በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ አሥር

ለንጹሕ አምልኮ ጥብቅና ቆሟል

ለንጹሕ አምልኮ ጥብቅና ቆሟል

1, 2. (ሀ) የኤልያስ ወገኖች ምን ነገር አጎሳቁሏቸዋል? (ለ) ኤልያስ በቀርሜሎስ ተራራ ላይ ከየትኞቹ ጠላቶቹ ጋር ተፋጠጠ?

ኤልያስ ሕዝቡ ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ሲያዘግም አሻግሮ እየተመለከተ ነው። ገና ጎህ መቅደዱ ቢሆንም እንኳ ሕዝቡ በረሃብና በችግር የተጎሳቆለ መሆኑን በግልጽ ማየት ይቻላል። ለሦስት ዓመት ተኩል የዘለቀው ድርቅ በሕዝቡ ላይ ትልቅ ጠባሳ ጥሏል።

2 ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ከሚጓዙት ሰዎች መካከል በትዕቢት የተወጠሩትና የይሖዋ ነቢይ የሆነውን ኤልያስን ክፉኛ የሚጠሉት 450 የበኣል ነቢያት ይገኙበታል። ንግሥት ኤልዛቤል በርካታ የይሖዋ አገልጋዮችን ያስገደለች ቢሆንም ኤልያስ ግን የበኣልን አምልኮ በጽናት ከመቃወም ወደኋላ አላለም። ግን እስከ መቼ? እነዚያ የበኣል ካህናት አንድ ሰው ብቻውን ሊቋቋማቸው እንደማይችል ሆኖ ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል። (1 ነገ. 18:4, 19, 20) ንጉሥ አክዓብም ለነገሥታት በተዘጋጀው ሠረገላው ወደ ተራራው መጥቷል። እሱም ቢሆን ኤልያስን አይወደውም።

3, 4. (ሀ) ኤልያስ ወሳኝ የሆነው ቀን ሊጠባ ሲል ፍርሃት ሳያድርበት አይቀርም የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

3 ብቸኛ የሆነው ይህ ነቢይ በዚያን ቀን በሕይወቱ አጋጥሞት የማያውቅ አንድ አስደናቂ ክንውን ሊመለከት ነው። ኤልያስ በአምላክና ክፉ በሆኑ ኃይሎች መካከል ከዚያ በፊት ታይቶ የማያውቅ አስደናቂ ግድድር የሚካሄድበት መድረክ ሲዘጋጅ ይመለከታል። ኤልያስ ጎህ መቅደድ ሲጀምር ምን ተሰምቶት ይሆን? ኤልያስ “እንደ እኛው ዓይነት ስሜት ያለው ሰው” ስለሆነ ፍርሃት ሳያድርበት አይቀርም። (ያዕቆብ 5:17ን አንብብ።) ሌላው ቢቀር፣ እምነት የለሽ በሆነው ሕዝብ፣ በከዳተኛ ንጉሣቸውና እሱን ከመግደል ወደኋላ በማይሉት የበኣል ነቢያት መከበቡ የብቸኝነት ስሜት እንዳሳደረበት ምንም ጥርጥር የለውም።—1 ነገ. 18:22

4 የሆነ ሆኖ እስራኤላውያንን ወደዚህ ችግር የመራቸው ምን ነበር? ይህን ታሪክ ማወቅህስ ለአንተ ምን ጥቅም አለው? ኤልያስ እምነት በማሳየት ረገድ ምን ምሳሌ እንደተወልን እንዲሁም በዛሬው ጊዜ ምሳሌውን መከተላችን ምን ጥቅም እንደሚያስገኝልን እስቲ እንመልከት።

ለረጅም ጊዜ የዘለቀው ግድድር ወደ መደምደሚያው ደረሰ

5, 6. (ሀ) በእስራኤል ውስጥ ምን ዓይነት ግድድር ነበር? (ለ) ንጉሥ አክዓብ ይሖዋን እጅግ ያስቆጣው እንዴት ነው?

