በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ ሥቃያችን ይሰማዋል?

አምላክ ሥቃያችን ይሰማዋል?

ከሰዎች አፈጣጠር ምን እንማራለን?

የሌላውን ሰው ችግር እንደ ራሳችን የምንመለከት ከሆነ ራሳችንን በዚያ ሰው ቦታ ላይ አስቀምጠን በማሰብ ያ ሰው የተሰማውን ስሜት ወይም ያጋጠመውን ሁኔታ እንጋራለን። የአእምሮ ጤና ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ሪክ ሀንሰን “የሌላውን ችግር እንደ ራስ አድርጎ የመመልከት ችሎታ በደማችን ውስጥ ያለ ነገር ነው” በማለት ተናግረዋል።

እስቲ አስበው፦ በምድር ላይ ካሉ ፍጥረታት መካከል የሌላውን ችግር እንደ ራሱ አድርጎ የመመልከት ችሎታ ያለው ፍጡር የለም፤ ታዲያ እኛ ይህ ችሎታ ሊኖረን የቻለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ዘር በአምላክ መልክ እንደተፈጠረ ይናገራል። (ዘፍጥረት 1:26) በአምላክ መልክ ተፈጥረናል ሲባል የአምላክን ግሩም ባሕርያት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የማንጸባረቅ ችሎታ አለን ማለት ነው። በመሆኑም አዛኝ የሆኑ ሰዎች የሌሎችን ችግር እንደ ራሳቸው አድርገው በመቁጠር ሰዎችን ለመርዳት የሚነሳሱት ሩኅሩኅ የሆነው ፈጣሪያቸው ይሖዋ አምላክ፣ እንደዚያ ዓይነት ባሕርይ ስላለው ነው።—ምሳሌ 14:31

መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ሥቃያችን እንደሚሰማው የሚያሳይ ምን ማስረጃ ይዟል?

አምላክ ሥቃያችን የሚሰማው ከመሆኑም ሌላ ችግር ሲደርስብን ማየት አይፈልግም። በግብፅ ውስጥ በከባድ ባርነት ከኖሩ በኋላ በበረሃ ለ40 ዓመት ያህል እንግልት የደረሰባቸውን የጥንቶቹን እስራኤላውያን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ “በጭንቃቸው ሁሉ እሱ ተጨነቀ” በማለት ይናገራል። (ኢሳይያስ 63:9) ይህ ጥቅስ አምላክ የእስራኤላውያንን ጭንቀት ያውቅ እንደነበረ ብቻ እንደማይገልጽ ልብ በል። ከዚህ ይልቅ ጭንቀታቸው ተሰምቶት ነበር። “እየደረሰባቸው ያለውን . . . ሥቃይ በሚገባ አውቃለሁ” በማለት ተናግሯል። (ዘፀአት 3:7) በተጨማሪም “እናንተን የሚነካ ሁሉ የዓይኔን ብሌን ይነካል” ብሏል። (ዘካርያስ 2:8) ሌሎች በእኛ ላይ ሥቃይ ሲያደርሱብን እሱም አብሮን ይሠቃያል።

ራሳችንን ልንኮንንና የአምላክ ርኅራኄ እንደማይገባን ሊሰማን ቢችልም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነው፤ ደግሞም ሁሉንም ነገር ያውቃል” የሚል ማጽናኛ ይሰጠናል። (1 ዮሐንስ 3:19, 20) አምላክ እኛ ራሳችንን ከምናውቀው በላይ ያውቀናል። ያለንበትን ሁኔታ፣ ሐሳባችንንና ስሜታችንን ሁሉ ጠንቅቆ ያውቃል። እንዲሁም በእኛ ላይ የደረሰው ነገር በእሱ ላይ የደረሰ ያህል ሥቃያችን ይሰማዋል።

