በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በኑናቩት፣ ካናዳ የሚገኘው የኢካሉዊት ከተማ። ውስጠኛው ፎቶ፦ ወንድሞችና እህቶች ከውሰና ሥነ ሥርዓቱ በኋላ ከአዳራሹ ውጪ ተሰባስበው

መስከረም 22, 2023
ዓለም አቀፋዊ ዜና

በካናዳና በዩናይትድ ስቴትስ ሰሜናዊ ጫፍ የሚኖሩ ሰዎች አስደሳች የሆነውን የመንግሥቱን መልእክት ሰሙ

በካናዳና በዩናይትድ ስቴትስ ሰሜናዊ ጫፍ የሚኖሩ ሰዎች አስደሳች የሆነውን የመንግሥቱን መልእክት ሰሙ

ወንድም ማርክ ሳንደርሰን በኢካሉዊት፣ ኑናቩት የውሰና ንግግር ሲያቀርብ

በኑናቩት፣ ካናዳ በምትገኘው የኢካሉዊት ከተማ አዲስ የተገነባ የስብሰባ አዳራሽ ግንቦት 20, 2023 ለይሖዋ አገልግሎት ተወስኗል፤ የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ማርክ ሳንደርሰን የውሰና ንግግር አቅርቧል። በውሰና ፕሮግራሙ ላይ 44 ሰዎች በአካል የተገኙ ሲሆን ሌሎች 388 ሰዎች ደግሞ ፕሮግራሙን በቪዲዮ ኮንፈረንስ ተከታትለዋል። ኑናቩት 1,837,000 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን የነዋሪዎቹ ብዛት ከ40,000 አይበልጥም፤ ይህም በሰፊ መሬት ላይ በጣም ጥቂት ሰዎች ተበታትነው ከሚኖሩባቸው የምድራችን ክፍሎች መካከል አንዱ ያደርገዋል። ከዚህ በፊት በ​jw.org ላይ እንደተገለጸው ወንድሞቻችን የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለመገንባት ለየት ያሉ ፈተናዎችን መወጣት አስፈልጓቸዋል። እውነትን ወደዚህ አካባቢ ያስተዋወቁት ደፋር ወንድሞች አስቸጋሪ የአየር ሁኔታዎችንና ወጣ ገባውን መልክዓ ምድር መቋቋም ነበረባቸው። እነዚህ ወንድሞች የተዉት የጽናት ምሳሌ በውሰና ፕሮግራሙ ላይ ተወስቷል።

ከካናዳ መሬት 40 በመቶውን የሚሸፍኑት ኑናቩት፣ ሰሜን ምዕራባዊ ክልሎች እና ዩኮን

በ1976 እህት ማርጋሬት ጋሊ ከሞንትሪያል፣ ኩዊቤክ ተነስታ 2,052 ኪሎ ሜትሮችን በመጓዝ ኑናቩት ውስጥ አሁን ኢካሉዊት ተብሎ ወደሚጠራው ቦታ ሄደች። በዚያ ሰፊና ጠፍ አገር የሰበከች የመጀመሪያዋ የይሖዋ ምሥክር እሷ ናት። በኋላ ላይ በዚያው ዓመት ወንድም ሃንስ ፒንታር የተባለ የወረዳ የበላይ ተመልካችና ሚስቱ ሚኔርቫ እህት ጋሊን ለማበረታታትና አብረዋት ለማገልገል ለአንድ ሳምንት የቆየ ልዩ ጉብኝት አድርገውላታል።

ቆየት ብሎም በ1983 ቀናተኛ ምሥክሮችን ያቀፈ አንድ አነስተኛ ቡድን ወደ ኢካሉዊት ተጓዘ። በስብከቱ ሥራ ላይ በትብብር ያደረጉት ጥረት ተሳክቶ ለመጀመሪያ ጊዜ የአካባቢው ነዋሪ የሆኑ የአንድ ቤተሰብ አባላት ሊጠመቁ ችለዋል። በቀጣዮቹ 20 ዓመታት ደፋር የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ወደዚህ ገለልተኛ አካባቢ በተደጋጋሚ ጉዞ በማድረግ ምሥራቹን ለሌሎች አካፍለዋል። በ2008 በኢካሉዊት አንድ ቡድን ተቋቋመ። በ2010 ይህ ቡድን ወደ ጉባኤ አድጎ በአንድ የትምህርት ቤት የስፖርት ማዘውተሪያ ውስጥ መሰብሰብ ጀመረ። ወንድሞችና እህቶች ጥቅምት 2022 አዲስ በተገነባላቸው የስብሰባ አዳራሽ መሰብሰብ ሲጀምሩ እጅግ ተደሰቱ።