5 ኤልያስ በአብዛኛው የሕይወቱ ዘመን፣ የሚኖርበት ምድርም ሆነ የሕዝቡ ማንነት ልዩ መገለጫ የነበረው ንጹሕ አምልኮ ችላ ሲባልና ሲረገጥ ተመልክቷል። በወቅቱ እስራኤል ውስጥ በንጹሕ አምልኮና በሐሰተኛ ሃይማኖት ማለትም ይሖዋ አምላክን በማምለክና በአካባቢያቸው የነበሩት ሕዝቦች የሚያመልኳቸውን ጣዖታት በማምለክ መካከል ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ግድድር ነበር። በኤልያስ ዘመን ይህ ግድድር ይበልጥ ተፋፍሞ ነበር።

6 ንጉሥ አክዓብ ይሖዋን እጅግ የሚያስቆጣ ድርጊት ፈጽሟል። የሲዶን ንጉሥ ልጅ የሆነችውን ኤልዛቤልን አግብቶ ነበር። ኤልዛቤል ደግሞ የበኣልን አምልኮ በእስራኤል ምድር ለማስፋፋትና የይሖዋን አምልኮ ለማጥፋት ቆርጣ ተነስታ ነበር። ብዙም ሳይቆይ አክዓብ በሚስቱ ተጽዕኖ ሥር ወደቀ። ለበኣል ቤተ ጣዖትና መሠዊያ የሠራ ከመሆኑም ሌላ የዚህ ባዕድ አምላክ ቀንደኛ አምላኪ ሆነ።—1 ነገ. 16:30-33

7. (ሀ) የበኣል አምልኮን አስጸያፊ ያደረገው ምንድን ነው? (ለ) በኤልያስ ዘመን የተከሰተው ድርቅ የቆየበትን የጊዜ ርዝመት በተመለከተ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ዘገባ እርስ በርሱ አይጋጭም የምንለው ለምንድን ነው? ( ሣጥኑንም ተመልከት።)

7 የበኣል አምልኮ ይህን ያህል አስጸያፊ የሆነው ለምንድን ነው? አብዛኞቹን ሰዎች ከእውነተኛው አምላክ እንዲርቁ በማባበል እስራኤልን አስቶ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ሰዎች አስጸያፊ ነገሮችንና የጭካኔ ድርጊቶችን እንዲፈጽሙ ያበረታታ ነበር። ይህም ወንዶችም ሆኑ ሴቶች በቤተ መቅደስ ውስጥ የሚፈጽሙትን ዝሙት፣ ልቅ የፆታ ብልግናን እንዲሁም ልጆችን መሥዋዕት አድርጎ ማቅረብን ይጨምራል። በዚህም የተነሳ ይሖዋ ድርቅ እንደሚመጣ እንዲነግረው ኤልያስን ወደ አክዓብ የላከው ሲሆን ነቢዩ ድርቁ መቆሙን እስኪናገር ድረስ የድርቁ ወቅት ይቀጥላል። (1 ነገ. 17:1) ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ኤልያስ ወደ አክዓብ ሄዶ ሕዝቡንና የበኣልን ነቢያት ወደ ቀርሜሎስ ተራራ እንዲሰበስብ ነገረው። *

የበኣል አምልኮ ዋነኛ ገጽታዎች በዛሬው ጊዜም በስፋት ይገኛሉ ሊባል ይችላል

8. ስለ በኣል አምልኮ የሚናገረው ይህ ዘገባ ለእኛ ምን ትርጉም አለው?

