በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ ሦስት

አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ ምንድን ነው?

አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ ምንድን ነው?
  • አምላክ ለሰው ዘር ያለው ዓላማ ምንድን ነው?

  • አምላክ ተቃውሞ የደረሰበት እንዴት ነው?

  • በምድር ላይ ያለው ሕይወት ወደፊት ምን መልክ ይኖረዋል?

1. አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ ምንድን ነው?

አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ በጣም አስደሳች ነው። ይሖዋ ምድር ደስተኛና ጤናማ በሆኑ ሰዎች እንድትሞላ ይፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስ ‘አምላክ በዔድን የአትክልት ስፍራ እንዳዘጋጀ’ እና “ለዐይን የሚያስደስት ለመብልም መልካም የሆነውን ዛፍ ሁሉ” እንዳበቀለ ይናገራል። አምላክ የመጀመሪያዎቹን ወንድና ሴት ማለትም አዳምንና ሔዋንን ከፈጠረ በኋላ በዚያች ውብ መኖሪያ ውስጥ በማስቀመጥ “ብዙ ተባዙ፤ ምድርን ሙሏት፤ ግዟትም” አላቸው። (ዘፍጥረት 1:28፤ 2:8, 9, 15) ስለዚህ የአምላክ ዓላማ ሰዎች ልጆችን እንዲወልዱ፣ መኖሪያቸው የሆነችውን ገነት በመላዋ ምድር ላይ እንዲያስፋፉና እንስሳትን እንዲንከባከቡ ነበር።

2. (ሀ) አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ እንደሚፈጸም እንዴት እናውቃለን? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ በሚለው መሠረት ለዘላለም የሚኖሩት ምን ዓይነት ሰዎች ናቸው?

2 ይሖዋ አምላክ የሰው ልጆች ገነት በሆነች ምድር ላይ እንዲኖሩ ያለው ዓላማ ይፈጸማል የሚል እምነት አለህ? አምላክ “የተናገርሁትን . . . እፈጽማለሁ” ሲል ተናግሯል። (ኢሳይያስ 46:9-11፤ 55:11) አዎን፣ አምላክ ዓላማውን እንደሚፈጽም የተረጋገጠ ነው! ‘ምድርን የፈጠራት መኖሪያ እንድትሆን እንጂ ለከንቱ እንዳልሆነ’ ገልጿል። (ኢሳይያስ 45:18 የ1954 ትርጉም) አምላክ በምድር ላይ እንዲኖሩ የሚፈልገው ምን ዓይነት ሰዎችን ነው? ለምን ያህል ጊዜስ እንዲኖሩ ይፈልጋል? መጽሐፍ ቅዱስ “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም  ይኖራሉ” ሲል መልስ ይሰጣል።—መዝሙር 37:29፤ ራእይ 21:3, 4

3. በአሁኑ ጊዜ በምድር ላይ ምን አሳዛኝ ሁኔታ ይታያል? ይህስ ምን ጥያቄዎች ያስነሳል?

3 እርግጥ ነው፣ ይህ ገና አልተፈጸመም። በአሁኑ ጊዜ ሰዎች ይታመማሉ እንዲሁም ይሞታሉ፤ አልፎ ተርፎም እርስ በርስ ይጋጫሉ ብሎም ይገዳደላሉ። በመሆኑም አንድ የተፈጠረ ችግር አለ። ይሁን እንጂ የአምላክ ዓላማ አሁን በምድር ላይ ከሚታየው ሁኔታ ፈጽሞ የተለየ እንደሆነ የተረጋገጠ ነው! ታዲያ የተፈጠረው ችግር ምንድን ነው? የአምላክ ዓላማ ያልተፈጸመው ለምንድን ነው? ችግሩ የተጠነሰሰው በሰማይ በመሆኑ የትኛውም በሰው ልጆች የተጻፈ የታሪክ መጽሐፍ መልሱን ሊሰጠን አይችልም።

አንድ ጠላት ተነሳ

4, 5. (ሀ) በእባብ አማካኝነት ሔዋንን ያነጋገራት ማን ነው? (ለ) ቀደም ሲል ጨዋና ሐቀኛ የነበረ ሰው ሌባ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?

