በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ አሥራ አንድ

በንቃትና በትዕግሥት ተጠባብቋል

በንቃትና በትዕግሥት ተጠባብቋል

1, 2. ኤልያስ ደስ የሚያሰኘው ባይሆንም እንኳ ምን ነገር ማከናወን ነበረበት? በኤልያስና በአክዓብ መካከል ምን ልዩነት ነበር?

ኤልያስ ብቻውን ሆኖ በሰማይ ወደሚገኘው አባቱ መጸለይ ፈልጎ ነበር። ሆኖም በዙሪያው የተሰበሰቡት ሰዎች ይህ እውነተኛ ነቢይ እሳት ከሰማይ ሲያወርድ የተመለከቱ ሲሆን ብዙዎቹም በእሱ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት መፈለጋቸው ግልጽ ነው። ኤልያስ ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ጫፍ በመውጣት ለብቻው ሆኖ ወደ ይሖዋ ከመጸለዩ በፊት ደስ የሚያሰኘው ባይሆንም ንጉሥ አክዓብን ማናገር ነበረበት።

2 አክዓብና ኤልያስ ፈጽሞ የተለያዩ ሰዎች ነበሩ። በምርጥ የንጉሥ ልብስ የተንቆጠቆጠው አክዓብ ስስታም ከመሆኑም ሌላ የራሱ አቋም የሌለው ከሃዲ ሰው ነበር። ኤልያስ ደግሞ ከእንስሳት ቆዳ አሊያም ከግመል ወይም ከፍየል ፀጉር የተሠራ ተራ የነቢይ ልብስ ለብሶ ነበር። ይህ ነቢይ በጣም ደፋር ከመሆኑም ሌላ ጽኑ አቋምና እምነት ያለው ሰው ነበር። ቀኑ እየተገባደደ ሲሄድ የሁለቱ ሰዎች ማንነት ይበልጥ ቁልጭ ብሎ ታየ።

3, 4. (ሀ) አክዓብና የበኣል አምላኪዎች የኀፍረት ማቅ የተከናነቡት ለምንድን ነው? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

3 ዕለቱ አክዓብም ሆነ ሌሎች የበኣል አምላኪዎች የኀፍረት ማቅ የተከናነቡበት ቀን ነበር። አክዓብና ሚስቱ ንግሥት ኤልዛቤል አሥሩን ነገዶች ባቀፈው የእስራኤል መንግሥት ውስጥ ያስፋፉት የነበረው አረማዊ እምነት ሐሰት መሆኑ ተረጋግጧል። በኣል አታላይ መሆኑ ተጋልጧል። ይህ በድን የሆነ አምላክ፣ ነቢያቱ እጅግ በመጨነቅ ልመና ቢያቀርቡም፣ ቢጨፍሩም እንዲሁም እንደ ልማዳቸው ደማቸውን ቢያዘሩም የእሳት ብልጭታ እንኳ በመፍጠር ምላሽ መስጠት አልቻለም። በኣል፣ 450 ነቢያቱ የሚገባቸውን ቅጣት እንዳያገኙ ከለላ አልሆናቸውም። ይሁንና ይህ ሐሰተኛ የሆነ አምላክ ሌላም ማድረግ የተሳነው ነገር አለ፤ ይህም በቅርቡ ሙሉ በሙሉ ይፋ ይሆናል። የበኣል ነቢያት ምድሪቱን ያጠቃውን ድርቅ እንዲያቆም ከሦስት ዓመት በላይ አምላካቸውን ሲለማመኑ ቆይተዋል፤ በኣል ግን መልስ መስጠት አልቻለም። በሌላ በኩል ግን ይሖዋ ድርቁ እንዲቆም በማድረግ እውነተኛው አምላክ እሱ መሆኑን በቅርቡ ያሳያል።—1 ነገ. 16:30 እስከ 17:1፤ 18:1-40

4 ይሁንና ይሖዋ ይህን የሚያደርገው መቼ ነው? እስከዚያው ድረስ ኤልያስ ምን ሲያደርግ ይቆይ ይሆን? ከዚህ የእምነት ሰው ምን እንማራለን? ዘገባውን ስንመረምር ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ እናገኛለን።—1 ነገሥት 18:41-46ን አንብብ።

የጸሎት ሰው

5. ኤልያስ ለአክዓብ ምን እንዲያደርግ ነገረው? አክዓብ በዕለቱ ከተከናወኑት ነገሮች ትምህርት አግኝቶ ይሆን?

