በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ መስማት ለተሳናቸው ሰዎች ያስባል

አምላክ መስማት ለተሳናቸው ሰዎች ያስባል

 በዛሬው ጊዜ በዓለም ዙሪያ 70 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ መስማት የተሳናቸው ሰዎች ያሉ ሲሆን አብዛኞቹ የሚግባቡት ከ200 ከሚበልጡት የምልክት ቋንቋዎች አንዱን በመጠቀም ነው። የሚያሳዝነው ቀጣዮቹ መረጃዎች እንደሚያሳዩት መስማት የተሳናቸው ሰዎች ብዙ ጊዜ በሌሎች ሰዎች ግፍ ይፈጸምባቸዋል።

  •   “በዓለም ዙሪያ መስማት የተሳናቸውና ለመስማት የሚቸገሩ ሰዎች መብቶች በአብዛኛው ችላ ይባላሉ።”—ብሔራዊ መስማት የተሳናቸው ሰዎች ማኅበር (ዩናይትድ ስቴትስ)

  •   “በታዳጊ አገሮች ውስጥ በጣም ድሃ ከሚባሉት ሰዎች መካከል መስማት የተሳናቸው ሰዎች ይገኙበታል፤ በቂ ትምህርትና መረጃ ለማግኘት እንዲሁም ሥራ ለመቀጠር ይቸገራሉ።”—የዓለም መስማት የተሳናቸው ሰዎች ፌዴሬሽን

 አምላክ መስማት ስለተሳናቸው ሰዎች ምን ይሰማዋል? መጽሐፍ ቅዱስ መስማት ስለተሳናቸው ሰዎች ምን ይላል? የይሖዋ ምሥክሮችስ በዛሬው ጊዜ እነሱን ለመርዳት ምን እያደረጉ ነው?

አምላክ መስማት ለተሳናቸው ሰዎች ያለው አመለካከት

 መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ a አምላክ መስማት ለተሳናቸው ሰዎች እንደሚያስብ ይጠቁማል። ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንዲያዙና እሱ ከሚሰጠው ትምህርት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይፈልጋል።

 ጥቅስ፦ “መስማት የተሳነውን አትርገም።”​—ዘሌዋውያን 19:14

 ትርጉሙ፦ ይሖዋ ለጥንቶቹ እስራኤላውያን የሰጠው ሕግ መስማት የተሳናቸውን ሰዎች መብት የሚያስጠብቅ ነበር።

 ጥቅስ፦ “አምላክ [አያዳላም]።”​—የሐዋርያት ሥራ 10:34

 ትርጉሙ፦ ይሖዋ መስማት የተሳናቸውን ሰዎች ጨምሮ ሁሉም ዓይነት ቋንቋ፣ ባሕልና አስተዳደግ ላላቸው ሰዎች ያስባል።

 ጥቅስ፦ “ኢየሱስ . . . የመንግሥቱን ምሥራች እየሰበከ . . . ይዞር ጀመር።”​—ማቴዎስ 9:35

 ትርጉሙ፦ ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው ሰዎችን ስለ አምላክ መንግሥት እንዲሁም ይህ መንግሥት መስማት የተሳናቸውን ሰዎች ጨምሮ ለሁሉም የሰው ልጆች ስለሚያከናውናቸው ነገሮች ለማስተማር ነው።​—ማቴዎስ 6:10

 ጥቅስ፦ ኢየሱስ “መስማት የተሳናቸው ሰዎች እንዲሰሙ፣ ዱዳዎችም እንዲናገሩ” አድርጓል።​—ማርቆስ 7:37

 ትርጉሙ፦ ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት መስማት የተሳናቸው ሰዎች እንዲሰሙና እንዲናገሩ እንደሚያደርግ አሳይቷል። በዚህ ወቅት ኢየሱስ መስማት የተሳነው ሰው የመስማትና የመናገር ችሎታውን መልሶ እንዲያገኝ ከማድረጉ በፊት አካላዊ መግለጫዎችን በመጠቀም በደግነት ከግለሰቡ ጋር ለመግባባት ጥረት አድርጓል።​—ማርቆስ 7:32

 ጥቅስ፦ “መስማት የተሳናቸው ሰዎች [ጆሮ] ይከፈታል።”​—ኢሳይያስ 35:5

 ትርጉሙ፦ ይሖዋ መስማት የተሳናቸው ሰዎች የሚሰሙበት ጊዜ እንደሚመጣ አስቀድሞ ተናግሯል።​—ኢሳይያስ 29:18

የይሖዋ ምሥክሮች መስማት የተሳናቸውን ሰዎች እየረዱ ያሉት እንዴት ነው?

 እኛ የይሖዋ ምሥክሮች ተስፋ የሚፈነጥቀውን የአምላክን መልእክት በዓለም ዙሪያ ላሉ መስማት የተሳናቸው ሰዎች እንሰብካለን። ይህን እያደረግን ያለነው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስንና መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ ቪዲዮዎችን ከ100 በሚበልጡ ምልክት ቋንቋዎች እናዘጋጃለን። በተጨማሪም በምልክት ቋንቋ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እንሰጣለን እንዲሁም ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችን እናደርጋለን። የአምላክን እርዳታ የሚፈልጉ ሁሉ እነዚህን ዝግጅቶች በነፃ ማግኘት ይችላሉ። ለምን? ምክንያቱም ኢየሱስ “በነፃ እንደተቀበላችሁ በነፃ ስጡ” በማለት አዞናል።​—ማቴዎስ 10:8

