በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

መላእክትን በተመለከተ እውነታው ምንድን ነው?

መላእክትን በተመለከተ እውነታው ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 መላእክት ከሰዎች የላቀ ኃይልና ችሎታ ያላቸው ፍጥረታት ናቸው። (2 ጴጥሮስ 2:11) መላእክት የሚኖሩት በሰማይ ማለትም ከግዑዙ ጽንፈ ዓለም ውጭ ባለው መንፈሳዊ ዓለም ውስጥ ነው። (1 ነገሥት 8:27፤ ዮሐንስ 6:38) ስለሆነም መንፈስ ተብለው የተጠሩበት ጊዜም አለ።—1 ነገሥት 22:21፤ መዝሙር 18:10

መላእክት የተፈጠሩት እንዴት ነው?

 አምላክ መላእክትን የፈጠረው መጽሐፍ ቅዱስ “የፍጥረት ሁሉ በኩር” ብሎ በሚጠራው በኢየሱስ አማካኝነት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ በፍጥረት ሥራው ላይ ኢየሱስን የተጠቀመበት እንዴት እንደሆነ ሲናገር “በሰማያትና በምድር ያሉ ሌሎች ነገሮች በሙሉ፣ የሚታዩትና የማይታዩት ነገሮች . . . የተፈጠሩት በእሱ [በኢየሱስ] አማካኝነት ነው” ይላል፤ “የማይታዩት” የሚለው አገላለጽ መላእክትንም ይጨምራል። (ቆላስይስ 1:13-17) መላእክት አይጋቡም እንዲሁም አይዋለዱም። (ማርቆስ 12:25) በመሆኑም ሁሉም “የእውነተኛው አምላክ ልጆች” ወደ ሕልውና የመጡት እያንዳንዳቸው በቀጥታ ተፈጥረው ነው።—ኢዮብ 1:6

 መላእክት የተፈጠሩት ምድር እንኳ ከመፈጠሯ ከረጅም ጊዜ በፊት ነው። አምላክ ምድርን በፈጠረበት ወቅት መላእክት ‘በደስታ ጮኸው’ ነበር።—ኢዮብ 38:4-7

ምን ያህል መላእክት አሉ?

 መጽሐፍ ቅዱስ ቁጥራቸው ምን ያህል እንደሆነ አይናገርም፤ ነገር ግን በጣም ብዙ እንደሆኑ ይጠቁማል። ለምሳሌ ያህል፣ ሐዋርያው ዮሐንስ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ መላእክትን በራእይ ተመልክቷል።—ራእይ 5:11፣ የግርጌ ማስታወሻ

መላእክት የየራሳቸው ስምና ማንነት አላቸው?

 አዎ። መጽሐፍ ቅዱስ ሚካኤልና ገብርኤል ተብለው ስለሚጠሩ ሁለት መላእክት ይናገራል። (ዳንኤል 12:1፤ ሉቃስ 1:26) a ሌሎች መላእክትም ስም እንዳላቸው ቢናገሩም ስማቸው ማን እንደሆነ ለመናገር ግን ፈቃደኛ አልሆኑም።—ዘፍጥረት 32:29፤ መሳፍንት 13:17, 18

 መላእክት የየራሳቸው ማንነት አላቸው። እንዲሁም እርስ በርስ የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ ይችላሉ። (1 ቆሮንቶስ 13:1) እንዲሁም የማሰብና አምላክን የማወደስ ችሎታ አላቸው። (ሉቃስ 2:13, 14) በተጨማሪም አንዳንድ መላእክት ከሰይጣን ጋር በማበር በአምላክ ላይ ባመፁበት ወቅት እንደታየው ትክክልና ስህተት የሆነውን የመምረጥ ነፃነት አላቸው።—ማቴዎስ 25:41፤ 2 ጴጥሮስ 2:4

መላእክት የተለያየ ማዕረግ አላቸው?

 አዎ። በኃይልም ሆነ በሥልጣን ከሁሉም የሚበልጠው መልአክ የመላእክት አለቃ የሆነው ሚካኤል ነው። (ይሁዳ 9፤ ራእይ 12:7) ሱራፌል በአምላክ ዙፋን አቅራቢያ የሚቆሙ ከፍተኛ ማዕረግ ያላቸው መላእክት ናቸው። (ኢሳይያስ 6:2, 6) ኪሩቤል የሚባሉት መላእክትም ከፍተኛ ማዕረግ ያላቸው ሲሆን ለየት ያለ ሥራ እንዲያከናውኑ ኃላፊነት ይሰጣቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ አዳምና ሔዋን ከኤደን ገነት ከተባረሩ በኋላ ኪሩቤል የኤደን ገነትን መግቢያ እንዲጠብቁ ተመድበው ነበር።—ዘፍጥረት 3:23, 24

መላእክት ሰዎችን ይረዳሉ?

 አዎ፣ አምላክ በዛሬው ጊዜ ሰዎችን ለመርዳት በታማኝ መላእክቱ ይጠቀማል።

እያንዳንዳችን ጠባቂ መልአክ አለን?