5 ኤልያስ ወደ አክዓብ ሄዶ፣ “የከባድ ዝናብ ድምፅ ይሰማልና ሂድና ብላ፤ ጠጣም” አለው። ይህ ክፉ ንጉሥ በዕለቱ ከተከናወኑት ነገሮች ትምህርት አግኝቶ ይሆን? ዘገባው ስለዚህ ጉዳይ በቀጥታ ባይናገርም አክዓብ ንስሐ እንደገባም ሆነ ወደ ይሖዋ ለመቅረብና ምሕረት ለማግኘት የነቢዩን እርዳታ እንደጠየቀም አይገልጽም። መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ነገር ቢኖር አክዓብ “ሊበላና ሊጠጣ” መሄዱን ብቻ ነው። (1 ነገ. 18:41, 42) ኤልያስስ ምን አድርጎ ይሆን?

6, 7. ኤልያስ ስለ ምን ጉዳይ ጸልዮአል? ለምንስ?

6 “ኤልያስ ግን ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ጫፍ ወጣ፤ ፊቱንም በጕልበቶቹ መካከል አድርጎ ወደ መሬት አቀረቀረ።” አክዓብ ሆዱን ለመሙላት ሲሄድ ኤልያስ በሰማይ ወደሚኖረው አባቱ የመጸለይ አጋጣሚ አገኘ። ኤልያስ ፊቱ ጉልበቱ ጋ እስኪደርስ ድረስ በትሕትና ራሱን እንዴት ዝቅ እንዳደረገ ልብ በል። ኤልያስ ምን እያደረገ ነበር? ምን እያደረገ እንደነበር መገመት አያስፈልገንም። መጽሐፍ ቅዱስ በያዕቆብ 5:18 ላይ ኤልያስ ድርቁ እንዲቆም እንደጸለየ ይነግረናል። በመሆኑም በቀርሜሎስ ተራራ አናት ላይ በነበረበት ወቅት እንዲህ ያለውን ጸሎት እያቀረበ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም።

ኤልያስ ያቀረባቸው ጸሎቶች የአምላክ ፈቃድ እንዲፈጸም ከፍተኛ ፍላጎት እንደነበረው ያሳያሉ

7 ቀደም ሲል ይሖዋ “በምድሪቱ ላይ ዝናብ አዘንባለሁ” በማለት ተናግሮ ነበር። (1 ነገ. 18:1) በመሆኑም ኤልያስ የይሖዋ ፈቃድ እንዲፈጸም ጸልዮአል፤ ይህም ከአንድ ሺህ ዓመት ገደማ በኋላ ኢየሱስ ተከታዮቹን እንዴት መጸለይ እንዳለባቸው ካስተማረው ትምህርት ጋር ይስማማል።—ማቴ. 6:9, 10

8. ኤልያስ የተወው ምሳሌ ስለ ጸሎት ምን ያስተምረናል?

8 ኤልያስ የተወው ምሳሌ ስለ ጸሎት ብዙ ነገር ያስተምረናል። ከምንም በላይ ኤልያስን የሚያሳስበው የአምላክ ፈቃድ መፈጸም ነበር። እኛም በምንጸልይበት ጊዜ፣ “የምንጠይቀው ነገር ምንም ይሁን ምን ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ ሁኔታ እስከለመንን ድረስ” አምላክ እንደሚሰማን ማስታወሳችን ጥሩ ነው። (1 ዮሐ. 5:14) ከዚህ በግልጽ መረዳት እንደምንችለው ተቀባይነት ባለው መንገድ መጸለይ እንድንችል የአምላክ ፈቃድ ምን እንደሆነ ማወቅ ያስፈልገናል፤ የአምላክ ፈቃድ ምን እንደሆነ ለማወቅ ደግሞ ዘወትር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ይኖርብናል። በተጨማሪም ኤልያስ ድርቁ እንዲቆም የጸለየው በትውልድ አገሩ የሚኖሩ ሰዎች የሚደርስባቸው መከራ ስላሳሰበው እንደሆነ ግልጽ ነው። በዚያን ዕለት ይሖዋ ያደረገውን ተአምር ሲመለከት ልቡ በአመስጋኝነት ስሜት እንደተሞላ ምንም ጥርጥር የለውም። እኛም በጸሎታችን ላይ የሌሎች ደህንነት እንደሚያሳስበን መግለጽ እንዲሁም ስለተደረገልን ነገር ከልብ ማመስገን እንችላለን።—2 ቆሮንቶስ 1:11ን እና ፊልጵስዩስ 4:6ን አንብብ።

