ለሮም ሰዎች የተጻፈ ደብዳቤ 5:1-21

  • በክርስቶስ አማካኝነት ከአምላክ ጋር መታረቅ (1-11)

  • በአዳም በኩል ሞት፣ በክርስቶስ በኩል ሕይወት (12-21)

    • ኃጢአትና ሞት ለሰው ሁሉ ተዳረሰ (12)

    • አንድ የጽድቅ ተግባር (18)

5  ስለዚህ አሁን በእምነት አማካኝነት ጻድቃን ናችሁ+ ስለተባልን በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኩል+ ከአምላክ ጋር ያለንን ሰላም ጠብቀን እንኑር፤*  ደግሞም በኢየሱስ አማካኝነት የአምላክን ጸጋ ለማግኘት በእምነት ወደ እሱ መቅረብ የቻልን ሲሆን ይህን ጸጋ አሁን አግኝተናል፤+ የአምላክንም ክብር እንደምናገኝ ተስፋ በማድረግ እጅግ እንደሰት።*  በዚህ ብቻ ሳይሆን በመከራ ውስጥ እያለንም እጅግ እንደሰት፤*+ ምክንያቱም መከራ ጽናትን እንደሚያስገኝ እናውቃለን፤+  ጽናትም በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንድናገኝ+ ያስችለናል፤ ተቀባይነት ማግኘት ደግሞ ተስፋን+ ያጎናጽፋል፤  ተስፋውም ሳይፈጸም ቀርቶ ለሐዘን* አይዳርገንም፤+ ምክንያቱም የአምላክ ፍቅር፣ በተሰጠን መንፈስ ቅዱስ አማካኝነት በልባችን ውስጥ ፈሷል።+  ገና ደካሞች ሳለን+ ክርስቶስ አስቀድሞ የተወሰነው ጊዜ ሲደርስ ለኃጢአተኞች ሞቷልና።  ለጻድቅ ሰው የሚሞት ማግኘት በጣም አዳጋች ነው፤ ለጥሩ ሰው ለመሞት የሚደፍር ግን ምናልባት ይገኝ ይሆናል።  ሆኖም አምላክ ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ እንዲሞትልን በማድረግ ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር አሳይቷል።+  ከእንግዲህ በደሙ ጻድቃን ናችሁ ስለተባልን+ በእሱ አማካኝነት ከአምላክ ቁጣ እንደምንድን ይበልጥ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።+ 10  ጠላቶች ሆነን ሳለን በልጁ ሞት አማካኝነት ከአምላክ ጋር ከታረቅን አሁን ታርቀን ሳለንማ+ በእሱ ሕይወት እንደምንድን የተረጋገጠ ነው። 11  ይህም ብቻ ሳይሆን አሁን እርቅ ባገኘንበት+ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት በአምላክ ሐሴት እያደረግን ነው። 12  ስለሆነም በአንድ ሰው አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤+ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ፤ ሁሉም ኃጢአት ስለሠሩም ሞት ለሰው ሁሉ ተዳረሰ።+ 13  ሕጉ ከመሰጠቱ በፊት ኃጢአት በዓለም ላይ ነበርና፤ ሆኖም ሕግ በሌለበት ማንም በኃጢአት አይጠየቅም።+ 14  ይሁንና አዳም ትእዛዝ በመተላለፍ የሠራውን ዓይነት ኃጢአት ባልሠሩት ላይም እንኳ ሳይቀር ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ ድረስ ሞት በሁሉ ላይ ነገሠ፤ አዳም በኋላ ለሚመጣው አምሳያ ነበር።+ 15  ሆኖም ስጦታው ያስገኘው ነገር በደሉ ካስከተለው ነገር የተለየ ነው። ምክንያቱም በአንድ ሰው በደል ብዙዎች ሞተዋል፤ ይሁንና የአምላክ ጸጋና ነፃ ስጦታው በአንዱ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ+ አማካኝነት ለብዙ ሰዎች ወደር የሌለው* ጥቅም አስገኝቷል!+ 16  በተጨማሪም ነፃ ስጦታው ያስገኘው ውጤት የአንዱ ሰው ኃጢአት+ ካመጣው ውጤት የተለየ ነው። ምክንያቱም አንድን በደል ተከትሎ የመጣው ፍርድ ኩነኔን አስከትሏል፤+ ብዙዎች በደል ከፈጸሙ በኋላ ግን አምላክ ጻድቃን እንዲባሉ የሚያስችል ስጦታ ሰጥቷል።+ 17  በአንድ ሰው በደል የተነሳ ሞት በዚህ ሰው በኩል ከነገሠ+ የአምላክን የተትረፈረፈ ጸጋና የጽድቅን ነፃ ስጦታ የሚቀበሉትማ+ በአንዱ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት+ ሕይወት አግኝተው ነገሥታት+ ሆነው እንደሚገዙ ይበልጥ የተረጋገጠ ነው! 18  ስለዚህ አንድ በደል ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲኮነኑ እንዳደረገ ሁሉ+ አንድ የጽድቅ ድርጊትም* ሁሉም ዓይነት ሰዎች ጻድቃን ናችሁ ተብለው ለሕይወት እንዲበቁ ያስችላል።+ 19  ምክንያቱም በአንዱ ሰው አለመታዘዝ ብዙዎች ኃጢአተኞች እንደሆኑ ሁሉ+ በአንዱ ሰው መታዘዝም ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ።+ 20  ሕጉ የመጣው ሰዎች ብዙ በደል እንደሚፈጽሙ ለማሳየት ነው።+ ይሁን እንጂ ሰዎች ብዙ ኃጢአት ሲፈጽሙ አምላክ ታላቅ ጸጋ አሳያቸው። 21  ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ኃጢአት ከሞት ጋር እንደነገሠ+ ሁሉ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የዘላለም ሕይወት ይገኝ ዘንድ ጸጋ በጽድቅ አማካኝነት እንዲነግሥ ነው።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

“ከአምላክ ጋር ሰላም አለን” ማለትም ሊሆን ይችላል።
“እጅግ እንደሰታለን” ማለትም ሊሆን ይችላል።
“እጅግ እንደሰታለን” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ለኀፍረት።”
ወይም “የተትረፈረፈ።”
ወይም “ከበደል ነፃ የሚያደርግ አንድ ድርጊትም።” ሰዎች ጻድቃን እንዲባሉ የሚያስችል ድርጊት ማለት ነው።