በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የአምላክ መንግሥት በሰዎች ልብ ውስጥ ያለ ነገር ነው?

የአምላክ መንግሥት በሰዎች ልብ ውስጥ ያለ ነገር ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 አይደለም፤ የአምላክ መንግሥት በክርስቲያኖች ልብ ውስጥ ያለ ሁኔታን የሚያመለክት ነገር አይደለም። a መጽሐፍ ቅዱስ ይህን መንግሥት “መንግሥተ ሰማያት” ብሎ በመጥራት የት እንደሚገኝ በግልጽ አስቀምጦታል። (ማቴዎስ 4:17) የአምላክ መንግሥት በሰማይ ሆኖ የሚገዛ እውን የሆነ መስተዳድር ነው የምንለው ለምን እንደሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ እንመልከት።

  •   የአምላክ መንግሥት ገዢዎች፣ ተገዢዎችና ሕጎች ያሉት ሲሆን የአምላክ ፈቃድ በሰማይ እና በምድር እንዲፈጸም የማድረግ ሥራ ተሰጥቶታል።—ማቴዎስ 6:10፤ ራእይ 5:10

  •   የአምላክ መንግሥት “በልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች፣ መንግሥታትና ሕዝቦች” የሚገዙለት መንግሥት ነው። (ዳንኤል 7:13, 14) የመግዛት ሥልጣኑን ያገኘው ከተገዢዎቹ ሳይሆን ከአምላክ ነው።—መዝሙር 2:4-6፤ ኢሳይያስ 9:7

  •   ኢየሱስ፣ ታማኝ ሐዋርያቱ በሰማይ ባለው መንግሥቱ አብረውት እንደሚሆኑና በዚያም ‘በዙፋን እንደሚቀመጡ’ ነግሯቸዋል።—ሉቃስ 22:28, 30

  •   ይህ መንግሥት ጠላቶች ያሉት ሲሆን ወደፊት እነዚህን ጠላቶቹን ያጠፋቸዋል።—መዝሙር 2:1, 2, 8, 9፤ 110:1, 2፤ 1 ቆሮንቶስ 15:25, 26

 መንግሥተ ሰማያት በሰው ልብ ውስጥ የሚገኝ ነገር እንደሆነ እንዲሁም የሚገዛው በግለሰቡ ልብ አማካኝነት እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ አያስተምርም። ይሁን እንጂ ‘የመንግሥቱ ቃል’ ወይም “የመንግሥቱ ምሥራች” በልባችን ውስጥ ሊያድር እንደሚችል እንዲያውም በልባችን ውስጥ እንዲያድር ማድረግ እንዳለብን መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል።—ማቴዎስ 13:19፤ 24:14

ኢየሱስ “የአምላክ መንግሥት በውስጣችሁ ነው” ሲል ምን ማለቱ ነበር?

 አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች (ለምሳሌ፣ ኪንግ ጄምስ ቨርዥን) ሉቃስ 17:21ን “የአምላክ መንግሥት በውስጣችሁ ነው” በማለት አስቀምጠውታል። በመሆኑም አንዳንድ ሰዎች ይህ ሐሳብ የአምላክ መንግሥት ስለሚገኝበት ቦታ ግራ እንዲጋቡ አድርጓቸዋል። ይህን ጥቅስ በትክክል ለመረዳት በመጀመሪያ የጥቅሱን ዐውድ እንመልከት።

የአምላክ መንግሥት ዓመፀኛና ነፍሰ ገዳይ በሆኑት የኢየሱስ ተቃዋሚዎች ልብ ውስጥ ሊገኝ አይችልም

 ኢየሱስ ይህን ሐሳብ የተናገረው ለፈሪሳውያን ነው፤ ፈሪሳውያን ደግሞ ኢየሱስን የሚቃወሙና እሱን ለማጥፋት እያሴሩ የነበሩ የሃይማኖት መሪዎች ናቸው። (ማቴዎስ 12:14፤ ሉቃስ 17:20) ታዲያ የአምላክ መንግሥት በእነዚህ ዓመፀኛ ሰዎች ልብ ውስጥ ያለውን ሁኔታ የሚያመለክት ሊሆን ይችላል? ኢየሱስ ፈሪሳውያንን “ውስጣችሁ . . . በግብዝነትና በዓመፅ የተሞላ ነው” ብሏቸዋል።—ማቴዎስ 23:27, 28

 በሉቃስ 17:21 ላይ የሚገኘውን የኢየሱስ ሐሳብ በትክክል ያስቀመጡ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች አሉ፦ “የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ናት።” (በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን፤ አዲሱ መደበኛ ትርጉም) “የአምላክ መንግሥት በመካከላችሁ ነው።” (አዲስ ዓለም ትርጉም) መንግሥተ ሰማያት በፈሪሳውያን ‘መካከል’ እንደሆነ የተገለጸው የዚህ መንግሥት ንጉሥ እንዲሆን በአምላክ የተሾመው ኢየሱስ በመካከላቸው ቆሞ ስለነበር ነው።—ሉቃስ 1:32, 33

a ብዙ የክርስትና ሃይማኖቶች፣ የአምላክ መንግሥት በአንድ ግለሰብ ውስጥ ወይም በልቡ ውስጥ የሚገኝ ነገር እንደሆነ ያስተምራሉ። ለምሳሌ ያህል በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኝ አንድ የክርስትና ሃይማኖት፣ የአምላክ መንግሥት በአንድ በኩል “አምላክ በአንድ ሰው ልብና ሕይወት ላይ መንገሡን የሚያመለክት ሁኔታ” እንደሆነ ያስተምራል። በተመሳሳይም የሮም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የሆኑት ቤነዲክት 16ኛ፣ የናዝሬቱ ኢየሱስ (እንግሊዝኛ) በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ “የአምላክ መንግሥት የሚመጣው ታዛዥ በሆነ ልብ በኩል ነው” በማለት ገልጸዋል።