8 ይሁንና ይህ ግድድር ለእኛ ምን ትርጉም ይኖረዋል? አንዳንዶች በአሁኑ ጊዜ የበኣል ቤተ ጣዖቶችና መሠዊያዎች ስለሌሉ ስለ በኣል አምልኮ የሚናገረው ታሪክ ለእኛ ጥቅም የለውም ብለው ያስቡ ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህ ዘገባ እንዲያው በታሪክነት እንዲወሳ ብቻ ተብሎ የተጻፈ አይደለም። (ሮም 15:4) “በኣል” የሚለው ቃል “ባለቤት” ወይም “ጌታ” የሚል ፍቺ አለው። ይሖዋ ሕዝቡ እሱን እንደ “በኣል” ወይም እንደ ባለቤት አድርገው እንዲመለከቱት ነግሯቸዋል። (ኢሳ. 54:5) በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ሰዎች ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ ሳይሆን ሌሎች የተለያዩ ጌቶችን እያገለገሉ ነው ቢባል አትስማማም? እውነት ነው፣ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ ዋነኛውን ቦታ የሚሰጡት ለገንዘብ፣ ለሰብዓዊ ሥራ፣ ለመዝናኛ ወይም የፆታ ፍላጎትን ለማርካት አሊያም በይሖዋ ምትክ የሚመለኩ ስፍር ቁጥር የሌላቸው አማልክትን ለማምለክ ከሆነ እነዚህ ነገሮች ጌቶቻቸው እንዲሆኑ መርጠዋል ማለት ነው። (ማቴ. 6:24፤ ሮም 6:16ን አንብብ።) የበኣል አምልኮ ዋነኛ ገጽታዎች በዛሬው ጊዜም በስፋት ይገኛሉ ሊባል ይችላል። በጥንት ዘመን በይሖዋና በበኣል መካከል በነበረው በዚህ ግድድር ላይ ማሰላሰላችን ማንን ማገልገል እንዳለብን በጥበብ እንድንመርጥ ይረዳናል።

‘በሁለት ሐሳብ የዋለሉት’ እንዴት ነበር?

9. (ሀ) የቀርሜሎስ ተራራ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ የበኣልን አምልኮ ምንነት ለማጋለጥ አመቺ ነበር የምንለው ለምንድን ነው? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።) (ለ) ኤልያስ ለተሰበሰበው ሕዝብ ምን ብሎ ተናገረ?

9 አንድ ሰው በቀርሜሎስ ተራራ ላይ ሆኖ ከታላቁ ባሕር (የሜድትራንያን ባሕር) በታች ካለው የቂሶን ወንዝ ሸለቆ አንስቶ በስተ ሰሜን ርቀው እስከሚገኙት የሊባኖስ ተራሮች ድረስ ማየት ይችላል። * ይሁንና በዚህ ወሳኝ ቀን ፀሐይዋ ፍንትው ብላ ስትወጣ የእስራኤልን ምድር የሚያይ ሰው ምድሪቱ በአሳዛኝ ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ ማወቅ አይሳነውም። በአንድ ወቅት በለምነቷ ትታወቅ የነበረችውና ይሖዋ ለአብርሃም ዘሮች የሰጣት ይህች ምድር ተራቁታለች። የአምላክ ሕዝቦች በመረጡት የሞኝነት አካሄድ ምክንያት ምድሪቱ በፀሐይ ሐሩር ተጠብሳለች! ኤልያስ ወደተሰበሰበው ሕዝብ ቀረብ ብሎ “በሁለት ሐሳብ የምትዋልሉት እስከ መቼ ድረስ ነው? እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] አምላክ ከሆነ እግዚአብሔርን [“ይሖዋን፣” NW] ተከተሉ፤ በኣል አምላክ ከሆነም በኣልን ተከተሉ” አላቸው።—1 ነገ. 18:21

10. የኤልያስ ወገን የነበሩት ሰዎች በሁለት ሐሳብ የዋለሉት እንዴት ነበር? የትኛውንስ ሐቅ ዘንግተዋል?