4 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው የመጀመሪያው መጽሐፍ በኤደን የአትክልት ሥፍራ አንድ ተቃዋሚ ብቅ እንዳለ ይገልጽልናል። ይህ ተቃዋሚ “እባብ” ተብሎ የተገለጸ ቢሆንም እንስሳ አይደለም። የመጨረሻው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ “ዲያብሎስ ወይም ሰይጣን ተብሎ የሚጠራው፣ ዓለምን ሁሉ የሚያስተው” ሲል ይገልጸዋል። “የጥንቱ እባብ” ተብሎም ተጠርቷል። (ዘፍጥረት 3:1፤ ራእይ 12:9) ጥሩ ችሎታ ያለው አንድ ሰው አሻንጉሊት እየተናገረ እንዳለ በማስመሰል መናገር እንደሚችል ሁሉ ይህ ኃይለኛ መልአክ ወይም የማይታይ መንፈሳዊ ፍጡርም ሔዋንን ለማነጋገር አንድን እባብ መሣሪያ አድርጎ ተጠቅሟል። ይህ መንፈሳዊ ፍጡር፣ አምላክ ምድርን ለሰው ልጆች ባዘጋጀበት ወቅት እንደነበረ ምንም ጥርጥር የለውም።—ኢዮብ 38:4, 7

5 ይሁን እንጂ የይሖዋ ፍጥረታት በሙሉ ፍጹማን በመሆናቸው ‘ዲያብሎስን’ ወይም ‘ሰይጣንን’ የፈጠረው ማን ነው? በአጭር አነጋገር ከአምላክ መንፈሳዊ ልጆች አንዱ ራሱን ለውጦ ዲያብሎስ ሆነ። ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? በአንድ ወቅት ጨዋና ሐቀኛ የነበረ ሰው ተለውጦ ሌባ ሊሆን እንደሚችል መገንዘብ ይኖርብናል። ይህ ሊሆን የሚችለው እንዴት  ነው? ግለሰቡ በልቡ ውስጥ መጥፎ ምኞት እንዲጸነስ ሊያደርግ ይችላል። ስለዚያ ነገር ማሰቡን ከቀጠለ መጥፎው ምኞት እያየለ ይሄዳል። ከዚያም ሁኔታው ከተመቻቸለት ሲያስበው የቆየውን መጥፎ ምኞት ወደ ተግባር ሊለውጠው ይችላል።—ያዕቆብ 1:13-15

6. አንድ ኃያል የሆነ የአምላክ መንፈሳዊ ልጅ ሰይጣን ዲያብሎስ የሆነው እንዴት ነው?

6 በሰይጣን ዲያብሎስ ላይም የደረሰው ሁኔታ ይኸው ነው። አምላክ አዳምና ሔዋንን ልጆች እንዲወልዱና ምድርን በዘሮቻቸው እንዲሞሉ ሲነግራቸው ሰይጣን ሳይሰማ አልቀረም። (ዘፍጥረት 1:27, 28) ‘እነዚህ ሁሉ ሰዎች እኮ አምላክን በማምለክ ፋንታ እኔን ሊያመልኩ ይችላሉ’ ብሎ አስቦ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ መጥፎ ምኞት በውስጡ ተጸነሰ። በመጨረሻም ይህን ምኞቱን ወደ ተግባር በመለወጥ ስለ አምላክ ውሸት ተናግሮ ሔዋንን አታለላት። (ዘፍጥረት 3:1-5) በዚህ መንገድ “ዲያብሎስ” ይኸውም “ስም አጥፊ” እንዲሁም “ሰይጣን” ማለትም “ተቃዋሚ” ሆነ።

7. (ሀ) አዳምና ሔዋን የሞቱት ለምንድን ነው? (ለ) የአዳም ዘሮች በሙሉ የሚያረጁትና የሚሞቱት ለምንድን ነው?