አምላክ ለተጨነቁ ሰዎች እንደሚደርስላቸው ስለምናውቅ መጽናኛ፣ ጥበብና ድጋፍ ለማግኘት ወደ እሱ መጠጋት እንችላለን

መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ማረጋገጫ

  • “ትጣራለህ፤ ይሖዋም ይመልስልሃል፤ እርዳታ ለማግኘት ትጮኻለህ፤ እሱም ‘አለሁልህ!’ ይልሃል።”—ኢሳይያስ 58:9

  • “‘ለእናንተ የማስበውን ሐሳብ በሚገባ አውቀዋለሁና’ ይላል ይሖዋ፤ ‘ለእናንተ የማስበው ጥፋትን ሳይሆን ሰላምን እንዲሁም የተሻለ ሕይወትንና ተስፋን ነው። እናንተም ትጠሩኛላችሁ፤ ወደ እኔም ቀርባችሁ ትጸልያላችሁ፤ እኔም እሰማችኋለሁ።’”—ኤርምያስ 29:11, 12

  • “እንባዬን በአቁማዳህ አጠራቅም። ደግሞስ በመጽሐፍህ ውስጥ ሰፍሮ የለም?”—መዝሙር 56:8

አምላክ ትኩረት ይሰጠናል፣ ስሜታችንን ይረዳልናል እንዲሁም ይራራልናል

አምላክ ሥቃያችን እንደሚሰማው ማወቃችን የሚደርስብንን መከራ ለመቋቋም ሊረዳን ይችላል? ማሪያ ያጋጠማትን ሁኔታ እንመልከት፦

“የ18 ዓመት ልጄ ለሁለት ዓመታት ያህል ከካንሰር ጋር ሲታገል ከቆየ በኋላ ሲሞት በከፍተኛ ሐዘን ስለተዋጥኩ ሕይወት መራራና ፍትሕ የጎደለው እንደሆነ ተሰማኝ። ይሖዋ ጣልቃ ገብቶ ልጄን ስላላዳነልኝ በእሱ ላይ ተበሳጨሁ!

“ከስድስት ዓመታት በኋላ፣ እኔ ባለሁበት ጉባኤ ውስጥ ያለች አንዲት አፍቃሪና ሩኅሩኅ እህት ይሖዋ ይወደኛል የሚል ስሜት እንደሌለኝ ስነግራት በጥሞና አዳመጠችኝ። ምንም ሳታቋርጠኝ ለሰዓታት ካዳመጠችኝ በኋላ አንድ ልብ የሚነካ ጥቅስ ጠቀሰችልኝ፤ ጥቅሱ በ1 ዮሐንስ 3:19, 20 ላይ የሚገኝ ሲሆን ‘አምላክ ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነው፤ ደግሞም ሁሉንም ነገር ያውቃል’ ይላል። ይሖዋ ጭንቀታችንን እንደሚረዳልን ገለጸችልኝ።

“ያም ሆኖ ብስጭቴ አልወጣልኝም ነበር! ከዚያም በመዝሙር 94:19 ላይ የሚገኘውን ‘በጭንቀት በተዋጥኩ ጊዜ፣ አጽናናኸኝ፤ ደግሞም አረጋጋኸኝ’ የሚለውን ጥቅስ አነበብኩ። ጥቅሱ ለእኔ ተብሎ እንደተጻፈ ተሰማኝ! ውሎ አድሮም ይሖዋ እንደሚያዳምጠኝና ስሜቴን እንደሚረዳልኝ ስለተገነዘብኩ ጭንቀቴን ለእሱ መናገር መቻሌ የመረጋጋት ስሜት እንዲሰማኝ አድርጓል።”

አምላክ ስሜታችንን እንደሚረዳልንና እንደሚራራልን ማወቅ ምንኛ የሚያጽናና ነው! ታዲያ አምላክ ስለ እኛ እንዲህ የሚሰማው ከሆነ ይህ ሁሉ መከራ የሚደርስብን ለምንድን ነው? አምላክ ለሠራነው ጥፋት እየቀጣን ስለሆነ ነው? አምላክ ማንኛውንም ዓይነት መከራ ለማስወገድ እርምጃ ይወስድ ይሆን? እነዚህ ጥያቄዎች በቀጣዮቹ ርዕሶች ላይ መልስ ያገኛሉ።