ጠንካራ እምነትና ነቅቶ የመጠበቅ ዝንባሌ

9. ኤልያስ አገልጋዩን ምን እንዲያደርግ ነገረው? የትኞቹን ሁለት ባሕርያት እንመለከታለን?

9 ኤልያስ፣ ይሖዋ ድርቁን ለማቆም እርምጃ እንደሚወስድ እርግጠኛ ቢሆንም ይህን የሚያደርገው መቼ እንደሆነ ግን የሚያውቀው ነገር አልነበረም። ታዲያ ነቢዩ በዚህ መሃል ምን አደረገ? ዘገባው ምን እንደሚል ልብ በል፦ “አገልጋዩንም፣ ‘ውጣና ወደ ባሕሩ ተመልከት’ አለው። አገልጋዩም ሄዶ ተመለከተና፤ ‘በዚያ ምንም የለም’ አለው። ኤልያስ ሰባት ጊዜ፣ ‘እንደ ገና ሂድ’ አለው።” (1 ነገ. 18:43) ኤልያስ ከተወው ምሳሌ ቢያንስ ሁለት ትምህርቶችን እናገኛለን። የመጀመሪያው ነቢዩ ያሳየው ጠንካራ እምነት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በንቃት ይጠባበቅ የነበረ መሆኑ ነው።

ኤልያስ፣ ይሖዋ እርምጃ ሊወስድ እንደሆነ የሚጠቁም ምልክት ለማየት ጓጉቶ ነበር

10, 11. (ሀ) ኤልያስ ይሖዋ በገባው ቃል እንደሚተማመን ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) እኛስ እንዲህ ያለ እምነት እንድናዳብር የሚረዳን ምንድን ነው?

10 ኤልያስ፣ ይሖዋ የተናገረውን ነገር እንደሚፈጽም ጠንካራ እምነት ስለነበረው ይሖዋ እርምጃ የሚወስድበት ጊዜ መድረሱን የሚያሳይ አንድ ፍንጭ ለማየት በጉጉት ይጠባበቅ ነበር። በመሆኑም አገልጋዩ ምቹ ወደሆነ አንድ ከፍታ ላይ በመውጣት ዝናብ እንደሚዘንብ የሚጠቁም ምልክት መኖር አለመኖሩን እንዲያይ ላከው። አገልጋዩም “በዚያ ምንም የለም” የሚል ተስፋ አስቆራጭ ሪፖርት ይዞ ተመለሰ። ሰማዩ ጥርት ያለ ከመሆኑም በላይ ደመና የሚባል ነገር አይታይበትም። እዚህ ላይ ጥያቄ የሚፈጥር አንድ ነገር እንዳለ አስተዋልክ? ኤልያስ ለአክዓብ “የከባድ ዝናብ ድምፅ ይሰማል” ብሎት እንደነበር አስታውስ። ነቢዩ በሰማዩ ላይ ምንም ደመና ሳይኖር እንዴት እንዲህ ሊል ቻለ?

11 ኤልያስ፣ ይሖዋ የገባውን ቃል ያውቃል። የይሖዋ ነቢይና ወኪል እንደመሆኑ መጠን አምላኩ ቃሉን እንደሚጠብቅ እርግጠኛ ነበር። ኤልያስ በይሖዋ ላይ እጅግ ከመተማመኑ የተነሳ ከባድ ዝናብ ሲጥል የሰማ ያህል ሆኖ ነበር። ይህ ታሪክ፣ መጽሐፍ ቅዱስ “የማይታየውን እንደሚያየው አድርጎ በጽናት ቀጥሏል” በማለት ስለ ሙሴ የተናገረውን አባባል ያስታውሰን ይሆናል። አምላክ ለአንተ ይህን ያህል እውን ነው? ይሖዋ፣ በእሱና በገባቸው ተስፋዎች ላይ እንዲህ ያለ እምነት እንዲኖረን የሚያስችል በቂ ማስረጃ ሰጥቶናል።—ዕብ. 11:1, 27

12. ኤልያስ በንቃት ይጠባበቅ እንደነበር ያሳየው እንዴት ነው? አንድ ትንሽ ደመና እንደታየች ሲሰማስ ምን አደረገ?