10 ኤልያስ ‘በሁለት ሐሳብ ትዋልላላችሁ’ ሲል ምን ማለቱ ነበር? ሕዝቡ ከይሖዋ አምልኮ ወይም ከበኣል አምልኮ አንዱን መምረጥ እንዳለበት አልተገነዘበም ነበር። ሁለቱንም ማምለክ እንደሚችሉ ማለትም በአንድ በኩል አስጸያፊ የሆኑ ድርጊቶችን በመፈጸም በኣልን ደስ ማሰኘት በሌላ በኩል ደግሞ የይሖዋን እርዳታ መጠየቅ እንደሚችሉ ተሰምቷቸው ነበር። ምናልባትም ይህን ያደረጉት በኣል እርሻቸውንና ከብቶቻቸውን እንደሚባርክላቸው፣ ‘የሰራዊት አምላክ’ የሆነው ይሖዋ ደግሞ በጦርነት እንደሚረዳቸው አስበው ሊሆን ይችላል። (1 ሳሙ. 17:45) እነዚህ ሰዎች አንድ ሐቅ ዘንግተዋል፤ በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ ብዙዎችም ይህን ቁም ነገር አያስተውሉትም። ይሖዋ ለእሱ የሚቀርበውን አምልኮ ማንም እንዲጋራው አይፈልግም። ሰዎች እሱን ብቻ እንዲያመልኩት ይፈልጋል፤ ደግሞም እንዲህ ዓይነት አምልኮ ይገባዋል። ለእሱ የሚቀርበውን አምልኮ ከሌላ ዓይነት አምልኮ ጋር መቀላቀል በእሱ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ከመሆኑም በላይ አስጸያፊ ተግባር ነው!—ዘፀአት 20:5ን አንብብ።

11. ኤልያስ በቀርሜሎስ ተራራ ላይ ያቀረበው ጥሪ በሕይወታችን ውስጥ ቅድሚያ ስለምንሰጣቸው ነገሮችና አምልኳችንን ስለምናቀርብበት መንገድ መለስ ብለን እንድንመረምር የሚያነሳሳን እንዴት ነው?

11 በመሆኑም እስራኤላውያን በአንድ ጊዜ ሁለት ዛፍ ላይ ለመውጣት እንደሚሞክር ሰው ሆነው ነበር። በዛሬው ጊዜም ብዙ ሰዎች ተመሳሳይ ስህተት ይሠራሉ፤ እንደ “በኣል” ያሉ ሌሎች ነገሮች በሕይወታቸው ውስጥ ቦታ እንዲኖራቸው በመፍቀድ ለአምላክ የሚያቀርቡትን አምልኮ ወደ ጎን ገሸሽ አድርገዋል። በመሆኑም ኤልያስ እስራኤላውያን በሁለት ሐሳብ ከመዋለል እንዲቆጠቡ ያቀረበላቸው ጥሪ በሕይወታችን ውስጥ ቅድሚያ ስለምንሰጣቸው ነገሮችና አምልኳችንን ስለምናቀርብበት መንገድ መለስ ብለን እንድንመረምር ያነሳሳናል።

የመጨረሻ ፈተና

12, 13. (ሀ) ኤልያስ ምን ፈተና አቀረበ? (ለ) እኛስ እንደ ኤልያስ ዓይነት እምነት እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

12 በመቀጠል ኤልያስ እውነተኛው አምላክ ማን እንደሆነ ለመለየት የሚያስችል ፈተና አቀረበ። ፈተናው በጣም ቀላል ነበር። የበኣል ካህናት መሠዊያ ይሠሩና በላዩ መሥዋዕት ያስቀምጣሉ፤ ከዚያም መሥዋዕቱን በእሳት እንዲያቃጥል አምላካቸውን ይለምኑታል። ኤልያስም ተመሳሳይ ነገር ያደርጋል። ኤልያስ “በእሳት የሚመልሰውም እርሱ እውነተኛ አምላክ ነው” በማለት ተናገረ። ኤልያስ እውነተኛው አምላክ ማን እንደሆነ አሳምሮ ያውቃል። እጅግ ጠንካራ እምነት ስለነበረውም ተቀናቃኞቹ ቅድሚያውን ወስደው የፈለጉትን እንዲያደርጉ ፈቀደላቸው። በመሆኑም ካህናቱ መሥዋዕት አድርገው የሚያቀርቡትን ወይፈን መረጡ፤ ከዚያም በኣል ፊት ቀረቡ። *1 ነገ. 18:24, 25