 እነዚህን መረጃዎች ከሚከተሉት ምንጮች በቀጥታ ኢንተርኔት ላይ ማግኘት ወይም ማውረድ ትችላለህ፦

 JW.ORG። በሁሉም ገጾች ላይ ከላይ የሚገኘውን የቋንቋ ምልክት በመጫን በመረጥከው የምልክት ቋንቋ መረጃዎችን ማግኘት ትችላለህ።

 JW Library Sign Language የተባለው አፕሊኬሽን። ይህን አፕሊኬሽን በኤሌክትሮኒክ መሣሪያህ ላይ በነፃ በመጫን የምልክት ቋንቋ ቪዲዮዎችን ማውረድ ወይም በቀጥታ መመልከት ትችላለህ።

የትኞቹን የመጽሐፍ ቅዱስ ማስተማሪያ መሣሪያዎች አዘጋጅተናል?

 መጽሐፍ ቅዱስ በምልክት ቋንቋ። በአሜሪካ ምልክት ቋንቋ የተዘጋጀው አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በዓለም ላይ የመጀመሪያው ሙሉ የምልክት ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። አዲስ ዓለም ትርጉም ሙሉ በሙሉም ሆነ በከፊል በበርካታ ምልክት ቋንቋዎች ይገኛል፤ ደግሞም በየዓመቱ አዳዲስ ቋንቋዎች እየተጨመሩ ነው። (የቋንቋዎቹን ዝርዝር ወይም ኢንተርኔት ላይ መጽሐፍ ቅዱሱን ለማግኘት  አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በምልክት ቋንቋ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

  •   መጽሐፍ ቅዱስን በምልክት ቋንቋ የምናዘጋጀው እንዴት እንደሆነ ለማየት ሙሉው አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በአሜሪካ ምልክት ቋንቋ ወጣ የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት።

  •   የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብህን ይበልጥ አስደሳች ለማድረግ JW Library Sign Language የተባለውን አፕሊኬሽን አውርድ። ይህ አፕሊኬሽን በምልክት ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የፈለግከውን ጥቅስ መርጠህ ለማየት ያስችልሃል።

  •   ዲሜትሮ እና ቪታ መስማት የተሳናቸው ወላጆች ናቸው፤ ልጆቻቸው ደግሞ መስማት ይችላሉ። ቤተሰባቸው በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን በምልክት ቋንቋ በማየቱ የተጠቀመው እንዴት እንደሆነ ተመልከት።

 ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምሩ ቪዲዮዎች። የይሖዋ ምሥክሮች ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ጠቃሚ ምክር መረዳትና ሥራ ላይ ማዋል እንዲችሉ የሚረዱ ቪዲዮዎችን በምልክት ቋንቋ አዘጋጅተዋል መጽሐፍ ቅዱስ . . .

 በግለሰብ ደረጃ የሚሰጥ አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት። የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት አንድ አስተማሪ ተመድቦልህ የመረዳት ችሎታህን ባገናዘበ መልኩ በምልክት ቋንቋ እንድትማር እንጋብዝሃለን። ይህ ነፃ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የሚሰጠው እንዴት እንደሆነ ማወቅ ከፈለግክ የይሖዋ ምሥክሮች መጥተው እንዲያነጋግሩህ መጠየቅ ትችላለህ።

 ጄሰን ሴናጆኖን የሚኖረው በፊሊፒንስ ነው። የምንሰጠው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ከአምላክ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንዲመሠርት የረዳው እንዴት እንደሆነ ተመልከት።

 ማሪዮ አንቱኔስ በሆንዱራስ የሚኖር የቤተ ክርስቲያን ፓስተር ነበር። “በጣም ብዙ ጥያቄ ነበረኝ” የሚል ርዕስ ባለው የሕይወት ታሪኩ ላይ ለተፈጠሩበት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎች መልስ ያገኘው እንዴት እንደሆነ አንብብ።

 ስብሰባዎችና ልዩ ፕሮግራሞች። በዓለም ዙሪያ በምልክት ቋንቋ የሚካሄዱ ጉባኤዎችና ቡድኖች አሉን፤ በእነዚህ ጉባኤዎችና ቡድኖች ውስጥ መስማት የተሳናቸው ሰዎች በየሳምንቱ በመሰብሰብ መጽሐፍ ቅዱስን ይማራሉ እንዲሁም አምልኮ ያቀርባሉ። በተጨማሪም በየዓመቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የሚሰጥባቸው ትላልቅ ፕሮግራሞችን እናዘጋጃለን። በስብሰባዎቻችንና በልዩ ፕሮግራሞቻችን ላይ መስማትም ማየትም ለማይችሉ ሰዎች የእጅ ለእጅ ምልክት ቋንቋ በመጠቀም እናስተረጉማለን። በተጨማሪም በብሬይል የተዘጋጁ ጽሑፎችን በነፃ እንሰጣለን።

 የይሖዋ ምሥክር የሆነው ጄምስ ራያን ሲወለድ ጀምሮ መስማት የተሳነው ነበር፤ በኋላም ዓይኑ ታወረ። የቤተሰቡና የጉባኤው እርዳታ፣ ካጣው ይልቅ ያገኘው ነገር እንደሚበልጥ እንዲሰማው ያደረገው እንዴት እንደሆነ ተመልከት።

a ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው። (መዝሙር 83:18) “ይሖዋ ማን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።