7 ሰይጣን ዲያብሎስ በመዋሸትና በማታለል አዳምና ሔዋን የአምላክን ትእዛዝ እንዲጥሱ አደረጋቸው። (ዘፍጥረት 2:17፤ 3:6) በዚህም ምክንያት አምላክ ትእዛዙን ከጣሱ ሞት እንደሚጠብቃቸው በነገራቸው መሠረት ከጊዜ በኋላ ሞቱ። (ዘፍጥረት 3:17-19) አዳም ኃጢአት በሠራበት ጊዜ ፍጽምና ስለጎደለው ለዘሮቹ በሙሉ ኃጢአትን አውርሷል። (ሮሜ 5:12) ይህን ሁኔታ ለማስረዳት እንጀራ ለመጋገር የሚያገለግል ምጣድ እንደ ምሳሌ መጠቀም ይቻላል። ምጣዱ ስንጥቅ ካለው በምጣዱ ላይ የሚጋገረው እንጀራ ሁሉ ምን ይኖረዋል? እያንዳንዱ እንጀራ በምጣዱ ላይ ያለውን ስንጥቅ ወይም እንከን ይዞ ይወጣል። በተመሳሳይም እያንዳንዱ ሰው ከአዳም አለፍጽምናን ወርሷል። ሁሉም ሰው የሚያረጀውና የሚሞተው በዚህ ምክንያት ነው።—ሮሜ 3:23

8, 9. (ሀ) ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው ሰይጣን ምን የሚል ተቃውሞ አስነስቷል? (ለ) አምላክ ዓመጸኞቹን ወዲያውኑ ያላጠፋቸው ለምንድን ነው?

8 ሰይጣን፣ አዳምና ሔዋን በአምላክ ላይ ኃጢአት እንዲሠሩ በገፋፋቸው  ጊዜ ዓመጽ እያነሳሳ ነበር። ይሖዋ የሚገዛበትን መንገድ መቃወሙ ነበር። በመሆኑም ሰይጣን በተዘዋዋሪ መንገድ ‘አምላክ ክፉ ገዥ ነው። ውሸት የሚናገር ከመሆኑም በላይ ተገዥዎቹን ጥሩ ነገር ይከለክላቸዋል። ሰዎች ለአምላክ መገዛት አያስፈልጋቸውም። ጥሩና መጥፎ የሆነውን ነገር በራሳቸው መወሰን ይችላሉ። በእኔ አገዛዝ ሥር ቢሆኑ ደግሞ የተሻለ  ጥቅም ያገኛሉ’ ማለቱ ነበር። አምላክ እንዲህ ላለው ስድብ ያዘለ ውንጀላ ምላሽ የሚሰጠው እንዴት ነው? አንዳንዶች፣ ዓመጸኞቹን ወዲያውኑ ማጥፋት ነበረበት ብለው ያስባሉ። ይሁን እንጂ ይህ እርምጃ ሰይጣን ላስነሳው ተቃውሞ ጥሩ ምላሽ ይሆናል? የአምላክ አገዛዝ ትክክል መሆኑን ያረጋግጣል?

9 ይሖዋ ፍጹም የሆነ የፍትሕ ባሕርይ ያለው አምላክ በመሆኑ ዓመጸኞቹን ወዲያውኑ ሊያጠፋቸው አይችልም። ሰይጣን ላስነሳው ተቃውሞ አጥጋቢ የሆነ ምላሽ ለመስጠትና ዲያብሎስ ውሸታም መሆኑን ለማረጋገጥ ጊዜ እንደሚያስፈልግ ተሰምቶታል። ስለሆነም አምላክ የሰው ልጆች ለተወሰነ ጊዜ በሰይጣን ተጽዕኖ ሥር ሆነው ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ ፈቀደላቸው። ይሖዋ ይህን ያደረገበት ምክንያትና ለእነዚህ አከራካሪ ጉዳዮች እልባት ሳይሰጥ ረዘም ያለ ጊዜ እንዲያልፍ የፈቀደበት ምክንያት በዚህ መጽሐፍ 11ኛ ምዕራፍ ላይ ይብራራል። ይሁን እንጂ አሁን እንደሚከተለው ብለን ማሰባችን ተገቢ ነው:- አዳምና ሔዋን ምንም ዓይነት መልካም ነገር አድርጎላቸው የማያውቀውን ሰይጣንን ማመናቸው ትክክል ነው? ሁሉን ነገር የሰጣቸው ፈጣሪያቸው ይሖዋ ጨካኝና ውሸታም ነው ብለው ማመናቸው ትክክል ነው? አንተ ብትሆን ኖሮ ምን ታደርግ ነበር?

10. ለሰይጣን ተቃውሞ ምላሽ በመስጠት ከይሖዋ ጎን መቆም የምትችለው እንዴት ነው?

