተኛ፣ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ተጨማሪ ነገር ማወቅ እፈልግ እንደሆነ ጠየቀችኝ። አሁንም እንደገና ‘አዎ’ አልኳት። ሦስተኛ፣ የምኖረው የት እንደሆነ ጠየቀችኝ። አድራሻዬን ስነግራት ቤቴ ከእነሱ ቤት ብዙም እንደማይርቅ ማወቅ ቻልን። ይህች ትንሽ ልጅ የጠየቀችኝ ሦስት ጥያቄዎች ሕይወቴን ለዘላለም እንደሚለውጡት አላሰብኩም ነበር።

ብዙም ሳይቆይ ብስክሌቷን እየነዳች ወደ ቤቴ መጣችና መጽሐፍ ቅዱስን ታስጠናኝ ጀመር። ለብዙ የሃይማኖት መሪዎች አቅርቤያቸው የነበሩትን ጥያቄዎች ጠየቅኋት። እሷም ከእነሱ በተለየ መልኩ ከራሴ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ግልጽና አጥጋቢ መልስ ሰጠችኝ፤ እነዚህን ሐሳቦች ከዚያ በፊት አይቻቸው አላውቅም ነበር!

ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማርኩት ነገር ደስተኛ እንድሆንና እርካታ እንዳገኝ አደረገኝ። በ1 ዮሐንስ 5:19 ላይ የሚገኘውን “መላው ዓለም ግን በክፉው ቁጥጥር ሥር ነው” የሚለውን ጥቅስ ሳነብ ልቤ ተነካ። በዓለም ላይ ለምናየው አሳዛኝ ነገር ሁሉ መንስኤው አምላክ ሳይሆን ሰይጣን እንደሆነ እንዲሁም አምላክ ለችግሩ ሁሉ መፍትሔ እንደሚያመጣ ሳውቅ እፎይታ ተሰማኝ። (ራእይ 21:3, 4) በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኙት ሐሳቦች በግልጽ ከተብራሩ አሳማኝ እንደሆኑ ተገነዘብኩ። መጽሐፍ ቅዱስን የምታስጠናኝ የይሖዋ ምሥክር ገና የ12 ዓመት ልጅ ብትሆንም እንኳ እውነት በማንኛውም ሰው በኩል ቢነገር እውነትነቱ እንደማይቀየር አምኜ ነበር።

እንደዚያም ሆኖ የይሖዋ ምሥክሮች፣ የሚሰብኩትን ነገር በሕይወታቸው ተግባራዊ ያደርጉ እንደሆነ ማየት ፈለግሁ። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስን የምታስተምረኝ ልጅ፣ እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደ ትዕግሥትና ደግነት ያሉ ባሕርያትን እንደሚያሳዩ አጥብቃ ትናገር ነበር። (ገላትያ 5:22, 23) ስለዚህ እሷ ራሷ እነዚህን ባሕርያት ታሳይ እንደሆነ ልፈትናት ወሰንኩ። አንድ ቀን ለጥናታችን ሆን ብዬ ዘግይቼ ደረስኩ። ‘ትጠብቀኝ ይሆን? ከጠበቀችኝ ደግሞ ዘግይቼ በመድረሴ ትናደድ ይሆን?’ እያልኩ አሰብኩ። ከዚያም ወደ መኪና ማቆሚያዬ አካባቢ ስደርስ ልጅቷ ቤቴ መግቢያ ላይ ስትጠብቀኝ አየኋት። ወደ መኪናዬ ሮጣ መጥታ እንዲህ አለችኝ፦ “እኔኮ ለጥናታችን ዘግይተሽ ስለማታውቂና ደህንነትሽ ስላሳሰበኝ ወደ ቤት ሄጄ እናቴን ‘ወደ ሆስፒታል ወይም ወደ ፖሊስ ደውለን እንጠይቅ’ ልላት ነበር። ‘ምን ሆና ነው’ ብዬ ተጨንቄ ነበር!”

