በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ንድፍ አውጪ አለው?

ዶልፊኖች አካባቢያቸውን ለማወቅ የሚጠቀሙበት ዘዴ

ዶልፊኖች አካባቢያቸውን ለማወቅ የሚጠቀሙበት ዘዴ

 ዶልፊኖች ፉጨትን ጨምሮ የተለያዩ ድምፆችን ካወጡ በኋላ ነጥሮ የሚመለሰውን ድምፅ በመስማት አቅጣጫቸውን መወሰንና በአካባቢያቸው ያሉትን ነገሮች ማወቅ ይችላሉ። ሳይንቲስቶች ቦትልኖዝ የተባለው ዶልፊን (ተርሲየፕስ ትራንካተስ) ያለውን ይህን ተፈጥሯዊ ችሎታ በመኮረጅ በድምፅ ሞገድ የሚሠሩ መሣሪያዎችን ለመሥራት እየሞከሩ ነው፤ እነዚህ መሣሪያዎች ውኃ ውስጥ የሚያገለግሉ ሲሆን አሁን ያለው ቴክኖሎጂ ሊፈታ የማይችላቸውን ችግሮች ለመፍታት ያስችላሉ።

 እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ ዶልፊኖች ድምፅን በመጠቀም የባሕር ወለል ላይ አሸዋ ውስጥ የተደበቁ ዓሣዎችን ማግኘት እንዲሁም ዓሣንና ድንጋይን ለይተው ማወቅ ይችላሉ። በኤደንብራ፣ ስኮትላንድ በሚገኘው ሄሪየት ዋት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ኬት ብራውን እንደተናገሩት ዶልፊኖች “ከአሥር ሜትር [ርቀት] ላይ ሆነው በአንድ ዕቃ ውስጥ ያለው ፈሳሽ ጨዋማ ያልሆነ ውኃ፣ ጨዋማ ውኃ፣ ጣፋጭ ፈሳሽ አሊያም ዘይት መሆኑን መለየት ይችላሉ።” ሳይንቲስቶች በተወሰነ መጠን እንኳ እንዲህ ማድረግ የሚችሉ መሣሪያዎችን የመሥራት ፍላጎት አላቸው።

ዶልፊኖች ከአሥር ሜትር ርቀት ላይ ሆነው የተለያየ ፈሳሽ የያዙ ዕቃዎችን መለየት ይችላሉ

 ተመራማሪዎች ዶልፊኖች ድምፅ የሚያወጡበትንና የሚሰሙበትን መንገድ በማጥናት ያንኑ አስመስለው ለመሥራት ሞክረዋል። በውጤቱም ከአንድ ሜትር ያነሰ ቁመት ባለው እንደ ቱቦ ያለ ዕቃ ውስጥ የሚቀመጥና ውስብስብ የሆነ የኤሌክትሮኒክ ሥርዓት ያለው ድምፅን ተጠቅሞ የሚሠራ መሣሪያ መሥራት ችለዋል። የሚሳይል ቅርጽ ባለው በራሱ የሚንቀሳቀስ ተሽከርካሪ ላይ የተገጠመው ይህ መሣሪያ የባሕርን ወለል ለመቃኘት እንዲሁም እንደ ወፍራም ሽቦዎች ወይም የፈሳሽ ማስተላለፊያ ቧንቧዎች ያሉ ባሕር ውስጥ የተዘረጉ ነገሮችን አግኝቶ ያለምንም ንክኪ ምርመራ ለማድረግ ያስችላል። መሣሪያውን የሠሩት ሰዎች ይህ ቴክኖሎጂ በነዳጅ ዘይትና ጋዝ ኢንዱስትሪ ውስጥ ሊያገለግል እንደሚችል ይናገራሉ። ዶልፊኖችን በመኮረጅ የተሠራው ይህ መሣሪያ አሁን ካሉት ድምፅን ተጠቅመው የሚሠሩ መሣሪያዎች በተሻለ መጠን መረጃዎችን ለመሰብሰብ እንደሚያስችል ይታመናል፤ ይህም ባለሙያዎች ውኃ ውስጥ የሚቀበሩ መሣሪያዎችን ከሁሉ በተሻለ ቦታ ላይ ማስቀመጥ እንዲችሉ እንዲሁም መሣሪያዎቹ ማንኛውም ጉዳት ሲደርስባቸው ማወቅ እንዲችሉ ይረዳል፤ ለምሳሌ የፈሳሽ ማስተላለፊያ ቧንቧዎች የተዘጉበትን ቦታ አሊያም ነዳጅ ለማውጣት በሚያገለግል ማሽን እግሮች ላይ የተፈጠረን ትንሽ ስንጥቅ እንኳ ለማወቅ ያስችላል።

 ታዲያ ምን ይመስልሃል? ቦትልኖዝ የተባለው ዶልፊን አካባቢውን ለማወቅ የሚጠቀምበት ዘዴ በዝግመተ ለውጥ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?