13 የምንኖረው ተአምራት በሚፈጸሙበት ዘመን ውስጥ አይደለም። ይሁንና ይሖዋ አልተለወጠም። እኛም ልክ እንደ ኤልያስ በእሱ ልንተማመን እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ ሌሎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጋር የማይስማማ ሐሳብ ቢኖራቸው ፈርተን ሐሳባቸውን እንዳይገልጹ አንከለክላቸውም። ከዚህ ይልቅ ኤልያስ እንዳደረገው ሁሉ እኛም እውነተኛው አምላክ ትክክለኛውን ነገር እንዲያስተውሉ እንዲረዳቸው እናደርጋለን። ይህንንም የምናደርገው በራሳችን ሳይሆን ነገሮችን “ለማቅናት” ተብሎ በመንፈስ መሪነት በተጻፈው ቃሉ በመታመን ነው።—2 ጢሞ. 3:16

ኤልያስ የበኣል አምልኮ እንዲሁ ሰዎችን ለማታለል ተብሎ የተፈጠረ መሆኑን አሳምሮ ስለሚያውቅ የአምላክ ሕዝቦችም የበኣል አምልኮ ሐሰት መሆኑን እንዲያዩ ፈልጎ ነበር

14. ኤልያስ በበኣል ነቢያት ላይ ያፌዘባቸው እንዴት ነበር? ለምንስ?

14 የበኣል ነቢያት መሥዋዕታቸውን አዘጋጅተው አምላካቸውን መጥራት ጀመሩ። “በኣል ሆይ ስማን” በማለት ደጋግመው ጮኹ። በዚህ ሁኔታ ሰዓታት አለፉ። መጽሐፍ ቅዱስ “ድምፅ ግን የለም፤ የሚመልስ አልነበረም” በማለት ይናገራል። እኩለ ቀን ላይ ኤልያስ፣ ‘በኣል ሥራ በዝቶበት ወይም በሐሳብ ተውጦ ሊሆን ይችላል፤ ተኝቶም ከሆነ የሚቀሰቅሰው ሰው ያስፈልገዋል’ እያለ በምጸት በመናገር በካህናቱ ላይ ያፌዝባቸው ጀመር። ኤልያስ እነዚህን ሐሰተኛ ነቢያት “ድምፃችሁን ከፍ አድርጋችሁ ጩኹ እንጂ!” አላቸው። በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ኤልያስ የበኣል አምልኮ እንዲሁ ሰዎችን ለማታለል ተብሎ የተፈጠረ መሆኑን አሳምሮ ስለሚያውቅ የአምላክ ሕዝቦችም የበኣል አምልኮ ሐሰት መሆኑን እንዲያዩ ፈልጎ ነበር።—1 ነገ. 18:26, 27

15. የበኣል ካህናት የገጠማቸው ሁኔታ ከይሖዋ ይልቅ ሌላ አምላክ ለማገልገል መምረጥ ሞኝነት እንደሆነ የሚያሳየው እንዴት ነው?

15 የበኣል ካህናትም ከቁጥጥር ውጭ ሆነው “እየጮኹ እንደ ልማዳቸው ደማቸው እስኪፈስ ድረስ ሰውነታቸውን በሰይፍና በጩቤ ያቈስሉ ነበር።” ይህን ሁሉ ያደረጉት እንዲያው በከንቱ ነበር! “አሁንም ድምፅ የለም፤ የመለሰና ከቁም ነገር የቈጠረውም አልነበረም።” (1 ነገ. 18:28, 29) በእርግጥም በኣል የሚባል አምላክ የለም። ከዚህ ይልቅ ሰይጣን ሰዎችን ከይሖዋ ለማራቅ የፈጠረው የሐሰት አምላክ ነው። ከይሖዋ ይልቅ ሌላ አምላክ ለማገልገል መምረጥ ለሐዘን ብሎም ለውርደት መዳረጉ አይቀሬ ነው።—መዝሙር 25:3ን እና መዝሙር 115:4-8ን አንብብ።

እውነተኛው አምላክ ምላሽ ሰጠ

16. (ሀ) ኤልያስ በቀርሜሎስ ተራራ ላይ የይሖዋን መሠዊያ እንደገና መሥራቱ ሕዝቡ ምን ነገር እንዲያስታውስ አድርጎ ሊሆን ይችላል? (ለ) ኤልያስ በአምላኩ ላይ ከፍተኛ እምነት እንዳለው ያሳየው በምን መንገድ ነው?

