በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ሮም ውስጥ የጣሊያን ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚገኝበት ፓላስ ኦቭ ጀስቲስ የተባለው ሕንፃ

የካቲት 9, 2021
ጣሊያን

የጣሊያን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሕክምና ከመምረጥ ጋር በተያያዘ በተከፈተው ክስ ለይሖዋ ምሥክሮች ፈረደ

የጣሊያን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሕክምና ከመምረጥ ጋር በተያያዘ በተከፈተው ክስ ለይሖዋ ምሥክሮች ፈረደ

የጣሊያን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከታካሚዎች ሕክምና የመምረጥ መብት ጋር በተያያዘ ለአንዲት የይሖዋ ምሥክር ፈረደ። ታኅሣሥ 23, 2020 ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሁሉም ታካሚዎች የሚፈልጉትን ሕክምና የመምረጥ መብት እንዳላቸው በይኗል፤ ይህም ከሃይማኖታዊ እምነታቸው ጋር የማይጋጭ ውጤታማ ሕክምና የመምረጥ መብትን ይጨምራል።

ጉዳዩ በ2005 ከተፈጠረ አንድ አሳዛኝ ክንውን ጋር የተያያዘ ነው፤ በዚያ ወቅት ሐኪሞች የአንዲት እህታችንን መብት ጥሰው ነበር። እህታችን ቀዶ ሕክምና ከማድረጓ በፊት፣ ደም እንደማትወስድ በግልጽ ተናግራ እንዲሁም ይህን ውሳኔዋን በሕክምና ሰነዷ ላይ አስፍራ ነበር። ሆኖም ሐኪሞቹ ፍላጎቷን ችላ ብለው በተደጋጋሚ ደም እንዲሰጣት አደረጉ።

ፍርድ ቤቱ ‘ደም አልወስድም ማለት አንድን ሕክምና ከመምረጥ ጋር ብቻ የተያያዘ እንዳልሆነ፣ ከዚህ ይልቅ አንድ ሰው በሃይማኖታዊ እምነቱ ምክንያት አስቦበት የሚያደርገው ውሳኔ’ እንደሆነ ገልጿል። ይህ መብት “ሕገ መንግሥቱ ‘ሙሉ በሙሉ’ ጥበቃ የሚያደርግለት ሊጣስ የማይገባው” መብት እንደሆነም ተናግሯል።

ይህ ውሳኔ የይሖዋ ምሥክሮች ከ2015 ወዲህ በጣሊያን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ካገኟቸው አሥር ተከታታይ ድሎች የመጨረሻው ነው። ፍርድ ቤቱ በእያንዳንዱ ውሳኔ ላይ ከሃይማኖታዊ ነፃነታችን ጋር የተያያዙ ወሳኝ ጉዳዮችን አስከብሯል። ውሳኔዎቹ የሚከተሉትን ጉዳዮች የሚመለከቱ ነበሩ፦

  • ደም ለመውሰድ ፈቃደኛ አለመሆን፦ የይሖዋ ምሥክሮች በተቻለ መጠን የተሻለውን ሕክምና ማግኘት ይፈልጋሉ፤ እንዲሁም አብዛኞቹን ሕክምናዎች ይቀበላሉ። ፍርድ ቤቶቹ የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ታካሚዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ከሠለጠነ ሕሊናቸው ጋር የሚስማማ ሕክምና የመምረጥ መብት እንዳላቸው አረጋግጠዋል። አንድ ታካሚ ደም ለመውሰድ ፈቃደኛ ካልሆነ ሐኪሞች ይህን ውሳኔውን ሊያከብሩለት ይገባል። አንድ ታካሚ በሃይማኖታዊ እምነቱ ምክንያት እንዲህ ዓይነት ውሳኔ የማድረግ ሕጋዊ መብት አለው።

  • ልጆች የማሳደግ መብት፦ የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ወላጆች ለልጆቻቸው ሃይማኖታዊ ትምህርት በመስጠት ረገድ የይሖዋ ምሥክር ካልሆኑ ወላጆች እኩል መብት አላቸው።

  • ውገዳ፦ የይሖዋ ምሥክሮች በተወገዱ ሰዎች ላይ በደል አይፈጽሙም። ሆኖም የይሖዋ ምሥክሮች ከጉባኤ ከተወገዱ ሰዎች ጋር ጊዜ ላለማሳለፍ የመምረጥ ነፃነት አላቸው። ይህ ሊከበር የሚገባው የሃይማኖታዊ ነፃነት አንድ ገጽታ ነው።

  • ግብር፦ የይሖዋ ምሥክሮች ግብር ይከፍላሉ፤ እንዲሁም ለአምልኮ ቦታዎች ግብር ከመክፈልና ከግብር ነፃ ከመሆን ጋር በተያያዘ ጣሊያን ውስጥ ካሉት ሌሎች ሃይማኖቶች ጋር ተመሳሳይ መብት አላቸው።

የመንግሥት ባለሥልጣናት የይሖዋ ሕዝቦች ያላቸውን የአምልኮ ነፃነት የሚያስከብሩ ውሳኔዎችን ሲያደርጉ በጣም እንደሰታለን።—ምሳሌ 21:1