12 በመቀጠል ደግሞ ኤልያስ ምን ያህል በንቃት ይጠባበቅ እንደነበር ልብ በል። አገልጋዩን አንዴ ወይም ሁለቴ ሳይሆን ሰባት ጊዜ ተመልሶ እንዲሄድ ልኮታል! አገልጋዩ አሁንም አሁንም ሲላክ ምን ያህል ሊሰላች እንደሚችል መገመት ትችላለህ፤ ሆኖም ኤልያስ አንድ ምልክት ለማየት ከፍተኛ ጉጉት የነበረው ሲሆን ተስፋም አልቆረጠም። በመጨረሻም አገልጋዩ ለሰባተኛ ጊዜ ደርሶ ሲመለስ ኤልያስን “እነሆ፤ የሰው እጅ የምታህል ትንሽ ደመና ከባሕሩ እየወጣች ነው” አለው። አገልጋዩ፣ የእጁን መዳፍ በማሳየት ከታላቁ ባሕር የወጣችውን የትንሿን ደመና መጠን ለመግለጽ ሲሞክር በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ! አገልጋዩ ይህች ትንሽ ደመና ያን ያህል ለውጥ እንደማታመጣ አስቦ ሊሆን ይችላል። ለኤልያስ ግን ትልቅ ትርጉም ነበራት። ስለሆነም ኤልያስ ወዲያውኑ ለአገልጋዩ “ሂድና አክዓብን፣ ‘ዝናቡ ሳያግድህ፣ ሠረገላህን ጭነህ ውረድ’ ብለህ ንገረው” የሚል መመሪያ ሰጠው።—1 ነገ. 18:44

13, 14. (ሀ) ኤልያስ ነቅቶ በመጠበቅ ረገድ የተወውን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ፈጣን እርምጃ እንድንወስድ የሚያነሳሱ ምን ምክንያቶች አሉን?

13 በዚህ ረገድም ቢሆን ኤልያስ ትልቅ ምሳሌ ይሆነናል። እኛም የምንኖረው አምላክ ዓላማውን ለማስፈጸም እርምጃ ሊወስድ በተቃረበበት ዘመን ላይ ነው። ኤልያስ ድርቁ የሚያበቃበትን ጊዜ ሲጠባበቅ ቆይቷል፤ ዛሬም ቢሆን የአምላክ አገልጋዮች ይህ ብልሹ ዓለም የሚጠፋበትን ጊዜ እየተጠባበቁ ነው። (1 ዮሐ. 2:17) ይሖዋ አምላክ እርምጃ እስኪወስድ ድረስ ልክ እንደ ኤልያስ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ንቁ ሆነን መጠበቅ ይኖርብናል። የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ፣ ተከታዮቹን “ስለዚህ ጌታችሁ በየትኛው ቀን እንደሚመጣ ስለማታውቁ ምንጊዜም ነቅታችሁ ጠብቁ” በማለት መክሯቸዋል። (ማቴ. 24:42) ሆኖም ኢየሱስ ይህን ሲል ተከታዮቹ መጨረሻው መቼ እንደሚመጣ ምንም የሚያውቁት ነገር እንደማይኖር መናገሩ ነበር? በፍጹም፤ ኢየሱስ መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት የዓለም ሁኔታ ምን ሊመስል እንደሚችል ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥቷል። እያንዳንዳችን ‘በዚህ ሥርዓት መደምደሚያ’ ላይ እንደምንገኝ የሚጠቁመው የተለያዩ ገጽታዎች ያሉት ይህ ምልክት እየተፈጸመ መሆኑን እየተመለከትን ነው።—ማቴዎስ 24:3-7ን አንብብ።

ኤልያስ አንዲት ትንሽ ደመና ማየቱ ይሖዋ እርምጃ የሚወስድበት ጊዜ መድረሱን እንዲያምን አድርጎታል፤ እኛም የመጨረሻውን ቀን ምልክት ማየታችን አፋጣኝ እርምጃ እንድንወስድ ሊያነሳሳን ይገባል