በሌላ ጊዜ ደግሞ ለ12 ዓመት ልጅ በጣም ይከብዳል ብዬ ያሰብኩትን አንድ ጥያቄ ጠየቅኋት። በራሷ ፈጥራ ለመመለስ ትሞክር እንደሆነ ማየት ፈልጌ ነበር። ጥያቄውን ሳቀርብላት ኮስተር ብላ አየችኝና “ይሄ ከባድ ጥያቄ ነው። ጥያቄሽን ልጻፈውና ወላጆቼን እጠይቃለሁ” አለችኝ። ከዚያም በሚቀጥለው ጊዜ ለጥናታችን ስንገናኝ ለጥያቄዬ መልስ የያዘ አንድ የመጠበቂያ ግንብ እትም ይዛ መጣች። በይሖዋ ምሥክሮች እንድሳብ ያደረገኝ ነገር ይኸው ነው፤ ማለትም ለነበሩኝ ጥያቄዎች ሁሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ መልሶችን ከጽሑፎቻቸው ላይ አገኝ ነበር። ከዚህች ትንሽ ልጅ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቴን የቀጠልኩ ሲሆን ከአንድ ዓመት በኋላ ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ። *

ያገኘሁት ጥቅም፦

ለጥያቄዎቼ አጥጋቢ መልሶች ሳገኝ የተማርኩትን ነገር ለሁሉም ሰው ማካፈል ፈለግሁ። (ማቴዎስ 12:35) መጀመሪያ ላይ ቤተሰቦቼ አዲሱን እምነቴን ተቃውመው ነበር። ይሁንና ከጊዜ በኋላ አመለካከታቸው ተለውጧል። እናቴ ከመሞቷ ጥቂት ቀደም ብሎ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀምራ ነበር። ራሷን ለአምላክ ወስና ሳትጠመቅ ሞት ቢቀድማትም ይሖዋን ለማገልገል ወስና እንደነበር እርግጠኛ ነኝ።

በ1978 ኢላያስ ካዛን የሚባል አንድ የይሖዋ ምሥክር አገባሁ። በ1981 እኔና ኢላያስ የዩናይትድ ስቴትስ ቤቴል * ቤተሰብ አባላት እንድንሆን ተጋበዝን። የሚያሳዝነው ግን በቤቴል ለአራት ዓመት ካገለገልን በኋላ ኢላያስ ሞተ። ባለቤቴ ቢሞትም በቤቴል ማገልገሌን የቀጠልኩ ሲሆን ይህም ትኩረቴን የማሳርፍበት ነገር እንዳገኝና እንድጽናና ረድቶኛል።

በ2006 እንደ እኔው የቤቴል ቤተሰብ አባል የሆነውን ሪቻርድ ኤልድረድን አገባሁ። እኔና ሪቻርድ አሁንም በቤቴል በደስታ እያገለገልን ነው። ስለ አምላክ እውነቱን ማወቄ፣ ያሳስቡኝ ለነበሩ ጥያቄዎች መልስ እንዳገኝ ብቻ ሳይሆን ሕይወቴ እውነተኛ ዓላማ እንዲኖረው እንደረዳኝ ከልብ ይሰማኛል፤ ይህ ሁሉ ሊሆን የቻለው አንዲት ትንሽ ልጅ በጠየቀችኝ ሦስት ጥያቄዎች የተነሳ ነው።

^ አን.16 ይህች ትንሽ ልጅ እንዲሁም ወንድሞቿና እህቶቿ በአጠቃላይ አምስት የሚሆኑ አስተማሪዎቻቸው መጽሐፍ ቅዱስን እንዲማሩና የይሖዋ ምሥክር እንዲሆኑ ረድተዋል።

^ አን.18 “የአምላክ ቤት” የሚል ትርጉም ያለው “ቤቴል” የሚለው ቃል የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ ያሉትን ቅርንጫፍ ቢሮዎቻቸውን የሚጠሩበት ስያሜ ነው። (ዘፍጥረት 28:17, 19፣ የግርጌ ማስታወሻ) የቤቴል ቤተሰብ አባላት፣ የይሖዋ ምሥክሮች ለሚያካሂዱት የማስተማር ሥራ ድጋፍ የሚሰጡ የተለያዩ ሥራዎችን ያከናውናሉ።