10 በዛሬው ጊዜ በእያንዳንዳችን ፊት ተመሳሳይ የሆኑ አከራካሪ ጉዳዮች ስለሚደቀኑ እነዚህን ጥያቄዎች ልናስብባቸው ይገባል። አዎን፣ ለሰይጣን ተቃውሞ ምላሽ በመስጠት ከይሖዋ ጎን መቆምህን ማሳየት የምትችልበት አጋጣሚ አለህ። ይሖዋን ገዥህ አድርገህ መቀበልና ሰይጣን ውሸታም መሆኑን ማሳየት ትችላለህ። (መዝሙር 73:28፤ ምሳሌ 27:11) የሚያሳዝነው ግን በዚህ ዓለም ላይ ካሉት በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መካከል እንዲህ ያለውን ምርጫ የሚያደርጉት ጥቂቶች ብቻ ናቸው። ይህ ደግሞ በእርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣን የዚህ ዓለም ገዥ እንደሆነ ያስተምራል? የሚል አስፈላጊ የሆነ ጥያቄ ያስነሳል።

 ይህን ዓለም የሚገዛው ማን ነው?

ሰይጣን የዓለም መንግሥታት በሙሉ የእሱ ባይሆኑ ኖሮ ለኢየሱስ ለመስጠት እንዴት ሐሳብ ሊያቀርብ ይችላል?

11, 12. (ሀ) በኢየሱስ ላይ የደረሰው ፈተና ሰይጣን የዚህ ዓለም ገዥ መሆኑን የሚያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ሰይጣን የዚህ ዓለም ገዥ መሆኑን የሚያሳይ ምን ሌላ ማስረጃ አለ?

11 ኢየሱስ የዚህ ዓለም ገዥ ሰይጣን መሆኑን ተጠራጥሮ አያውቅም። በአንድ ወቅት ሰይጣን ተአምራዊ በሆነ መንገድ ለኢየሱስ ‘የዓለምን መንግሥታት ከነክብራቸው’ አሳይቶት ነበር። ከዚያም ሰይጣን “ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ” ሲል ቃል ገባለት። (ማቴዎስ 4:8, 9፤ ሉቃስ 4:5, 6) እስቲ አስበው። ሰይጣን የእነዚህ መንግሥታት ገዥ ባይሆን ኖሮ ይህ ግብዣ ለኢየሱስ ፈተና ይሆንበት ነበር? ኢየሱስ እነዚህ ሁሉ የዓለም መንግሥታት የሰይጣን መሆናቸውን አልካደም። ገዥያቸው ሰይጣን ባይሆን ኖሮ ኢየሱስ ይህን ከመናገር ወደኋላ አይልም ነበር።

12 እርግጥ ነው፣ ይሖዋ ሁሉን ቻይ አምላክና ዕጹብ ድንቅ የሆነው ጽንፈ ዓለም ፈጣሪ ነው። (ራእይ 4:11) ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ የትም ቦታ ላይ ይሖዋ አምላክም ሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ የዚህ ዓለም ገዥ እንደሆኑ አይናገርም። እንዲያውም ኢየሱስ በቀጥታ ሰይጣንን “የዚህ ዓለም ገዥ” ሲል ጠርቶታል። (ዮሐንስ 12:31፤ 14:30፤ 16:11) አልፎ ተርፎም መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣን ዲያብሎስን “የዚህ ዓለም አምላክ” ሲል ይጠራዋል። (2 ቆሮንቶስ 4:3, 4) ይህን ተቃዋሚ ወይም ሰይጣንን በተመለከተ ክርስቲያኑ ሐዋርያ ዮሐንስ ‘መላው ዓለም በክፉው ሥር ነው’ ሲል ጽፏል።—1 ዮሐንስ 5:19

የሰይጣን ዓለም የሚወገደው እንዴት ነው?

13. አዲስ ዓለም መምጣቱ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

13 ዓመት አልፎ ዓመት በተተካ ቁጥር ይህ ዓለም ለሕይወት ይበልጥ አስጊ እየሆነ መጥቷል። በጦርነት በሚፋጁ ሠራዊቶች፣ አጭበርባሪ በሆኑ ፖለቲከኞች፣ ግብዝ በሆኑ የሃይማኖት መሪዎችና ርኅራኄ በሌላቸው ወንጀለኞች ተሞልቷል። ዓለም በአጠቃላይ ሊለወጥና ሊስተካከል ከማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ክፉውን ዓለም በአርማጌዶን ጦርነት የሚያጠፋበት ጊዜ እንደተቃረበ ይገልጻል። በዚያን  ጊዜ ይህ ዓለም ጽድቅ በሚሰፍንበት አዲስ ዓለም ይተካል።—ራእይ 16:14-16

14. አምላክ የመንግሥቱ ገዥ እንዲሆን የመረጠው ማንን ነው? ይህስ በትንቢት የተነገረው እንዴት ነው?

