በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በሎቩዋ የስደተኞች ካምፕ ውስጥ የሚኖሩ ስደተኞች በቼሉባ ቋንቋ በተዘጋጀው የወረዳ ስብሰባ ላይ

መስከረም 12, 2019
አንጎላ

በአንጎላ በሚገኝ የስደተኞች ካምፕ ውስጥ በሊንጋላ እና በቼሉባ ቋንቋዎች የወረዳ ስብሰባ ተካሄደ

በአንጎላ በሚገኝ የስደተኞች ካምፕ ውስጥ በሊንጋላ እና በቼሉባ ቋንቋዎች የወረዳ ስብሰባ ተካሄደ

“ብርቱ ሁኑ!” የተሰኘው የወረዳ ስብሰባ ግንቦት 25 እና 26, 2019 በሎቩዋ የስደተኞች ካምፕ ውስጥ በሊንጋላ እና በቼሉባ ቋንቋዎች ተካሂዷል። ይህ ካምፕ የሚገኘው የአንጎላ ዋና ከተማ ከሆነችው ከሉዋንዳ 1,022 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው። ስብሰባው በተካሄደበት ወቅት በሎቩዋ ካምፕ ውስጥ 177 አስፋፊዎችና ቤተሰቦቻቸው ይኖሩ ነበር። ሆኖም በሊንጋላ ቋንቋ በተካሄደው ስብሰባ ላይ 380 የሚያህሉ ሰዎች የተገኙ ሲሆን 3 ተጠማቂዎች ነበሩ፤ በቼሉባ ቋንቋ በተካሄደው ስብሰባ ላይ ደግሞ 630 ሰዎች የተገኙ ሲሆን 6 ሰዎች ተጠምቀዋል።

በሎቩዋ የሚገኙት አብዛኞቹ ወንድሞቻችን ወደዚያ የሸሹት በኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ውስጥ በተነሳው ዓመፅ ምክንያት ነው። በካምፑ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ከካምፑ መውጣት ስለማይፈቀድላቸው በዚያ ያሉ ወንድሞች በሌሎች ከተሞች ውስጥ በሚካሄዱ መንፈሳዊ ፕሮግራሞች ላይ መገኘት አይችሉም። በመሆኑም ቅርንጫፍ ቢሮው በካምፑ ውስጥ የወረዳ ስብሰባ እንዲካሄድ ዝግጅት ከማድረጉም በተጨማሪ ሁለት ጊዜያዊ የጉባኤ ስብሰባ አዳራሾችን ገንብቷል። በእነዚህ አዳራሾች ውስጥ በሊንጋላ ቋንቋ የሚመራ አንድ ጉባኤና በቼሉባ ቋንቋ የሚመሩ ሦስት ጉባኤዎች ይሰበሰባሉ።

ግንቦት 24, 2019 የወረዳ የበላይ ተመልካቹና የቅርንጫፍ ቢሮው ተወካይ ወደ ሎቩዋ ካምፕ ሄደው የድምፅ መሣሪያዎቹንና መድረኩን አዘጋጁ። ስደተኞቹ ወንድሞቻችን የሚኖሩት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ቢሆንም ሸራ፣ አጣና፣ ገመድ፣ ምስማርና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶችን በፈቃደኝነት ሰጥተዋል።

በካምፑ ውስጥ ካሉት በቼሉባ ቋንቋ የሚመሩ ጉባኤዎች መካከል በአንዱ ውስጥ የሚያገለግል ኦኖሬ ሎንቶንጎ የተባለ የጉባኤ አገልጋይ ከወረዳ ስብሰባው በኋላ እንዲህ ብሏል፦ “በስደተኞች ካምፕ ውስጥ ተፈታታኝ ሁኔታ ቢኖርም የወረዳ ስብሰባ መካሄዱን ማየታችን ይሖዋ በቡድን ደረጃ ብቻ ሳይሆን በግለሰብ ደረጃም እንደሚወደን አረጋግጦልናል። በጣም ደስ ብሎኛል!”

በፖለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት ከመኖሪያቸው ለተፈናቀሉ ወንድሞቻችን መጸለያችንን እንቀጥላለን። የትም ቢሆኑ ይሖዋ የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍና መንፈሳዊ ምግብ እንደሚሰጣቸው እንተማመናለን።—ሮም 8:38, 39

 

ወንድሞች መድረኩንና የድምፅ መሣሪያዎችን ሲያዘጋጁ

በቼሉባ ቋንቋ በተካሄደው ስብሰባ ላይ ስድስት የጥምቀት ዕጩዎች ለተጠማቂዎች የሚቀርቡትን ጥያቄዎች ለመመለስ ተነስተው

የሊንጋላ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ ወንድሞችና እህቶች የጥምቀት ሥርዓቱን ለመመልከት ከካምፑ ሁለት ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኝ ወንዝ ሲሄዱ

የአንጎላ ቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ጆሃንስ ደ ጃገር ከወረዳ ስብሰባው በኋላ ከሊንጋላ ተናጋሪ ወንድሞችና እህቶች ጋር ሆኖ