በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ኢየሱስ ምን ይመስል ነበር?

ኢየሱስ ምን ይመስል ነበር?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 መጽሐፍ ቅዱስ የኢየሱስ መልክ ምን ይመስል እንደነበር ስለማይናገር መልኩ ምን ዓይነት እንደነበር በትክክል የሚያውቅ ሰው የለም። ይህም ኢየሱስ ምን ይመስል እንደነበረ ማወቅ ያን ያህል አስፈላጊ እንዳልሆነ ያሳያል። ይሁንና፣ መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ምን ይመስል እንደነበር የሚጠቁም የተወሰነ ፍንጭ ይሰጠናል።

  •   አጠቃላይ ገጽታ፦ ኢየሱስ አይሁዳዊ ነበር፤ በመሆኑም አይሁዳውያን ያሏቸውን አንዳንድ ገጽታዎች ከእናቱ ሳይወርስ አይቀርም። (ዕብራውያን 7:14) ከሌሎች ሰዎች የተለየ ዓይነት መልክ የነበረው አይመስልም። እንዲያውም በአንድ ወቅት ከገሊላ እስከ ኢየሩሳሌም ድረስ ማንም ሰው ሳያውቀው በስውር መሄድ ችሎ ነበር። (ዮሐንስ 7:10, 11) በተጨማሪም፣ ከቅርብ ደቀ መዛሙርቱ እንኳ ለየት የሚያደርግ መልክ እንዳልነበረው መረዳት ይቻላል። ኢየሱስን ሊያስሩ የመጡት የጦር መሣሪያ የታጠቁ ሰዎች ኢየሱስ የትኛው እንደሆነ ለማወቅ የአስቆሮቱ ይሁዳ ጥቆማ አስፈልጓቸው እንደነበር አስታውስ።—ማቴዎስ 26:47-49

  •   የፀጉር ርዝመት፦ ኢየሱስ ረጅም ፀጉር የነበረው አይመስልም፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ “ወንድ ፀጉሩን ቢያስረዝም ውርደት እንደሚሆንበት” ይናገራል።—1 ቆሮንቶስ 11:14

  •   ጢም፦ ኢየሱስ ጢሙን ያሳድግ ነበር። ኢየሱስ የአይሁድን ሕግ ይከተል የነበረ ሲሆን፣ ሕጉ እስራኤላውያን ወንዶች ‘የጢማቸውን ዳር ዳር እንዳይላጩ’ ያዝዝ ነበር። (ዘሌዋውያን 19:27፤ ገላትያ 4:4) በተጨማሪም፣ ኢየሱስ ስለሚደርስበት መከራ የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ኢየሱስ ጢም እንደነበረው ይገልጻል።—ኢሳይያስ 50:6

  •   ቁመና፦ ማስረጃዎቹ በሙሉ ኢየሱስ ጠንካራ ሰውነት እንደነበረው ይጠቁማሉ። በአገልግሎቱ ወቅት ረጅም ርቀት ተጉዟል። (ማቴዎስ 9:35) ሁለት ጊዜ የገንዘብ መንዛሪዎችን ጠረጴዛዎች ገለባብጦ ቤተ መቅደሱን አጽድቷል፤ አንዴ ደግሞ ጅራፍ ሠርቶ ከብቶችን አባሯል። (ሉቃስ 19:45, 46፤ ዮሐንስ 2:14, 15) በማክሊንቶክና በስትሮንግ የተዘጋጀው ሳይክሎፒዲያ እንዲህ ይላል፦ “የወንጌል ዘገባዎቹ በሙሉ [ኢየሱስ] ጤናማና ጠንካራ እንደነበር ይጠቁማሉ።”—ጥራዝ 4፣ ገጽ 884

  •   የፊቱ ገጽታ፦ ኢየሱስ አፍቃሪና ሩኅሩኅ ሰው ነበር፤ በመሆኑም የፊቱ ገጽታ ይህን ማንጸባረቁ እንደማይቀር ግልጽ ነው። (ማቴዎስ 11:28, 29) ሁሉም ዓይነት ሰዎች ማጽናኛና እርዳታ ለማግኘት ወደ እሱ ይመጡ ነበር። (ሉቃስ 5:12, 13፤ 7:37, 38) ትንንሽ ልጆች እንኳ ከእሱ ጋር መሆን ያስደስታቸው ነበር።—ማቴዎስ 19:13-15፤ ማርቆስ 9:35-37

ብዙዎች ስለ ኢየሱስ መልክ ያላቸው የተሳሳተ አመለካከት

 የተሳሳተ አመለካከት፦ አንዳንድ ሰዎች፣ የራእይ መጽሐፍ የኢየሱስን ፀጉር ከሱፍ፣ እግሮቹን ደግሞ ከጋለ መዳብ ጋር ስለሚያመሳስለው ኢየሱስ አፍሪካዊ ይመስል ነበር ማለት ነው ብለው ይናገራሉ።—ራእይ 1:14, 15