14 ይሖዋ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስን የሰማያዊ መንግሥቱ ወይም መስተዳድሩ ገዥ እንዲሆን መርጦታል። መጽሐፍ ቅዱስ ከብዙ ዓመታት በፊት “ሕፃን ተወልዶልናልና፤ ወንድ ልጅ ተሰጥቶናል፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል። ስሙም . . . የሰላም ልዑል ይባላል። ለመንግሥቱ ስፋት፣ ለሰላሙም ብዛት ፍጻሜ የለውም” ሲል ተንብዮ ነበር። (ኢሳይያስ 9:6, 7) ይህን መንግሥት በተመለከተ ኢየሱስ ተከታዮቹ “መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች፣ እንዲሁ በምድር ትሁን” ብለው እንዲጸልዩ አስተምሯቸዋል። (ማቴዎስ 6:10) በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ወደፊት እንደምንመለከተው የአምላክ መንግሥት በቅርቡ የዚህን ዓለም መንግሥታት በሙሉ በማጥፋት በእነሱ ቦታ ይተካል። (ዳንኤል 2:44) ከዚያም ምድርን ገነት ያደርጋል።

አዲስ ዓለም የሚመጣበት ጊዜ ቀርቧል!

15. ‘አዲሱ ምድር’ ምንድን ነው?

15 መጽሐፍ ቅዱስ “ጽድቅ የሚኖርበትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር በተስፋ ቃሉ መሠረት እንጠባበቃለን” ሲል ዋስትና ይሰጠናል። (2 ጴጥሮስ 3:13፤ ኢሳይያስ 65:17) አንዳንድ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ “ምድር” የሚለውን ቃል የሚጠቀመው በምድር ላይ የሚኖሩትን ሰዎች ለማመልከት ነው። (ዘፍጥረት 11:1 የ1954 ትርጉም) ስለዚህ ጻድቁ “አዲስ ምድር” የአምላክን ሞገስ የሚያገኘውን ሰብዓዊ ኅብረተሰብ ያመለክታል።

16. አምላክ በእሱ ፊት ተቀባይነት ለሚያገኙ ሰዎች የሚሰጠው እጅግ ውድ የሆነ ስጦታ ምንድን ነው? ይህን ስጦታ ለማግኘትስ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

16 ኢየሱስ በመጪው አዲስ ዓለም በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያገኙ ሁሉ “የዘላለም ሕይወት” ስጦታን እንደሚቀበሉ ቃል ገብቷል። (ማርቆስ 10:30) እባክህ ዮሐንስ 3:16ንና 17:3ን አውጣና ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ምን ማድረግ እንደሚያስፈልገን የተናገረውን ሐሳብ አንብብ። አሁን ደግሞ በመጪው ምድራዊ ገነት ውስጥ ይህን አስደሳች  የሆነ የአምላክ ስጦታ ለመቀበል ብቁ የሆኑ ሰዎች የሚያገኟቸውን በረከቶች በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ተመልከት።

17, 18. በየትኛውም የምድር ክፍል ሰላምና የተረጋጋ ሁኔታ እንደሚሰፍን እንዴት እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

17 ክፋት፣ ጦርነት፣ ወንጀልና ዓመጽ ይወገዳሉ። “ክፉ ሰው አይዘልቅም . . . ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ።” (መዝሙር 37:10, 11) አምላክ ‘ከዳር እስከ ዳር ጦርነትን ከምድር ስለሚያስወግድ’ ሰላም ይሰፍናል። (መዝሙር 46:9፤ ኢሳይያስ 2:4) ከዚያም “ጽድቅ ይሰፍናል፤ ጨረቃ ከስፍራዋ እስከምትታጣ ድረስም [ለዘላለም] ሰላም ይበዛል።”—መዝሙር 72:7

18 የይሖዋ አምላኪዎች በተረጋጋ ሁኔታ ይኖራሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበሩት እስራኤላውያን አምላክን እስከታዘዙ ድረስ በተረጋጋ ሁኔታ ይኖሩ ነበር። (ዘሌዋውያን 25:18, 19) በገነት ውስጥም ተመሳሳይ በሆነ የተረጋጋ ሁኔታ መኖር መቻል ምንኛ የሚያስደስት ነው!—ኢሳይያስ 32:18፤ ሚክያስ 4:4

19. በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ምግብ እንደሚትረፈረፍ እንዴት እናውቃለን?

