በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል—ጋያና

ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል—ጋያና

 “ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ማገልገል የሚያስገኘውን ደስታ ለመግለጽ ቃላት ያጥረኛል!” ይህን የተናገረው በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖረው ጆሹዋ ነው፤ ጆሹዋ በጋያና ለተወሰነ ጊዜ አገልግሏል። በደቡብ አሜሪካ በምትገኘው በዚህች ፍሬያማ አገር ያገለገሉ ሌሎች በርካታ ወንድሞችም ተመሳሳይ ስሜት አላቸው። a እኛስ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ከሚያገለግሉ ወንድሞች ምን ትምህርት እናገኛለን? በውጭ አገር ለማገልገል የምትፈልግ ከሆነ ከእነዚህ ወንድሞች የምታገኘው ትምህርት እንዴት ሊረዳህ ይችላል?

ያነሳሳቸው ምንድን ነው?

ላይነል

 ላይነል የተባለ አንድ ወንድም ወደ ጋያና ከመዛወሩ በፊት በአገሩ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በሚገኝ እምብዛም ያልተሰበከበት አንድ ክልል አገልግሎ ነበር። ላይነል እንዲህ ብሏል፦ “20 የምንሆን ወንድሞች እና እህቶች ዌስት ቨርጂኒያ በሚገኝ ገጠራማ ክልል ውስጥ እንድናገለግል ተመደብን። በእነዚያ ሁለት ሳምንታት የነበረኝ የአገልግሎት እንቅስቃሴ እንዲሁም ከወንድሞችና ከእህቶች ጋር ያሳለፍኩት አስደሳች ጊዜ በሕይወቴ ላይ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል። አቅሜ በፈቀደ መጠን ይሖዋን በተሟላ ሁኔታ ለማገልገል ቁርጥ ውሳኔ እንዳደርግ አነሳስቶኛል።”

ኤሪካ እና ጋርት

 ጋርት እና ኤሪካ የተባሉ ባልና ሚስት በውጭ አገር ስለማገልገል በደንብ ሲያስቡ ከቆዩ በኋላ ወደ ጋያና ለመሄድ ወሰኑ። ኤሪካ ምክንያቱን ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “እኔና ባለቤቴ ወደ ጋያና ተዛውረው የሚያገለግሉ ባልና ሚስት እናውቅ ነበር። ለአገልግሎታቸው ያላቸው ቅንዓትና ፍቅር እኛም ወደዚያ እንድንሄድ አነሳስቶናል።” ኤሪካ እና ጋርት በዚህ “አስደሳች ምድብ” ለሦስት ዓመታት ቆይተዋል። ጋርት “የውጭ አገር አገልግሎትን ቀምሰን ጥሩ መሆኑን አይተናል” በማለት ተናግሯል። ከጊዜ በኋላ እሱና ባለቤቱ በጊልያድ ትምህርት ቤት የተካፈሉ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በቦሊቪያ እያገለገሉ ነው።

በሌላ አገር የሚያገለግሉ ክርስቲያኖች ግሩም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት የማድረግ አጋጣሚ ያገኛሉ

ዝግጅት ያደረጉት እንዴት ነው?

 መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወታችንን ቀላል እንድናደርግ ያበረታታናል። (ዕብራውያን 13:5) በተጨማሪም በሕይወታችን ውስጥ ትልቅ ውሳኔ ከማድረጋችን በፊት ወጪያችንን እንድናሰላ ይመክረናል። (ሉቃስ 14:26-33) ይህ ምክር ወደ ውጭ አገር ተዛውሮ ከማገልገል ጋር በተያያዘም ይሠራል። ጋርት እንዲህ ብሏል፦ “እኔና ኤሪካ ወደ ጋያና ከመሄዳችን በፊት ኑሯችንን ማቅለል አስፈልጎናል። ለዚህም ሲባል ድርጅታችንን፣ ቤታችንንና የማንጠቀምባቸውን ቁሶቁሶች መሸጥ ነበረብን። ይህን ለማድረግ የተወሰኑ ዓመታት ወስዶብናል። በዚህ መሃል ግን በጋያና የማገልገል ፍላጎታችን እንዳይጠፋ እንጠነቀቅ ነበር፤ ለዚህም ሲባል ሁልጊዜ ግባችንን በአእምሯችን እንይዝ እንዲሁም በየዓመቱ ወደ ጋያና እንሄድ ነበር።”