16 በመጨረሻም፣ አመሻሹ ላይ ኤልያስ መሥዋዕት የሚያቀርብበት ጊዜ ደረሰ። ኤልያስ ፈርሶ የነበረውን የይሖዋ መሠዊያ በድጋሚ ሠራ፤ ይህን መሠዊያ ያፈረሱት የንጹሕ አምልኮ ጠላቶች ሳይሆኑ አይቀሩም። ኤልያስ መሠዊያውን ለመሥራት 12 ድንጋዮችን የተጠቀመ ሲሆን ይህን ያደረገው አሥሩን ነገዶች ባቀፈው የእስራኤል መንግሥት ውስጥ ያሉት ሰዎች ቀደም ሲል ለ12ቱ የእስራኤል ነገዶች የተሰጠውን ሕግ የመታዘዝ ግዴታ እንዳለባቸው ለማስታወስ ፈልጎ ሊሆን ይችላል። ከዚያም መሥዋዕቱን በመሠዊያው ላይ ካስቀመጠ በኋላ ሁሉም ነገር በውኃ እንዲጥለቀለቅ አደረገ፤ ውኃው የተቀዳው በአቅራቢያው ከነበረው የሜድትራንያን ባሕር ሊሆን ይችላል። ከዚህም ባሻገር በመሠዊያው ዙሪያ ጉድጓድ እንዲቆፈርና በውኃ እንዲሞላ አደረገ። የበኣል ነቢያት የፈለጉትን ሁሉ ለማድረግ የሚያስችል ምቹ አጋጣሚ እንዲያገኙ የፈቀደላቸው ቢሆንም ለራሱ ግን ሁኔታው ይበልጥ ከባድ እንዲሆን አደረገ፤ ይህን ሁሉ ያደረገው በአምላኩ ላይ ከፍተኛ እምነት ስለነበረው ነው።—1 ነገ. 18:30-35

ኤልያስ በጸሎቱ ላይ ይሖዋ የሕዝቡን ‘ልብ እንዲመልስ’ መጠየቁ አሁንም ለእነሱ ምን ያህል እንደሚያስብ ያሳያል

17. ኤልያስ ያቀረበው ጸሎት እሱን በጣም ያሳሰበው ነገር ምን እንደሆነ በግልጽ የሚያሳየው እንዴት ነው? እኛስ በጸሎታችን የእሱን ምሳሌ መከተል የምንችለው በምን መንገድ ነው?

17 ሁሉም ነገር ከተዘጋጀ በኋላ ኤልያስ ጸሎት አቀረበ። በዚህ ወቅት ያቀረበው አጭር ጸሎት እሱን በጣም ያሳሰበው ነገር ምን መሆኑን በግልጽ የሚያሳይ ነበር። በመጀመሪያ ደረጃ፣ “የእስራኤል አምላክ” ይሖዋ እንጂ በኣል አለመሆኑ እንዲታወቅ ፈልጎ ነበር። በሁለተኛ ደረጃ፣ ሁሉም ሰው እሱ የይሖዋ አገልጋይ መሆኑን እንዲረዳና ክብርም ሆነ ምሥጋና ሊሰጥ የሚገባው ለአምላክ መሆኑን እንዲያውቅ ፈልጓል። በመጨረሻም ይሖዋ የሕዝቡን ‘ልብ እንዲመልስ’ በመጠየቅ አሁንም ለእነሱ ምን ያህል እንደሚያስብ አሳይቷል። (1 ነገ. 18:36, 37) ምንም እንኳ እስራኤላውያን እምነት የለሽ መሆናቸው ብዙ ችግሮች ያስከተለ ቢሆንም ኤልያስ ይወዳቸው ነበር። እኛስ ለአምላክ በምናቀርበው ጸሎት የስሙ ጉዳይ እንደሚያሳስበን፣ ትሑቶች እንደሆንና ችግር ላይ ለወደቁ ሰዎች ርኅራኄ እንዳለን ማሳየት እንችል ይሆን?

