በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቫካቪል፣ ካሊፎርኒያ የሚገኘው እስር ቤት

ታኅሣሥ 25, 2020
ዩናይትድ ስቴትስ

የእንቅስቃሴ ገደብ ቢጣልም ለእስረኞች የሚቀርበው መንፈሳዊ ምግብ ቀጥሏል

የእንቅስቃሴ ገደብ ቢጣልም ለእስረኞች የሚቀርበው መንፈሳዊ ምግብ ቀጥሏል

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በመላው ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኙ ማረሚያ ቤቶች ላይ የእንቅስቃሴ ገደብ ተጥሎ ነበር፤ በዚህም የተነሳ በመቶዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ቀድሞ ያደርጉት እንደነበረው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ለመስጠትና መጽሐፍ ቅዱስ ለማስተማር ወደ ማረሚያ ቤቶች መሄድ አልቻሉም፤ ይህ ደግሞ በሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞች መንፈሳዊ ምግብ እንዳይደርሳቸው እንቅፋት የሚፈጥር ነበር። ወንድሞቻችን ግን የኮቪድ-19 የደህንነት መመሪያዎችን በጠበቀ መልኩ በእስር ቤት የሚያከናውኑትን አገልግሎት ለመቀጠል የሚያስችሏቸው ዘዴዎች ቀይሰዋል።

በዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ቢሮ ክልል በማረሚያ ቤቶች የሚሰጠውን አገልግሎት የሚያስተባብረው ወንድም ዳን ሆተን እንዲህ ብሏል፦ “በጣም ያሳሰበን፣ እኛ ካልሄድን መንፈሳዊ ምግብ የሚያገኙበት መንገድ የሌላቸው እስረኞች ጉዳይ ነበር። ደግሞም እነዚህ ሰዎች በተለይ በዚህ ጊዜ የእኛ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል።”

ለምሳሌ ያህል፣ ወንድም ማይካ ሲርስታድ በማረሚያ ቤቶቹ ውስጥ የ​JW ብሮድካስቲንግ ቪዲዮዎችን ማሳየት ይቻል እንደሆነ በቫካቪል፣ ካሊፎርኒያ ያሉ የእስር ቤት ኃላፊዎችን ጠይቆ ነበር። ኃላፊዎቹ በካሊፎርኒያ ግዛት ባሉት በ33ቱም እስር ቤቶች ውስጥ በሚተላለፍ የቴሌቪዥን ጣቢያ ቪዲዮዎቹን እንዲያሳይ ሲጠይቁት ወንድማችን በጣም ተገረመ። በዚህም የተነሳ ‘ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ’! የተሰኘው የ2020 የክልል ስብሰባ ፕሮግራም በ28 ደቂቃ ቪዲዮዎች ተቆራርጦ በቀን ሦስት ጊዜ እንዲታይ ተደረገ፤ በአጠቃላይ 130,000 የሚሆኑ ሰዎች ይህን ፕሮግራም የማየት አጋጣሚ ነበራቸው።

ወንድም ማይካ ሲርስታድ እንዲህ ብሏል፦ “በሚያስገርም ሁኔታ የይሖዋን እጅ አይተናል። ይሖዋ አንድ ነገር እንዲሆን ከፈለገ፣ ምንም የሚያግደው ነገር የለም!”

በፍሎሪዳ የሚገኘው የሳራሶታ ወህኒ ቤት ኃላፊዎች፣ አዎንታዊ አመለካከት ለመያዝ የሚረዱ መጻሕፍት ለእስረኞች ማቅረብ ፈለጉ፤ ኃላፊዎቹ ይህን ማድረግ የፈለጉት እስረኞቹ የተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ የሚፈጥረውን ውጥረት እንዲቋቋሙ ይረዳቸዋል ብለው ስላሰቡ ነው። የኃላፊዎቹን ፍላጎት የተረዱት ወንድሞቻችን፣ በእንግሊዝኛና በስፓንኛ ቋንቋዎች መጽሐፍ ቅዱሶችና የተለያዩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ለመስጠት ጥያቄ አቀረቡ። ኃላፊዎቹ የወንድሞችን ጥያቄ ተቀበሉ። ወንድሞች በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት መጽሐፍ ቅዱስን ለማስተማርም ዝግጅት አደረጉ። በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት መጽሐፍ ቅዱስን እንዲማር ስለተደረገለት ዝግጅት አንድ እስረኛ ለአስተማሪው እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ለጥናት የምንገናኝበትን ጊዜ በጉጉት ነው የምጠብቀው። መጽሐፍ ቅዱስን እንዳነብ ያበረታታኛል። አሁን ስለ ወደፊቱ ጊዜ ያለኝ አመለካከት ተለውጧል።”

የሳራሶታ ወህኒ ቤት ኃላፊዎች፣ 70 እንግሊዝኛና ስፓንኛ መጽሐፍ ቅዱሶችን እንዲሁም 30 መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ከወንድም ማኖሎ ሮድሪጌዝ ቤት ሲወስዱ፤ ወንድም ማኖሎ ሮድሪጌዝ ጽሑፎቹን መኪናቸው ላይ በመጫን ሲያግዛቸው

ወረርሽኝም ሆነ እስር ቤት አፍቃሪው አባታችን ይሖዋ፣ በመንፈሳዊ የተጠሙ ሰዎችን ፍላጎት ከማርካት ሊያግዱት አይችሉም፤ በዚህም በጣም ደስተኞች ነን።—መዝሙር 139:7-10