 እውነታው፦ የራእይ መጽሐፍ “በምልክቶች” የቀረበ ነው። (ራእይ 1:1) ስለ ኢየሱስ ፀጉርና እግር የተሰጠው መግለጫ ኢየሱስ ትንሣኤ ካገኘ በኋላ ስላሉት ባሕርያት ለመግለጽ የተጠቀሰ ምሳሌ እንጂ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት የነበረውን መልክ አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ አይደለም። ራእይ 1:14 የኢየሱስ “ራሱና ፀጉሩ እንደ ነጭ ሱፍ፣ እንደ በረዶም ነጭ” እንደሆነ ይናገራል፤ ጥቅሱ ለንጽጽር የተጠቀመው ቀለምን እንጂ የፀጉርን ልስላሴ አይደለም። ይህ ለረጅም ዘመን ያካበተው ጥበብ እንዳለው ለማመልከት የተጠቀሰ ሐሳብ ነው። (ራእይ 3:14) ይህ ጥቅስ የኢየሱስን ፀጉር ልስላሴ ከበረዶ ጋር እያመሳሰለ እንዳልሆነ ሁሉ ሱፍም የተጠቀሰው የኢየሱስን ፀጉር ልስላሴ ከሱፍ ጋር ለማወዳደር አይደለም።

 የኢየሱስ እግሮች ‘እቶን ውስጥ የጋለ የጠራ መዳብ’ ይመስሉ ነበር። (ራእይ 1:15) እንዲሁም ፊቱ “በሙሉ ድምቀቱ እንደሚያበራ ፀሐይ ነበር።” (ራእይ 1:16) በምድር ላይ የትኛውም ዘር እዚህ ላይ የተጠቀሰውን ዓይነት ቀለም ሊኖረው አይችልም፤ ስለዚህ ይህ ራእይ ከሞት የተነሳው ኢየሱስ “ሊቀረብ በማይችል ብርሃን ውስጥ” እንደሚኖር ለማሳየት ተብሎ የታየ ምሳሌያዊ ራእይ መሆን አለበት።—1 ጢሞቴዎስ 6:16

 የተሳሳተ አመለካከት፦ ኢየሱስ ከሲታና ደካማ ነበር።

 እውነታው፦ ኢየሱስ ወንዳ ወንድ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ሊያስሩት በመጡት መሣሪያ የታጠቁ ሰዎች ፊት ማንነቱን በድፍረት ተናግሯል። (ዮሐንስ 18:4-8) እንዲሁም የጉልበት ሥራ በሚጠይቀው በአናጺነት ሙያ ተሠማርቶ ነበር፤ ይህ ደግሞ ጠንካራ ሰውነት ያለው ሰው እንደነበረ ይጠቁማል።—ማርቆስ 6:3

 ታዲያ ኢየሱስ የመከራ እንጨቱን ለመሸከም እርዳታ ያስፈለገው ለምን ነበር? እንዲሁም፣ አብረውት ከተሰቀሉት ሌሎች ሰዎች ቀድሞ የሞተውስ ለምንድን ነው? (ሉቃስ 23:26፤ ዮሐንስ 19:31-33) ኢየሱስ ከመሰቀሉ በፊት ሰውነቱ በጣም ተዳክሞ ነበር። ሌሊቱን ሙሉ ሳይተኛ ነበር ያደረው፤ ይህ የሆነው በከፍተኛ ጭንቀት ተውጦ ስለነበር ሳይሆን አይቀርም። (ሉቃስ 22:42-44) ሌሊቱን አይሁዳውያን ሲያሠቃዩት አደሩ፤ በማግስቱ ጠዋት ደግሞ ሮማውያን ሲገርፉት ነበር። (ማቴዎስ 26:67, 68፤ ዮሐንስ 19:1-3) የኢየሱስን ሞት ያፋጠኑት እነዚህ ነገሮች ሳይሆኑ አይቀሩም።

 የተሳሳተ አመለካከት፦ ኢየሱስ ሁልጊዜ ኮስታራና የሚተክዝ ሰው ነበር።

 እውነታው፦ ኢየሱስ የሰማይ አባቱን ይሖዋን ሙሉ በሙሉ ይመስለዋል፤ መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ ይሖዋ ‘ደስተኛ አምላክ’ እንደሆነ ይናገራል። (1 ጢሞቴዎስ 1:11፤ ዮሐንስ 14:9) እንዲያውም ኢየሱስ፣ ደስተኛ መሆን የሚቻልበትን መንገድ ለሰዎች አስተምሯቸዋል። (ማቴዎስ 5:3-9፤ ሉቃስ 11:28) እነዚህ ማስረጃዎች በኢየሱስ ፊት ላይ በአብዛኛው ደስታ ይነበብ እንደነበረ ይጠቁማሉ።