ለብዙ ዓመታት በካናዳ ሰሜናዊ ጫፍ ያለውን አስቸጋሪ ሁኔታ ተቋቁመው ራሳቸውን ሳይቆጥቡ ያገለገሉ ደፋር አስፋፊዎች

ልዩ አቅኚዎች ከሌሎች አስፋፊዎች ጋር በመሆን ከኢካሉዊት በተጨማሪ በመላው ኑናቩት በሚገኙ ገለልተኛ ክልሎች ውስጥ ሰብከዋል። ወንድም ጆወል ቴርየ እና ባለቤቱ ሸሪል ከእነዚህ ሰባኪዎች መካከል ይገኙበታል። ከኢካሉዊት በስተ ምዕራብ 1,329 ኪሎ ሜትሮች ርቆ ወደሚገኘው ወደ ቤከር ሌክ ተዛውረው መስበክ ጀመሩ። ወንድም ጆወል ሁኔታውን ሲያስታውስ እንዲህ ይላል፦ “ብርዱ፣ ከሰዎች ርቆ መኖሩና የጠየቀብን ወጪ እንዳለ ሆኖ የከፈልነው መሥዋዕትነት ግን ክሶናል። የቤከር ሌክ ነዋሪዎች የሰጡት ምላሽ ይሖዋ እንደባረከን የሚያሳይና ልብን በደስታ የሚያሞቅ ነበር። በዚያ ለሚኖሩ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት የማካፈል አጋጣሚ በማግኘታችን አመስጋኞች ነን።”

ወንድም ጆወል ቴርየ እና ጆሴፍ ኡታትናክ ዊኒፔግ፣ ካናዳ በተካሄደው “በትዕግሥት ጠብቁ”! የክልል ስብሰባ ላይ፣ ነሐሴ 25, 2023

ጆሴፍ ኡታትናክ የቤከር ሌክ ነዋሪ ነው፤ ለመንግሥቱ ምሥራችም አዎንታዊ ምላሽ ሰጥቷል። ከወንድም ጆወል ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የተስማማ ሲሆን በ2021 ተጠምቋል። በአሁን ወቅት በቤከር ሌክ የሚኖረው አስፋፊ ወንድም ጆሴፍ ብቻ ነው። ግንቦት 2023 በኢካሉዊት የስብሰባ አዳራሽ ውሰና ፕሮግራም እንደሚደረግ ሲሰማ በዝግጅቱ ላይ ለመገኘት ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። ከተጠመቀ ወዲህ ከወንድሞችና ከእህቶች ጋር በአካል በስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ሲሰበሰብ ይህ የመጀመሪያው ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “የስብሰባ አዳራሹ ተጠናቅቆ ሳየው በጣም ነው የተገረምኩት። በግንባታ ሥራው ከተካፈሉት መካከል ብዙዎቹ የአካባቢው ነዋሪዎች አልነበሩም፤ የአየር ጠባዩንም ሆነ የአካባቢውን ሁኔታ አያውቁትም። ይህን ለማድረግ ያነሳሳቸው ለይሖዋና ለሌሎች ያላቸው ፍቅር እንደሆነ በግልጽ ይታይ ነበር።”

በአሁኑ ወቅት በካናዳ ሰሜናዊ ክልሎች ውስጥ 178 ወንድሞችና እህቶችን ያቀፉ አራት ጉባኤዎች አሉ፤ በኑናቩት አንድ ጉባኤ፣ በሰሜን ምዕራባዊ ክልሎች ሁለት ጉባኤዎች እና በዩኮን አንድ ጉባኤ ይገኛሉ። እነዚህ ክልሎች ከካናዳ የመሬት ስፋት ውስጥ ወደ 40 በመቶ የሚጠጋውን ይሸፍናሉ። በካናዳ ሰሜናዊ ጫፍ ከባድ ቅዝቃዜ ያለ ሲሆን መልክዓ ምድሩም አባጣ ጎርባጣ ነው፤ ይህም በዚህ ገለልተኛ ክልል ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችን ማግኘት ከባድ እንዲሆን ያደርጋል። በእርግጥም በዚህ ርቆ በሚገኝ ክልል ምሥራቹን ለመስበክ ራሳቸውን ያቀረቡት ወንድሞችና እህቶች የሚያደርጉት ጥረት የሚደነቅ ነው።—የሐዋርያት ሥራ 1:8