18, 19. (ሀ) ይሖዋ፣ ኤልያስ ላቀረበው ጸሎት ምላሽ የሰጠው እንዴት ነው? (ለ) ኤልያስ ሕዝቡ ምን እንዲያደርግ አዘዘ? የበኣል ካህናት ምሕረት ሊደረግላቸው አይገባም የምንለው ለምንድን ነው?

18 ኤልያስ ጸሎት ከማቅረቡ በፊት ሕዝቡ ‘ይሖዋም ልክ እንደ በኣል ሐሰተኛ አምላክ ይሆን እንዴ?’ የሚል ጥያቄ ተፈጥሮበት ሊሆን ይችላል። ይሁንና ከጸሎቱ በኋላ እንዲህ ስላለው ነገር ለማሰብ የሚያስችል ጊዜ እንኳ አልነበራቸውም። ዘገባው ስለ ሁኔታው ሲገልጽ “ከዚያም የእግዚአብሔር [“የይሖዋ፣” NW] እሳት ወርዳ መሥዋዕቱን፣ ዕንጨቱን፣ ድንጋዩንና ዐፈሩን ፈጽማ በላች፤ በጕድጓዱ ውስጥ ያለውንም ውሃ ላሰች” ይላል። (1 ነገ. 18:38) እንዴት ያለ አስደናቂ ምላሽ ነው! ታዲያ ሕዝቡ ምን ተሰማው?

‘ከዚያም የይሖዋ እሳት ወረደ’

19 ሕዝቡም ይህን ሲመለከት “አምላክ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] እርሱ እውነተኛ ነው! እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] እርሱ እውነተኛ አምላክ ነው!” በማለት ጮኸ። (1 ነገ. 18:39) በመጨረሻ፣ እውነተኛው አምላክ ማን እንደሆነ ተገነዘቡ። ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን እምነት እንዳላቸው አላሳዩም። እንደ እውነቱ ከሆነ ይሖዋ፣ ኤልያስ ላቀረበው ጸሎት መልስ በመስጠት ከሰማይ እሳት መላኩን ካዩ በኋላ እሱ እውነተኛ አምላክ መሆኑን መናገራቸው እምነት እንደነበራቸው ያሳያል ለማለት አያስደፍርም። በመሆኑም ኤልያስ እምነት እንዳላቸው የሚያሳይ ሌላ ነገር እንዲያደርጉ ጠየቃቸው። ከበርካታ ዓመታት በፊት ሊያደርጉት ይገባ የነበረውን ነገር እንዲፈጽሙ ማለትም የይሖዋን ሕግ እንዲታዘዙ ነገራቸው። የአምላክ ሕግ ሐሰተኛ ነቢያትና ጣዖት አምላኪዎች መገደል እንዳለባቸው ይገልጻል። (ዘዳ. 13:5-9) እነዚህ የበኣል ካህናት የይሖዋ አምላክ ቀንደኛ ጠላቶች የነበሩ ሲሆን የአምላክን ዓላማ ሆን ብለው ይቃወሙ ነበር። ታዲያ እነዚህ ሰዎች ምሕረት ሊደረግላቸው ይገባል? ምንም የማያውቁ ሕፃናትን ከነሕይወታቸው ለበኣል መሥዋዕት ሲያደርጉ ትንሽ እንኳ ርኅራኄ ታይቶባቸው ነበር? (ምሳሌ 21:13ን አንብብ፤ ኤር. 19:5) ስለዚህ እነዚህ ሰዎች ምንም ምሕረት አይገባቸውም! በመሆኑም ኤልያስ የበኣል ነቢያት እንዲገደሉ አዘዘ፤ ደግሞም ተገደሉ።—1 ነገ. 18:40

20. በዛሬው ጊዜ ያሉ አንዳንድ ተቺዎች ኤልያስ በበኣል ካህናት ላይ የወሰደውን የፍርድ እርምጃ በተመለከተ የሚሰማቸው ስጋት መሠረተ ቢስ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