19 የምግብ እጥረት አይኖርም። መዝሙራዊው “በምድሪቱ ላይ እህል ይትረፍረፍ፤ በተራሮችም ዐናት ላይ ይወዛወዝ” ሲል ዘምሯል። (መዝሙር 72:16) ይሖዋ አምላክ የእርሱ የሆኑትን ጻድቃን ይባርካል፤ ‘ምድርም ፍሬዋን ትሰጣለች።’—መዝሙር 67:6

20. መላዋ ምድር ገነት እንደምትሆን እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

20 መላዋ ምድር ገነት ትሆናለች። በአንድ ወቅት ኃጢአተኛ የሆኑ ሰዎች ያበላሿት ምድር ውብ በሆኑ አዳዲስ ቤቶችና የአትክልት ሥፍራዎች ትሞላለች። (ኢሳይያስ 65:21-24፤ ራእይ 11:18) ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ሰዎች የሚኖሩባቸው የምድር ክፍሎች እየተስፋፉ ስለሚሄዱ መላዋ ምድር እንደ ኤደን ገነት ውብና ፍሬያማ ትሆናለች። በተጨማሪም አምላክ ‘እጁን በመዘርጋት የሕያዋን ፍጥረታትን ሁሉ ፍላጎት ያረካል።’—መዝሙር 145:16

21. በሰዎችና በእንስሳት መካከል ሰላም እንደሚሰፍን የሚያሳየው ምንድን ነው?

21 በሰዎችና በእንስሳት መካከል ሰላም ይሰፍናል። የዱርና የቤት  እንስሳት በአንድነት ይመገባሉ። በአሁኑ ጊዜ አደገኛ የሆኑትን እንስሳት በዚያን ጊዜ ሕፃን ልጅ እንኳ አይፈራቸውም።—ኢሳይያስ 11:6-9፤ 65:25

22. በሽታ ምን ይሆናል?

22 በሽታ ይጠፋል። ኢየሱስ የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ገዥ ሆኖ የሚያከናውነው ፈውስ ምድር ሳለ ካከናወነው ፈውስ ይበልጥ መጠነ ሰፊ ይሆናል። (ማቴዎስ 9:35፤ ማርቆስ 1:40-42፤ ዮሐንስ 5:5-9) በዚያን ጊዜ “‘ታምሜአለሁ’ የሚል አይኖርም።”—ኢሳይያስ 33:24፤ 35:5, 6

23. ትንሣኤ ልባችን በሐሴት እንዲሞላ የሚያደርገው ለምንድን ነው?

23 በሞት ያጣናቸው ሰዎች ለዘላለም የመኖር ተስፋ ይዘው ከሞት ይነሳሉ። በሞት አንቀላፍተው የሚገኙና አምላክ የሚያስባቸው ሰዎች ሁሉ ዳግም ሕያው ይሆናሉ። እንዲያውም ‘ጻድቃንም ኀጥአንም ከሙታን ይነሣሉ።’—የሐዋርያት ሥራ 24:15፤ ዮሐንስ 5:28, 29

24. በምድር ላይ በገነት ስለ መኖር ስታስብ ምን ይሰማሃል?

24 ስለ ታላቁ ፈጣሪያችን ስለ ይሖዋ አምላክ ለመማርና እሱን ለማገልገል ቁርጥ ውሳኔ የሚያደርጉ ሁሉ አስደሳች ጊዜ ይጠብቃቸዋል! ኢየሱስ ከጎኑ ለተሰቀለው ክፉ አድራጊ “ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” ብሎ ቃል በገባለት ጊዜ የተናገረው ስለመጪዋ ምድራዊ ገነት ነበር። (ሉቃስ 23:43) እነዚህን ሁሉ በረከቶች ማግኘት የምንችልበትን በር ስለከፈተልን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ይበልጥ መማራችን በጣም አስፈላጊ ነው።