በአላስካ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ ገለልተኛ ክልሎች

ከላይ በስተ ቀኝ፦ በሄይንዝ፣ አላስካ የሚገኘው የስብሰባ አዳራሽ። ከታች በስተ ቀኝ፦ በሄይንዝ የሚገኘው ጉባኤ በአዲሱ አዳራሽ ውስጥ ተሰብስቦ

አላስካ 1,723,000 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን ከዩናይትድ ስቴትስ ግዛቶች ሁሉ ትልቁና ሰሜናዊው ጫፍ ነው፤ ስፋቱ ከቴክሳስ ግዛት በእጥፍ ይበልጣል። በአላስካ 730,000 ገደማ ሰዎች ይኖራሉ። የመንግሥቱ ምሥራች ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አላስካ የደረሰው በ1897 ነው፤ በአሁኑ ወቅት በ30 ጉባኤዎችና በ8 ቡድኖች ውስጥ የሚያገለግሉ 2,400 ገደማ የመንግሥቱ አስፋፊዎች አሉ። በአንከሬጅ ማለትም በአላስካ ትልቋ ከተማ አስር ጉባኤዎችና አምስት ቡድኖች አሉ፤ ጉባኤዎቹ ከሚመሩባቸው ቋንቋዎች መካከል ህሞንግ፣ ኮሪያኛ እና የማዕከላዊ አላስካ ዩፒክ የተባለው አገር በቀል ቋንቋ ይገኙበታል። እንደ ፌርባንክስ፣ ዡኖ እና ዋሲላ ባሉ ሌሎች ከተሞችም እንዲሁ በተለያዩ ቋንቋዎች የሚመሩ ጉባኤዎችና ቡድኖች አሉ። በተጨማሪም ገለልተኛ ክልል በሆኑት እንደ ቤቴል፣ ራንጌል እና ሄይንዝ ባሉ አነስተኛ ከተሞች ውስጥ ምሥራቹ እየተሰበከ ይገኛል።

ወንድም ኬነዝ ኩክ በሄይንዝ፣ አላስካ የውሰና ንግግር ሲያቀርብ

ነሐሴ 2014 ሴባቢ ሌባሎ እና ደስቲን ዋትሰን የተባሉ ሁለት ልዩ አቅኚ ወንድሞች ወደ ሄይንዝ ተዛውረው እንዲያገለግሉ ተጋበዙ። ሄይንዝ ከአንከሬጅ በስተ ደቡብ ምሥራቅ አቅጣጫ 825 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቃ የምትገኝ ቦታ ናት። ልዩ አቅኚዎቹ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ፍላጎት ላሳዩ 40 የአካባቢው ነዋሪዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራት ጀመሩ። ከእነዚህ ጥናቶች መካከል የተወሰኑት እድገት አድርገው ተጠመቁ። በ2018 በሄይንዝ አነስተኛ ጉባኤ ተቋቁሞ በአካባቢው በሚገኝ አንድ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ መሰብሰብ ጀመረ። በ2021 አንድ ሕንፃ ተገዝቶ ወደ መሰብሰቢያ አዳራሽነት ተቀየረ። በኋላም መስከረም 2022 አዳራሹ ለይሖዋ አገልግሎት ተወሰነ፤ የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ኬነዝ ኩክ 48 ሰዎች በተገኙበትና ለ86 ሰዎች በቪዲዮ ኮንፈረንስ በተላለፈ ፕሮግራም ላይ የውሰና ንግግር አቀረበ። በአሁኑ ወቅት ይህ ጉባኤ በሄይንዝ እና በሌሎች ርቀው የሚገኙ ክልሎች ምሥራቹን የሚሰብኩ 21 አስፋፊዎች አሉት።

ወንድም ደስቲን ዋትሰን (በስተ ግራ) እና ወንድም ሴባቢ ሌባሎ (በስተ ቀኝ) በ2014 ሄይንዝ፣ አላስካ ሲደርሱ

ወንድም ሌባሎ በ2022 በተካሄደው የስብሰባ አዳራሽ ውሰና ላይ በተገኘ ጊዜ እንዲህ ሲል ቀድሞ የነበረውን ሁኔታ አስታውሷል፦ “የዛሬ ስምንት ዓመት እኔ እዚህ ስመጣ ጉባኤ ተቋቁሞ የስብሰባ አዳራሽ ይገነባል ብሎ ማሰብ ዘበት ነበር። ይሖዋ ርቀው በሚገኙ አካባቢዎች እንኳ ሳይቀር ‘ሁሉም ዓይነት ሰዎች’ ስለ እሱ እንዲማሩ ማስቻሉ በጣም የሚያበረታታ ነው።”—1 ጢሞቴዎስ 2:4