 መላእክት የአምላክ አገልጋዮች መንፈሳዊ ጉዳት እንዳይደርስባቸው የሚከላከሉ ቢሆንም አምላክ ለእያንዳንዱ ክርስቲያን አንድ አንድ ጠባቂ መልአክ ይመድባል ማለት አይደለም። b (ማቴዎስ 18:10) መላእክት፣ የአምላክ አገልጋዮች ምንም ፈተና እንዳይደርስባቸው ጥበቃ አያደርጉም። አብዛኛውን ጊዜ አምላክ፣ አንድ ሰው ከፈተና ‘የሚወጣበትን መንገድ’ የሚያዘጋጀው ግለሰቡ ፈተናውን መቋቋም የሚችልበት ጥበብና ጥንካሬ እንዲኖረው በማድረግ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።—1 ቆሮንቶስ 10:12, 13፤ ያዕቆብ 1:2-5

ሰዎች መላእክትን በተመለከተ ያላቸው የተሳሳተ አመለካከት

 የተሳሳተ አመለካከት፦ ሁሉም መላእክት ጥሩ ናቸው።

 እውነታው፦ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ “ክፉ መንፈሳዊ ኃይሎች” እንዲሁም ‘ኃጢአት ስለሠሩ መላእክት’ ይናገራል። (ኤፌሶን 6:12፤ 2 ጴጥሮስ 2:4) እነዚህ ክፉ መላእክት ከሰይጣን ጋር በማበር በአምላክ ላይ ያመፁ ሲሆን አጋንንት ተብለው ይጠራሉ።

 የተሳሳተ አመለካከት፦ መላእክት አይሞቱም።

 እውነታው፦ ሰይጣን ዲያብሎስን ጨምሮ ክፉ መላእክት በሙሉ ይጠፋሉ።—ይሁዳ 6

 የተሳሳተ አመለካከት፦ ሰዎች ሲሞቱ መላእክት ይሆናሉ።

 እውነታው፦ መላእክት፣ ትንሣኤ ያገኙ ሰዎች ሳይሆኑ አምላክ በቀጥታ መልአክ አድርጎ የፈጠራቸው ፍጥረታት ናቸው። (ቆላስይስ 1:16) አምላክ ትንሣኤ አግኝተው ወደ ሰማይ ለሚሄዱ ሰዎች የማይሞት ሕይወት ይሰጣቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 15:53, 54) እነዚህ ሰዎች ከመላእክት እንኳ የላቀ ቦታ ይኖራቸዋል።—1 ቆሮንቶስ 6:3

 የተሳሳተ አመለካከት፦ መላእክት የተፈጠሩት ሰዎችን ለማገልገል ነው።

 እውነታው፦ መላእክት ትእዛዝ የሚቀበሉት ከሰው ሳይሆን ከአምላክ ነው። (መዝሙር 103:20, 21) ኢየሱስም እንኳ የመላእክትን እርዳታ ለማግኘት አባቱን መጠየቅ እንዳለበት ተናግሯል።—ማቴዎስ 26:53

 የተሳሳተ አመለካከት፦ መላእክት እንዲረዱን ወደ እነሱ መጸለይ እንችላለን።

 እውነታው፦ ጸሎት የአምልኳችን ክፍል ነው፤ አምልኮ መቅረብ የሚገባው ደግሞ ለይሖዋ አምላክ ብቻ ነው። (ራእይ 19:10) መጸለይ ያለብን በኢየሱስ በኩል ወደ አምላክ ብቻ ነው።—ዮሐንስ 14:6

a አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ኢሳይያስ 14:12 ላይ “ሉሲፈር” የሚለውን ቃል የሚጠቀሙ ሲሆን፤ ብዙዎች ይህ መጠሪያ ሰይጣን ዲያብሎስ መልአክ በነበረበት ወቅት ይጠራበት የነበረው ስም እንደሆነ ይሰማቸዋል። ሆኖም እዚህ ጥቅስ ላይ የተሠራበት የዕብራይስጥ ቃል ትርጉሙ ‘የሚያበራ ኮከብ’ ማለት ነው። ከጥቅሱ አገባብ መረዳት እንደሚቻለው ይህ አጠራር የሚያመለክተው ሰይጣንን ሳይሆን እብሪተኛ በመሆኑ ምክንያት አምላክ የሚያዋርደውን የባቢሎንን ሥርወ መንግሥት ነው። (ኢሳይያስ 14:4, 13-20) ‘የሚያበራ ኮከብ’ የሚለው አገላለጽ የባቢሎን ሥርወ መንግሥት ከወደቀ በኋላ የሚኖረውን ሁኔታ ለመግለጽ የገባ የምጸት አነጋገር ነው።

b አንዳንዶች ጴጥሮስ ከእስር ቤት ስለወጣበት መንገድ የሚናገረው ታሪክ ጴጥሮስ ጠባቂ መልአክ እንደነበረው የሚጠቁም እንደሆነ ይሰማቸዋል። (የሐዋርያት ሥራ 12:6-16) ሆኖም ደቀ መዛሙርቱ “[የጴጥሮስ] መልአክ” በማለት ሊናገሩ የቻሉት ‘ጴጥሮስ ራሱ ሳይሆን አንድ መልአክ እሱን ወክሎ መጥቷል’ ብለው በስህተት ስላሰቡ ሊሆን ይችላል።