በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የይሖዋ ምሥክሮች በብሉይ ኪዳን ያምናሉ?

የይሖዋ ምሥክሮች በብሉይ ኪዳን ያምናሉ?

 አዎ። የይሖዋ ምሥክሮች መላው መጽሐፍ ቅዱስ ‘በአምላክ መንፈስ መሪነት እንደተጻፈና ጠቃሚ’ እንደሆነ ያምናሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) ይህ ደግሞ በተለምዶ ብሉይ ኪዳን እና አዲስ ኪዳን ተብለው የሚጠሩትን ክፍሎች ይጨምራል። አብዛኛውን ጊዜ፣ የይሖዋ ምሥክሮች እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትና የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት በማለት ይጠሯቸዋል። ይህም አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ጊዜ እንዳለፈባቸው ወይም እንደማይጠቅሙ አድርገን እንደማንመለከታቸው ያሳያል።

ክርስቲያኖች ብሉይ ኪዳንም ሆነ አዲስ ኪዳን የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?

 ክርስቲያኑ ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት “ቀደም ብሎ የተጻፈው ነገር ሁሉ ለእኛ ትምህርት እንዲሆን ተጽፏል” ብሏል። (ሮም 15:4) በመሆኑም በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ አስፈላጊ መረጃ እናገኛለን። ለምሳሌ ያህል፣ መጻሕፍቱ ጠቃሚ የሆኑ ታሪኮችንና ምክሮችን ይዘዋል።

  •   ጠቃሚ የሆኑ ታሪኮች። የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ስለ ፍጥረት እንዲሁም የሰው ዘር በኃጢአት የወደቀው እንዴት እንደሆነ የሚገልጽ ዝርዝር ዘገባ ይዘዋል። ይህ መረጃ ባይኖረን ኖሮ ለሚከተሉት ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ማግኘት አንችልም ነበር፦ የመጣነው ከየት ነው? ሰዎች የሚሞቱት ለምንድን ነው? (ዘፍጥረት 2:7, 17) በተጨማሪም በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ላይ፣ ይሖዋ እንደ እኛ ዓይነት ስሜት ካላቸው ሰዎች ጋር የነበረውን ግንኙነት የሚያሳዩ ታሪኮችን ማግኘት እንችላለን።​—ያዕቆብ 5:17

  •   ጠቃሚ የሆኑ ምክሮች። የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል የሆኑት የምሳሌና የመክብብ መጻሕፍት ጊዜ የማይሽራቸውና ጥበብ ያዘሉ ምክሮችን ይዘዋል። ለአብነት ያህል፣ አስደሳች የቤተሰብ ሕይወት መምራትና (ምሳሌ 15:17) ለሥራ ተገቢውን አመለካከት መያዝ ስለሚቻልበት መንገድ የሚገልጽ (ምሳሌ 10:4፤ መክብብ 4:6) እንዲሁም ወጣቶች ሕይወታቸውን ከሁሉ በተሻለ መንገድ እንዲጠቀሙበት የሚረዳ (መክብብ 11:9 እስከ 12:1) ምክር ይሰጣሉ።

 በተጨማሪም በቶራ (የመጀመሪያዎቹ አምስት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት) ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኘውን የሙሴን ሕግ በማጥናት ጥቅም ማግኘት እንችላለን። ክርስቲያኖች ይህንን ሕግ እንዲጠብቁ ባይታዘዙም እንኳ በውስጡ ያሉት መመሪያዎች ደስተኛ ሕይወት ለመምራት እንድንችል ይረዱናል።​—ዘሌዋውያን 19:18፤ ዘዳግም 6:5-7