14 እያንዳንዱ የምልክቱ ገጽታ ጠንካራና አሳማኝ ማስረጃ ይዟል። ታዲያ እንዲህ ያለው ማስረጃ ይሖዋን በጥድፊያ ስሜት እንድናገለግል አነሳስቶናል? ከአድማስ ማዶ የታየችው አንዲት ትንሽ ደመና ኤልያስ፣ ይሖዋ እርምጃ የሚወስድበት ጊዜ መድረሱን እንዲያምን አድርጋዋለች። ይህ ታማኝ ነቢይ የጠበቀው ነገር ሳይፈጸም በመቅረቱ የተነሳ ለሐዘን ተዳርጎ ይሆን?

ይሖዋ እፎይታና በረከት ያመጣል

15, 16. በሚያስገርም ፍጥነት የተከናወኑት ነገሮች የትኞቹ ናቸው? ኤልያስ ስለ አክዓብ ምን አስቦ ሊሆን ይችላል?

15 ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “ወዲያውኑም ሰማዩ በጥቍር ደመና ተሸፈነ፤ ነፋሱ ነፈሰ፤ ከባድ ዝናብ ጣለ፤ አክዓብም በሠረገላ ተቀምጦ ወደ ኢይዝራኤል ሄደ።” (1 ነገ. 18:45) ሁሉም ነገር በሚያስገርም ፍጥነት መከናወን ጀመረ። የኤልያስ አገልጋይ የነቢዩን መልእክት ለአክዓብ እየነገረው ሳለ ያቺ ትንሽ ደመና እየበዛች በመሄዷ ሰማዩ እየተሸፈነና እየጠቆረ መጣ። ከባድ ነፋስም ነፈሰ። በመጨረሻም ከሦስት ዓመት ተኩል በኋላ በእስራኤል ምድር ላይ ዝናብ ጣለ። ደርቆ የተሰነጣጠቀው መሬት በዝናቡ ራሰ። ኃይለኛ ዶፍ በመጣሉ የተነሳ ሞልቶ የነበረው የቂሶን ወንዝ በዚያ የታረዱትን የበኣል ነቢያት ደም ጠራርጎ እንደወሰደው ጥርጥር የለውም። አስቸጋሪ የነበሩት እስራኤላውያንም አስጸያፊ የሆነውን የበኣል አምልኮ ከምድሪቱ ሙሉ በሙሉ ማስወገድ የሚችሉበት አጋጣሚ ነበራቸው።

“ከባድ ዝናብ ጣለ”

16 ኤልያስ ይህ ይፈጸማል ብሎ ጠብቆ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም! አክዓብ ይህን አስደናቂ ክንውን ሲመለከት ምን ያደርግ ይሆን ብሎ ሳያስብ አይቀርም። አክዓብ ንስሐ በመግባት ምድሪቱን በበኣል አምልኮ ከመበከል ይቆጠብ ይሆን? በዕለቱ የተከናወኑት ነገሮች እንዲህ ያለ እርምጃ እንዲወስድ ሊገፋፉት ይገባ ነበር። እርግጥ ነው፣ በወቅቱ አክዓብ ምን አስቦ እንደነበር የምናውቀው ነገር የለም። ዘገባው የሚናገረው ነገር ቢኖር አክዓብ “በሠረገላ ተቀምጦ ወደ ኢይዝራኤል” እንደሄደ ብቻ ነው። ከተከናወኑት ነገሮች ትምህርት አግኝቶ ይሆን? አካሄዱንስ ለመለወጥ ቆርጦ ይሆን? በፍጹም! ቆየት ብለው የተከናወኑት ነገሮች ይህን እንዳላደረገ ያሳያሉ። ይሁንና አክዓብም ሆነ ኤልያስ በዚህ ዕለት ገና የሚያከናውኑት ነገር አለ።

17, 18. (ሀ) ኤልያስ ወደ ኢይዝራኤል ሲሄድ በመንገድ ላይ ምን አጋጠመው? (ለ) ኤልያስ ከቀርሜሎስ ወደ ኢይዝራኤል እየሮጠ መሄዱ አስደናቂ ነው የምንለው ለምንድን ነው? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)

