በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በሥራ ላይ ያልነበረ የእሳት አደጋ ሠራተኛ የሰዎችን ሕይወት አተረፈ

በሥራ ላይ ያልነበረ የእሳት አደጋ ሠራተኛ የሰዎችን ሕይወት አተረፈ

እሁድ፣ ጥር 5, 2014 ሰርዥ ዤራርዲን ፈረንሳይ ውስጥ በፓሪስ ከተማ አቅራቢያ በሚካሄድ የይሖዋ ምሥክሮች ትልቅ ስብሰባ ላይ ለመገኘት በአውቶብስ እየተጓዘ ነው፤ በጉዞ ላይ ሳለ አንድ አሰቃቂ አደጋ ተመለከተ። እንዲህ በማለት የተፈጠረውን ሁኔታ ተርኳል፦ “አንድ መኪና ድልድዩን ደግፎ ከያዘው ግንብ ጋር ከተጋጨ በኋላ አየር ላይ ተንሳፈፈ። ከዚያም መኪናው ከድልድዩ ጋር ተላተመና በእሳት ተያይዞ በአናቱ መሬት ላይ አረፈ።”

ሰርዥ ከ40 ለሚበልጡ ዓመታት የእሳት አደጋ ሠራተኛ ሆኖ አገልግሏል። የእሳት አደጋ ብርጌድ አዛዥ እንደመሆኑ መጠን ፈጣን እርምጃ ወሰደ። እንዲህ ብሏል፦ “እየተጓዝን የነበረው በተቃራኒው አቅጣጫ ቢሆንም ሹፌሩ መኪናውን እንዲያቆም ጠየቅሁት፤ ከዚያም በእሳት ወደተያያዘው መኪና እየሮጥኩ ሄድኩ።” ሰርዥ “አድኑኝ! አድኑኝ!” የሚል ጩኸት ሰማ። ከዚያ በኋላ የተፈጠረውን ሁኔታ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ሙሉ ልብስና ከረባት ለብሼ ነበር፤ በዚያ ላይ ደግሞ ለደህንነት አስፈላጊ የሆነ ትጥቅ አልያዝኩም። ይሁን እንጂ ሰዎች ሲጮኹ ስሰማ እነሱን ማዳን እንደምችል ተሰማኝ!”

ሰርዥ መኪናውን እየዞረ ሲመለከት ራሱን ሊስት የደረሰ አንድ ተሳፋሪ አየ፤ ከዚያም አደጋው ከደረሰበት ቦታ አራቀው። “ሰውየው ሌሎች ሁለት ሰዎች መኪናው ውስጥ እንዳሉ ነገረኝ” በማለት ሰርዥ ተናግሯል። “በዚህ ጊዜ በርከት ያሉ መኪኖች ቆመው ነበር። ይሁንና ኃይለኛ ሙቀትና እሳት ስለነበር ሰዎች ወደ መኪናው መጠጋት አልቻሉም።”

በርካታ የትላልቅ መኪና ሹፌሮች የእሳት ማጥፊያ ይዘው መጡ። ከዚያም ሰርዥ የሰጣቸውን መመሪያ ተከትለው የእሳት ማጥፊያውን መኪናው ላይ ረጩበት፤ ስለዚህ ለጊዜውም ቢሆን እሳቱ ጠፋ። የመኪናው ሹፌር ከሥር ተቀርቅሮ ነበር። በመሆኑም ሰርዥና አብረውት የነበሩት ሰዎች መኪናውን ብድግ አድርገው ካነሱት በኋላ ሹፌሩን እየጎተቱ አወጡት።

“በዚህ ጊዜ እሳቱ እንደ ድንገት ቡልቅ ብሎ መንደድ ጀመረ!” በማለት ሰርዥ የተፈጠረውን ሁኔታ ገልጿል። ሆኖም በመኪናው ውስጥ የነበረ ሌላ ሰው በመኪና ቀበቶው እንደታሰረ ወደ ታች ተዘቅዝቆ ነበር። በዚህ ወቅት የቆዳ ልብስ የለበሰና በሥራ ላይ ያልነበረ ሌላ የእሳት አደጋ ሠራተኛ መጣ። ሰርዥ እንዲህ ብሏል፦ “መኪናው ሊፈነዳ እንደሆነ ነገርኳቸው፤ ስለዚህ ሰውየውን እጁን ይዘን እየጎተትን ከመኪናው ውስጥ አወጣነው።” አንድ ደቂቃ በማይሞላ ጊዜ ውስጥ መኪናው ፈነዳ።

የእሳት አደጋ ብርጌድ እና የሕክምና ባለሙያዎች ወደ ቦታው ከደረሱ በኋላ አደጋ የደረሰባቸውን ሰዎች የረዱ ከመሆኑም ሌላ እሳቱን አጠፉ። ሰርዥም በአደጋው ምክንያት እጆቹ ቆሳስለው ስለነበር የመጀመሪያ ሕክምና እርዳታ ተሰጠው። ሰርዥ ወደ ስብሰባው ጉዞውን ለመቀጠል ተመልሶ ወደ አውቶብሱ ሲገባ በርካታ ሰዎች ወደ እሱ መጥተው አመሰገኑት።

ሰርዥ እርዳታ ማበርከት በመቻሉ ተደስቷል። እንዲህ ብሏል፦ “በአምላኬ በይሖዋ ፊት የእነዚህን ሰዎች ሕይወት የማዳን ኃላፊነት እንዳለብኝ ተሰምቶኝ ነበር። ደግሞም እነዚህን ሰዎች ማዳን በመቻሌ በጣም ረክቻለሁ።”