በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የይሖዋ ምሥክሮች ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ የሚሰብኩት መዳን ያስገኝልናል ብለው ነው?

የይሖዋ ምሥክሮች ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ የሚሰብኩት መዳን ያስገኝልናል ብለው ነው?

 አይደለም። አዘውትረን ከቤት ወደ ቤት እንሰብካለን፤ ነገር ግን ይህን ሥራ የምናከናውነው በራሳችን ጥረት መዳን እናገኛለን ብለን ስለምናምን አይደለም። (ኤፌሶን 2:8) ይህን የምንልበት ምክንያት አለን።

 እስቲ የሚከተለውን ንጽጽር ልብ በል፦ አንድ በጣም ደግ የሆነ ሰው፣ እሱ በመረጠው ቦታና ቀን ላይ ለሚገኙ ሰዎች በሙሉ ውድ ስጦታ እንደሚሰጥ ቃል ገባ እንበል። ግለሰቡ ቃሉን እንደሚጠብቅ ከልብ የምታምን ከሆነ እሱ ያዘዘውን ነገር ለማድረግ አትነሳሳም? እንዲህ እንደምታደርግ ምንም ጥርጥር የለውም! እንዲያውም ጓደኞችህና ቤተሰቦችህ በአጋጣሚው እንዲጠቀሙ በማሰብ ሁኔታውን ለእነሱ መንገርህ አይቀርም። ያም ሆኖ ግለሰቡ ያዘዘህን ነገር የምታደርገው ስጦታውን የምታገኘው በራስህ ጥረት እንደሆነ በማሰብ አይደለም። ምንም ይሁን ምን ሰውየው ስጦታውን ለመስጠት አዘጋጅቷል።

 በተመሳሳይም አምላክ፣ እሱን ለሚታዘዙ ሰዎች ሁሉ የዘላለም ሕይወት ለመስጠት ቃል መግባቱን የይሖዋ ምሥክሮች ያምናሉ። (ሮም 6:23) ሌሎችም ከዚህ ዝግጅት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ስለምንፈልግ ስለ እምነታችን ለሌሎች እንናገራለን። ነገር ግን ለሰዎች የምንሰብከው በእኛ ጥረት መዳን እናገኛለን ብለን አይደለም። (ሮም 1:17፤ 3:28) በእርግጥም የትኛውም ሰው ምንም ያህል ጥረት ቢያደርግ በራሱ ልፋት ይህን አስደናቂ በረከት ከአምላክ ማግኘት አይችልም። ‘የዳንነው እኛ በሠራነው የጽድቅ ሥራ ሳይሆን በአምላክ ምሕረት ነው።’—ቲቶ 3:5