17 የይሖዋ ነቢይ፣ አክዓብ የሄደበትን መንገድ ተከትሎ መጓዝ ጀመረ። ረጅም፣ በጨለማ የተዋጠና የጨቀየ መንገድ ከፊቱ ይጠብቀዋል። ሆኖም አንድ ያልተጠበቀ ነገር ተከሰተ።

18 “የእግዚአብሔርም ኀይል በኤልያስ ላይ ወረደ፤ ኤልያስም ልብሱን ከፍ አድርጎ በቀበቶው ካጠበቀ በኋላ እስከ ኢይዝራኤል ድረስ በአክዓብ ፊት ሮጠ።” (1 ነገ. 18:46) ከዚህ በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው የይሖዋ ኃይል በተለየ መንገድ በኤልያስ ላይ እየሠራ ነበር። ኢይዝራኤል የምትገኘው 30 ኪሎ ሜትር ገደማ ላይ ሲሆን ኤልያስ ደግሞ ዕድሜው ገፍቷል። * ይህ ነቢይ እንደ ልብ ለመሮጥ እንዲያመቸው የለበሰውን ረጅም መጎናጸፊያ ሰብሰብ አድርጎ ወገቡ ላይ በቀበቶው ሸብ በማድረግ በጨቀየው መንገድ ላይ ሲሮጥ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። እሱም በከፍተኛ ፍጥነት በመሮጥ የቤተ መንግሥቱ ሠረገላ ላይ ደረሰበት፤ ከዚያም አልፎት ሄደ!

19. (ሀ) ኤልያስ ከአምላክ ያገኘው ኃይልና ጥንካሬ የትኞቹን ትንቢቶች ያስታውሰናል? (ለ) ኤልያስ ወደ ኢይዝራኤል እየሮጠ ሲሄድ ስለ ምን ነገር እርግጠኛ ነበር?

19 ይህ ለኤልያስ እንዴት ያለ በረከት ነበር! እንዲህ የመሰለ ምናልባትም በወጣትነት ጊዜው ተሰምቶት የማያውቀው ዓይነት ኃይል፣ ጥንካሬና ብርታት ሲሰማው ምን ያህል ተደስቶ ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም። ይህ ሁኔታ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ወደፊት ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ፍጹም የሆነ ጤንነትና ብርታት እንደሚያገኙ ዋስትና የሚሰጡትን ትንቢቶች አስታውሶን ይሆናል። (ኢሳይያስ 35:6ን አንብብ፤ ሉቃስ 23:43) ኤልያስ በዚያ በጨቀየ መንገድ ላይ ሲሮጥ፣ ብቻውን እውነተኛ አምላክ የሆነውን የአባቱን የይሖዋን ሞገስ እንዳገኘ ተገንዝቦ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም!

20. የይሖዋን በረከት ለማግኘት ጥረት ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

20 ይሖዋ እኛን ለመባረክ ይጓጓል። እንግዲያው እነዚህን በረከቶች ለማግኘት ጥረት እናድርግ፤ ደግሞም እንዲህ ማድረጋችን የሚያስቆጭ አይደለም። እንደ ኤልያስ ሁሉ እኛም፣ በዚህ አደገኛና አጣዳፊ ዘመን ውስጥ ይሖዋ እርምጃ የሚወስድበት ጊዜ መቅረቡን የሚያሳዩትን ጠንካራ ማስረጃዎች በጥንቃቄ በመመርመር ነቅተን መጠበቅ ያስፈልገናል። እኛም እንደ ኤልያስ “የእውነት አምላክ” የሆነው ይሖዋ በገባቸው ተስፋዎች ላይ ሙሉ በሙሉ እምነት እንድንጥል የሚያደርጉ በቂ ምክንያቶች አሉን።—መዝ. 31:5

^ አን.18 ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ይሖዋ፣ ኤልሳዕን እንዲያሠለጥነው ለኤልያስ ኃላፊነት ሰጠው፤ ኤልሳዕ “የኤልያስን እጅ ያስታጥብ” እንደነበር ተጠቅሷል። (2 ነገ. 3:11) ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው ኤልሳዕ፣ አረጋዊውን ኤልያስን በሚያስፈልገው ሁሉ በመርዳት የእሱ አገልጋይ ሆኖ ሠርቷል።