20 በዛሬው ጊዜ ያሉ ተቺዎች በቀርሜሎስ ተራራ የቀረበው ፈተና በዚህ መንገድ መደምደሙ ትክክል እንዳልነበር ይናገራሉ። እንዲያውም አንዳንድ ሰዎች፣ አክራሪዎች በሃይማኖት ስም የሚፈጽሙት ዓመፅ ተቀባይነት እንዳለው ለማስረዳት ይህን ታሪክ እንደ ማስረጃ አድርገው ሊጠቅሱ ይችላሉ የሚል ስጋት አላቸው። በዛሬው ጊዜ ደግሞ የዓመፅ ድርጊት የሚፈጽሙ አክራሪ ሃይማኖታዊ ቡድኖች ተበራክተዋል። ሆኖም ኤልያስ አክራሪ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋን በመወከል የአምላክን የጽድቅ ፍርድ አስፈጽሟል። ከዚህም በላይ፣ በአሁኑ ጊዜ ያሉ እውነተኛ ክርስቲያኖች በክፉዎች ላይ ሰይፍ በማንሳት ኤልያስ የወሰደው ዓይነት እርምጃ ሊወስዱ እንደማይችሉ ያውቃሉ። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ ለጴጥሮስ “ሰይፍህን ወደ ቦታው መልስ፤ ሰይፍ የሚመዙ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ” ሲል በተናገረው ሐሳብ ላይ የሚገኘውን ለሁሉም ደቀ መዛሙርት የሚሆን መመሪያ ይከተላሉ። (ማቴ. 26:52) ወደፊት ይሖዋ በልጁ ተጠቅሞ መለኮታዊውን ፍርድ ያስፈጽማል።

21. በዛሬው ጊዜ ያሉ እውነተኛ ክርስቲያኖች ኤልያስ የተወውን ምሳሌ መከተላቸው ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?

21 አንድ እውነተኛ ክርስቲያን በአምላክ ላይ እምነት እንዳለው በሚያሳይ መንገድ መኖር ይጠበቅበታል። (ዮሐ. 3:16) ይህን ማድረግ የሚቻልበት አንዱ መንገድ ደግሞ እንደ ኤልያስ ያሉ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች የተዉትን የእምነት ምሳሌ መከተል ነው። ኤልያስ ይሖዋን ብቻ ያመለከ ሲሆን ሌሎችም እንዲህ እንዲያደርጉ አበረታቷል። ሰይጣን ሰዎችን ከይሖዋ ለማራቅ የሚጠቀምበት ሃይማኖት ሐሰት መሆኑን በድፍረት አጋልጧል። በራሱ ችሎታ ከመታመንና በገዛ ፍላጎቱ ከመመራት ይልቅ ይሖዋ ነገሮችን እንደሚያስተካክል እምነት ነበረው። በእርግጥም ኤልያስ ለንጹሕ አምልኮ ጥብቅና ቆሟል። እኛም በእምነቱ እንምሰለው!

^ አን.9 የቀርሜሎስ ተራራ ከበታቹ ካለው ባሕር ከሚነፍሰው እርጥበት አዘል አየር በቂ ዝናብና ጠል ስለሚያገኝ አብዛኛውን ጊዜ ለምለም ነበር። በኣል ዝናብ ያዘንባል ተብሎ ይታመን ስለነበር ይህ ተራራ በበኣል አምልኮ ውስጥ ወሳኝ ቦታ እንደነበረው ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። በመሆኑም ባዶና ጠፍ የሆነው የቀርሜሎስ ተራራ የበኣል አምልኮ ሐሰት መሆኑን ለማጋለጥ ተስማሚ ቦታ ነበር።

^ አን.12 ኤልያስ በመሥዋዕቱ ላይ “እሳት አታንድዱበት” ማለቱ ትኩረት የሚስብ ነው። አንዳንድ ምሁራን እንደሚሉት ከሆነ እነዚህ ጣዖት አምላኪዎች አንዳንዴ ከታች ስውር የሆነ ቀዳዳ ያላቸውን መሠዊያዎች በመጠቀም እሳቱ የመጣው ከሰው ኃይል በላይ ከሆነ አካል እንደሆነ ለማስመሰል ይሞክሩ ነበር።