ሺኔድ እና ፖል

 ሌላው አሳሳቢ ነገር ደግሞ የገቢ ጉዳይ ነው። ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ የሚያገለግሉ አንዳንድ ሰዎች የሚያገለግሉበት አገር ሕግ የሚፈቅድላቸው ከሆነ በዚያው አገር ሥራ ይሠራሉ። አንዳንዶች በአገራቸው ይሠሩ የነበሩትን ሥራ በኢንተርኔት አማካኝነት መሥራታቸውን ይቀጥላሉ። ሌሎች ደግሞ ለተወሰነ ጊዜ ወደ አገራቸው ተመልሰው በመሥራት ገንዘብ ያጠራቅማሉ። ለምሳሌ ፖልና ሺኔድ የተባሉ ባልና ሚስት በዓመት አንዴ ወደ አየርላንድ ተመልሰው ይሠሩ ነበር። በዚህ መልኩ ለ18 ዓመታት በጋያና ማገልገል ችለዋል፤ እንዲያውም ሰባቱን ዓመታት ያገለገሉት ልጅ ከወለዱ በኋላ ነው።

ክሪስቶፈር እና ሎሪሳ

 መዝሙር 37:5 “መንገድህን ለይሖዋ አደራ ስጥ፤ በእሱ ታመን፤ እሱም ለአንተ ሲል እርምጃ ይወስዳል” ይላል። በዩናይትድ ስቴትስ ይኖሩ የነበሩት ክሪስቶፈርና ሎሪሳ በውጭ አገር ለማገልገል ያላቸውን ግብ አስመልክቶ አዘውትረው ይጸልዩ ነበር። በተጨማሪም ወደ ውጭ አገር ለመዛወር ምን ማድረግ እንደሚያስፈልጋቸው እንዲሁም መዛወራቸው ያለውን መልካም ጎንና ተፈታታኝ ሁኔታ በቤተሰብ አምልኳቸው ወቅት ይወያዩ ነበር። እንዲሁም አዲስ ቋንቋ መማር እንዳያስፈልጋቸው በዋነኝነት እንግሊዝኛ የሚነገርበትን ጋያናን መረጡ።

 ቀጥሎም በምሳሌ 15:22 ላይ የሚገኘውን “መመካከር ከሌለ የታቀደው ነገር ሳይሳካ ይቀራል፤ በብዙ አማካሪዎች ግን ይሳካል” የሚለውን ምክር ተግባራዊ አደረጉ። ስላሉበት ሁኔታና በጋያና ለማገልገል ያላቸውን ፍላጎት በመግለጽ በጋያና የሚከናወነውን ሥራ ለሚከታተለው ቅርንጫፍ ቢሮ ጻፉ። b እንዲሁም በአገሪቱ ስላለው የሕክምና ሁኔታ፣ ስለ አየሩ ጠባይና ስለ ባሕሉ ጠየቁ። ቅርንጫፍ ቢሮው ጥያቄያቸውን የመለሰላቸው ሲሆን በሚሄዱበት ቦታ የሚገኙትን ሽማግሌዎች አድራሻ ሰጣቸው።

 ቀደም ሲል የተጠቀሰው ላይነል በጋያና ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኖ እያገለገለ ነው። እሱም ወደ ጋያና ከመሄዱ በፊት በምሳሌ 15:22 ላይ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ አድርጎ ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “ወደዚያ ለመሄድ ገንዘብ ከማጠራቀም በተጨማሪ በሌሎች አገሮች ያገለገሉ ሰዎችን አነጋገርኩ። ጉዳዩን ከቤተሰቤ፣ ከጉባኤያችን ሽማግሌዎችና ከወረዳ የበላይ ተመልካቻችን ጋር ተወያየሁበት። እንዲሁም ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ማገልገልን በተመለከተ በጽሑፎቻችን ላይ የወጡትን ሐሳቦች በሙሉ አንብቤያለሁ።”

ጆሴፍ እና ክርስቲና

 በውጭ አገር ለማገልገል የሚፈልጉ ብዙ ክርስቲያኖች ሊሄዱ ያሰቡበትን አገር በቅድሚያ ይጎበኛሉ፤ ይህም የጥበብ እርምጃ ነው። ጆሴፍና ክርስቲና የተባሉ ባልና ሚስት እንዲህ ብለዋል፦ “ለመጀመሪያ ጊዜ ጋያና ስንሄድ በዚያ ለሦስት ወር ቆይተን ነበር። ይህም ስለ አገሪቱ ለማወቅ አስችሎናል። ከዚያም ወደ አገራችን ተመልሰን ሁኔታዎችን ካመቻቸን በኋላ ወደ ጋያና ተዛወርን።”

አካባቢውን የለመዱት እንዴት ነው?

