በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ነቅታችሁ ጠብቁ!

ዓለም አቀፍ የዋጋ ግሽበት—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ዓለም አቀፍ የዋጋ ግሽበት—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 ሰኔ 2022 በወጣው ሪፖርት ላይ የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት እንዲህ ሲሉ አስጠንቅቀዋል፦ “የዓለም ኢኮኖሚ በድጋሚ አደጋ ላይ ወድቋል። የአሁኑን ፈታኝ የሚያደርገው፣ የዋጋ ግሽበቱ እንዳለ ሆኖ አዝጋሚ የኢኮኖሚ እድገት ያጋጠመን መሆኑ ነው።”

 ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም እንዲህ ብሏል፦ “የነዳጅና የምግብ ዋጋ በአስደንጋጭ ሁኔታ እየጨመረ ነው፤ በዚህ በጣም የሚጎዱት ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ናቸው።”

 መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያለ ከባድ የኢኮኖሚ ችግር ያጋጠመን ለምን እንደሆነ ይነግረናል፤ ችግሩን ለመቋቋም ምን ማድረግ እንደምንችል ይመክረናል፤ እንዲሁም ዘላቂ መፍትሔ የሚሆነውን ነገር በመናገር ተስፋ ይሰጠናል።

“በመጨረሻዎቹ ቀናት” የዋጋ ንረት ይከሰታል

  •    መጽሐፍ ቅዱስ፣ የምንኖርበትን ጊዜ ‘የመጨረሻዎቹ ቀናት’ ብሎ ይጠራዋል።—2 ጢሞቴዎስ 3:1

  •    ኢየሱስ በእነዚህ ‘የመጨረሻዎቹ ቀናት’ “የሚያስፈሩ ነገሮች” እንደሚከሰቱ ተናግሯል። (ሉቃስ 21:11) የዋጋ ግሽበት እየተባባሰ ሲሄድ ሰዎች ፍርሃት ያድርባቸዋል። ‘ነገ ምን እሆናለሁ?’ ‘ቤተሰቤን ምን አበላለሁ?’ እያሉ ይጨነቃሉ።

  •    “በመጨረሻዎቹ ቀናት” የምግብ ዋጋ እንደሚጨምር የራእይ መጽሐፍ አስቀድሞ ተናግሯል። ትንቢቱ እንዲህ ይላል፦ “[አንድ] ድምፅ፣ ‘ግማሽ ኪሎ ያኽል ስንዴ የአንድ ቀን ደመወዝ፣ . . . አንድ ኪሎ ተኩል ያኽል ገብስ ለአንድ ቀን ደመወዝ ይሁን . . .’ ሲል ሰማሁ።”—ራእይ 6:6 የታረመው የ1980 ትርጉም

 ስለ “መጨረሻዎቹ ቀናት” እንዲሁም በራእይ መጽሐፍ ላይ ስለሚገኘው ትንቢት ይበልጥ ማወቅ ትፈልጋለህ? ከ1914 ወዲህ የዓለም ሁኔታ ተቀይሯል የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት፤ እንዲሁም “አራቱ ፈረሰኞች—እነማን ናቸው?” የሚለውን ርዕስ አንብብ።

ሁሉም የኢኮኖሚ ችግሮች መፍትሔ ያገኛሉ

  •    “ቤቶችን ይሠራሉ፤ በዚያም ይኖራሉ፤ ወይንንም ይተክላሉ፤ ፍሬውንም ይበላሉ። እነሱ በሠሩት ቤት ሌላ ሰው አይኖርም፤ እነሱ የተከሉትንም ሌላ ሰው አይበላውም።”—ኢሳይያስ 65:21, 22

  •    “በምድር ላይ እህል ይትረፈረፋል፤ በተራሮችም አናት ላይ በብዛት ይኖራል።”—መዝሙር 72:16

  •    “‘የተጎሳቆሉት ሰዎች በመጨቆናቸው፣ ድሆችም በመቃተታቸው፣ እርምጃ ለመውሰድ እነሳለሁ’ ይላል ይሖዋ።”—መዝሙር 12:5 a

 አምላክ፣ ፍትሐዊ ያልሆነውን የኢኮኖሚ ሥርዓት በቅርቡ እልባት ያበጅለታል፤ ይህን ለውጥ የሚያመጣው በአንድ አገር ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ላይ ነው። እንዴት የሚለውን ማወቅ ከፈለግህ “ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ሥርዓት የሚኖርበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?” የሚለውን ርዕስ አንብብ።

 ሆኖም ይህ ጊዜ እስኪመጣ መጽሐፍ ቅዱስ ፈተና የሆነብንን የዋጋ ንረት ለመቋቋም ይረዳናል። እንዴት? ገንዘባችንን በጥበብ መጠቀም እንድንችል ጠቃሚ ምክር ይሰጠናል። (ምሳሌ 23:4, 5፤ መክብብ 7:12) ስለዚህ ጉዳይ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “ዓለም በተቃወሰበት ጊዜ—መተዳደሪያህ” እና “በአነስተኛ ገቢ መኖር የምትችለው እንዴት ነው?” የሚሉትን ርዕሶች አንብብ።

a ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው።—መዝሙር 83:18