በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

“ይሖዋን ለማገልገል አቅሜ የፈቀደውን ሁሉ አደርጋለሁ”

“ይሖዋን ለማገልገል አቅሜ የፈቀደውን ሁሉ አደርጋለሁ”

 በጀርመን የሚኖሩት ኢርማ የተባሉ ሴት፣ ዕድሜያቸው ወደ 90 ዓመት ተጠግቷል። ሁለት ከባድ አደጋዎች ስለደረሱባቸውና በርካታ ቀዶ ጥገናዎች ስላደረጉ እንደቀድሞው ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ መስበክ አይችሉም። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ስለ እምነታቸው የሚናገሩት ለዘመዶቻቸውና ለሚያውቋቸው ሰዎች ደብዳቤ በመጻፍ ነው። ኢርማ የሚጽፏቸው የሚያበረታቱ ደብዳቤዎች ብዙዎችን አጽናንተዋል፤ እንዲያውም እነዚህ ደብዳቤዎች የሚደርሷቸው ሰዎች በተደጋጋሚ ስልክ በመደወል ቀጣዩ ደብዳቤ የሚደርሳቸው መቼ እንደሆነ ይጠይቃሉ። በተጨማሪም ብዙ ሰዎች የምስጋና ደብዳቤዎችን በመጻፍ እንዲህ ያሉ ደብዳቤዎችን መልሰው ማግኘት እንደሚፈልጉ ይገልጻሉ። ኢርማ “እንዲህ ያሉ ምላሾችን ማግኘቴ ደስተኛ እንድሆንና መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችን በንቃት እንዳከናውን ረድቶኛል” በማለት ተናግረዋል።

 ኢርማ በአረጋውያን መንከባከቢያ ተቋማት ውስጥ ላሉ ሰዎችም ደብዳቤ ይጽፋሉ። እንዲህ ብለዋል፦ “ባለቤታቸውን በሞት ያጡ አንዲት በዕድሜ የገፉ ሴት፣ የጻፍኩላቸው ደብዳቤ በጣም እንዳጽናናቸው ደውለው ነገሩኝ። ደብዳቤውን መጽሐፍ ቅዱሳቸው ውስጥ ያስቀመጡት ሲሆን ብዙ ጊዜ ምሽት ላይ ያነብቡታል። በቅርቡ ባለቤታቸው የሞቱባቸው ሌላ ሴትም ከቄሱ ስብከት ይልቅ እኔ የጻፍኩላቸው ደብዳቤ እንዳጽናናቸው ነገሩኝ። እንዲሁም ብዙ ጥያቄዎች ስላሏቸው መጥተው ሊያናግሩኝ እንደሚፈልጉ ገለጹልኝ።”

 ኢርማ የሚያውቋቸው የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ አንዲት ሴት ራቅ ወዳለ ቦታ ሲሄዱ ኢርማን ደብዳቤ እንዲጽፉላቸው ጠይቀዋቸዋል። ኢርማ እንዲህ ብለዋል፦ “ሴትየዋ የጻፍኩላቸውን ደብዳቤዎች በሙሉ አስቀምጠዋቸው ነበር። እሳቸው ከሞቱ በኋላ ልጃቸው ደውላ ለእናቷ የጻፍኳቸውን ደብዳቤዎች በሙሉ እንዳነበበቻቸው ነገረችኝ። ከዚያም ለእሷም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን የያዙ ደብዳቤዎችን ልልክላት እችል እንደሆነ ጠየቀችኝ።”

 ኢርማ በአገልግሎታቸው በጣም ደስተኛ ናቸው። እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል፦ “ይሖዋ እሱን ለማገልገል የሚያስችል ጥንካሬ እንዲሰጠኝ እለምነዋለሁ። ከቤት ወደ ቤት እየሄድኩ መስበክ ባልችልም ይሖዋን ለማገልገል አቅሜ የፈቀደውን ሁሉ አደርጋለሁ።”