በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ፍቅር ለማሳየት ጥረት አድርግ

ፍቅር ለማሳየት ጥረት አድርግ

እንዲህ አለማድረግ ምን ችግር አለው?

ጭፍን ጥላቻ በአንዴ ከውስጣችን አይወገድም። አንድን ቫይረስ ለማጥፋት ጊዜና ጥረት እንደሚጠይቅ ሁሉ ጭፍን ጥላቻን ለማጥፋትም ጊዜና ጥረት ይጠይቃል። ታዲያ ጭፍን ጥላቻን ለማስወገድ ምን ማድረግ ትችላለህ?

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ

“ፍቅርን ልበሱ፤ ፍቅር ፍጹም የሆነ የአንድነት ማሰሪያ ነውና።”—ቆላስይስ 3:14

ከዚህ ጥቅስ ምን ትምህርት እናገኛለን? የደግነት ተግባር ሰዎችን እርስ በርስ ያቀራርባል። ለሌሎች ፍቅር ባሳየህ መጠን በውስጥህ ያለው ጭፍን ጥላቻም የዚያኑ ያህል ይቀንሳል። ለሰዎች ያለህ ፍቅር እየጨመረ ከሄደ ጥላቻ ወይም ንቀት በልብህ ውስጥ ቦታ አያገኙም።

ምን ማድረግ ትችላለህ?

በጭፍን ለምትጠላቸው ሰዎች ፍቅር ማሳየት የምትችልባቸውን አንዳንድ መንገዶች አስብ። ትልቅ ነገር ማድረግ እንዳለብህ ሊሰማህ አይገባም። ከሚከተሉት ነገሮች መካከል ቢያንስ አንዱን ለማድረግ ሞክር፦

ፍቅር ለማሳየት ስትል የምታደርገው ትንሹ ነገር ጭፍን ጥላቻን በማስወገድ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል

  • በር ከፍተህ በመያዝ ወይም በሕዝብ መጓጓዣ ላይ ወንበርህን በመልቀቅ ጥሩ ምግባር አሳይ።

  • የአንተን ቋንቋ ጥርት አድርገው መናገር ባይችሉም እንኳ ከእነሱ ጋር ለመጨዋወት ጥረት አድርግ።

  • ግራ የሚገባህ ነገር በሚያደርጉበት ጊዜ በትዕግሥት ለማለፍ ሞክር።

  • ስላስጨነቋቸው ነገሮች ሲነግሩህ በአዘኔታ ስሜት አዳምጣቸው።