ጆሹዋ

 ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት አገር የሚያገለግሉ ክርስቲያኖች በአገልግሎታቸው ስኬታማ ለመሆን የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ማሳየት እንዲሁም የአካባቢውን ሁኔታና ባሕል ለመልመድ ፈቃደኛ መሆን ይጠበቅባቸዋል። ለምሳሌ ቀዝቀዝ ካለ አካባቢ ወደ ሞቃታማ አካባቢ የሚዛወሩ ሰዎች በቤታቸው ብዙ ዓይነት ነፍሳት ሊገጥማቸው ይችላል። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ጆሹዋ እንዲህ ብሏል፦ “እንደዚህ ብዙ ነፍሳት ባሉበት አካባቢ ኖሬ አላውቅም፤ ደግሞ በጋያና ያሉት ነፍሳት ትላልቅ ናቸው! ከጊዜ በኋላ ግን ለመድኳቸው። እንዲሁም ቤቴን በንጽሕና ከያዝኩ ነፍሳት ያን ያህል እንደማይበዙ ተገነዘብኩ። ይህም ዕቃ ማጠብን፣ ቆሻሻ ማውጣትንና ቤቱን አዘውትሮ ማጽዳትን ይጨምራል።”

 በሌላ አገር ያለውን ሕይወት መልመድ አዳዲስ የምግብ ዓይነቶችን መብላትንና አዘገጃጀታቸውን መማርንም ሊጠይቅ ይችላል። ጆሹዋ እንዲህ ብሏል፦ “እኔና አብሮኝ የሚኖረው ወንድም በአካባቢው የተለመዱ ምግቦች እንዴት እንደሚዘጋጁ እንዲያሳዩን ወንድሞችንና እህቶችን እንጠይቃቸው ነበር። አዲስ ዓይነት ምግብ ማብሰል ስንማር አንዳንድ የጉባኤውን አባላት እንጋብዝ ነበር። ይህም ከወንድሞች ጋር ይበልጥ ለመተዋወቅና ወዳጅነት ለመመሥረት ረድቶናል።”

ፖል እና ካትሊን

 ፖልና ካትሊን የአካባቢውን ባሕል አስመልክቶ እንዲህ ብለዋል፦ “በአካባቢው ተገቢ የሚባለውን ሥነ ምግባርና አለባበስ መልመድ አስፈልጎን ነበር፤ ይህ ለእኛ አዲስ ነገር ነው። ስለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች እስካልተጣሱ ድረስ ትሑት ሆነን ማስተካከያ ማድረግ ነበረብን። ባሕሉን መልመዳችን ከጉባኤው ጋር አቀራርቦናል እንዲሁም በአገልግሎታችን መልካም ውጤት አስገኝቶልናል።”

ምን ጥቅም አግኝተዋል?

 ጆሴፍና ክርስቲና እንዲህ ብለዋል፦ “ያገኘነው በረከት ካጋጠመን ችግር በእጅጉ የላቀ ነው። አዲስ ነገር መሞከራችን ቅድሚያ በምንሰጣቸው ነገሮች ረገድ ማስተካከያ እንድናደርግ ረድቶናል። ቀደም ሲል በጣም አስፈላጊ ናቸው ብለን የምናስባቸው ነገሮች ያን ያህል አስፈላጊ እንዳልሆኑ ተረድተናል። ያገኘናቸው ተሞክሮዎች ይሖዋን ለማገልገል የቻልነውን ሁሉ ማድረጋችንን እንድንቀጥል አነሳስተውናል። በሕይወታችን እውነተኛ እርካታ አግኝተናል።” ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ የሚያገለግሉ ብዙ ክርስቲያኖችም የጆሴፍንና የክርስቲናን ሐሳብ ይጋራሉ።

 ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ኤሪካ እንዲህ ብላለች፦ “እኔና ባለቤቴ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ማገልገላችን በይሖዋ መታመን ሲባል ምን ማለት እንደሆነ አስተምሮናል። ከዚህ በፊት አይተን በማናውቀው መንገድ የይሖዋን እጅ ማየት ችለናል። ደግሞም አዳዲስ ነገሮችን አብረን መሞከራችን ትዳራችንን አጠናክሮታል።”

a በጋያና የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ታሪክ በ2005 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ (እንግሊዝኛ) ላይ ይገኛል።

b በጋያና የሚከናወነውን ሥራ የሚከታተለው የትሪኒዳድ እና ቶቤጎ ቅርንጫፍ ቢሮ ነው።