በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ተጨማሪ ጊዜ ለማግኘት የሚረዱ 20 መንገዶች

ተጨማሪ ጊዜ ለማግኘት የሚረዱ 20 መንገዶች

ቆርጠህ ተጠቀምበት

ተጨማሪ ጊዜ ለማግኘት የሚረዱ 20 መንገዶች

“አመቺ የሆነውን ጊዜ ለራሳችሁ በመግዛት . . . በጥበብ መመላለሳችሁን ቀጥሉ።”—ቆላስይስ 4:5

በእያንዳንዱ ቀንና ሰዓት ምን ነገሮችን እንደምታደርግ ለይተህ ካወቅህ በኋላ ተፈታታኝ የሆነው ነገር እቅድህን ወደ ተግባር መለወጡ ነው። ቀጥሎ የቀረቡት ሐሳቦች ይህን እንድታደርግ ሊረዱህ ይችላሉ።

1 በየዕለቱ የምትሠራቸውን ነገሮች በዝርዝር ጻፍ። የምታከናውናቸውን ነገሮች በጊዜ ቅደም ተከተል አስፍራቸው። ሰፋ ያለ ጊዜ በሚጠይቁ ሥራዎች ላይ ምልክት አድርግ። እያንዳንዱን ሥራ ሠርተህ ስታጠናቅቅ ምልክት አድርግበት። ያልተጠናቀቁ ሥራዎችን በማግስቱ በምትሠራቸው ሥራዎች ዝርዝር ውስጥ አካትታቸው።

2 በሁሉም ማስታወሻዎችህ ላይ የምታሰፍረው መረጃ አንድ ዓይነት እንዲሆኑ አድርግ። አንዳንድ ቀጠሮዎችህን በሌላ ማስታወሻ ላይ ባለመመዝገብህ ምክንያት ቀጠሮ እንዳትዘነጋ ተጠንቀቅ። ልታስታውሰው የምትፈልገው ነገር በኮምፒውተርህና በእጅህ በምትይዘው ማስታወሻህ ላይ የምትመዘግብ ከሆነ ሁለቱም ላይ መጻፍህን አትርሳ።

3 “የድርጊት መርሐ ግብር” ይኑርህ። ይህ መርሐ ግብር አንድን ውጥን ከግብ ለማድረስ መከናወን ያለባቸውን ዝርዝር ነገሮችን ያካተተ ይሁን፤ እነዚህን ነገሮች በቅደም ተከተል ጻፋቸው።

4 በአብዛኛው ይበልጥ አስፈላጊ ናቸው የምትላቸውን ሥራዎች አስቀድም። እንዲህ ማድረግህ እምብዛም አስፈላጊ ላልሆኑ ሥራዎች ጊዜ ማግኘቱን ቀላል ያደርግልሃል።

5 ልትደርስባቸው የምትችላቸውን ግቦች አውጣ። በቀላሉ የሚደረስበት ግብ የሚባለው በምትሠራበት ድርጅት ውስጥ ሥራ አስኪያጅ መሆን ሳይሆን በአንድ ሥራ ላይ ችሎታህን ማሻሻል ነው።

6 ለሁሉም ነገር ጊዜ እንደማታገኝ አምነህ ተቀበል። ጥሩ ውጤት ለሚያስገኙ እንቅስቃሴዎች የበለጠ ጊዜ ስጥ። አስቸኳይ የሆኑ ወይም የግድ መሠራት ያለባቸውን ሥራዎች በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? እነዚህን ሥራዎች መተው ወይም ሌላ ሰው እንዲረዳህ ማድረግ የማትችል ከሆነ ቶሎ ልትሠራቸው የምትችልባቸውን መንገዶች ፈልግ። እምብዛም አስፈላጊ ያልሆኑ አንዳንድ ሥራዎች ካስፈለገ ለወራት ሊቆዩ ይችላሉ፤ አለዚያም ጭራሹኑም መሠራት ላያስፈልጋቸው ይችላል። ከግብህ አንጻር በጣም አስፈላጊ ናቸው ለምትላቸው ሥራዎች በተቻለ መጠን ሰፋ ያለ ጊዜ መድብ።

7 ጊዜህን ምን በማድረግ እንዳሳለፍክ በማስታወሻህ ላይ ጻፍ። ጊዜህ እንዴት እንዳለፈ ለማወቅ ለአንድ ወይም ለሁለት ሳምንታት ተከታትለህ ጻፍ። አብዛኛው ጊዜህ የጠፋው አስፈላጊ ባልሆኑ እንቅስቃሴዎች ነው? ብዙ ጊዜ የምታደርገውን ነገር የሚያስተጓጉልብህ አንድ ሰው ነው ወይስ የተለያዩ ሰዎች ናቸው? እንቅስቃሴህን የሚያስተጓጉል ነገር የሚገጥምህ በቀኑ ወይም በሳምንቱ ውስጥ በተወሰነ ጊዜ ላይ ነው? ጊዜህን የሚያባክኑ አላስፈላጊ እንቅስቃሴዎችን አስወግድ።

8 የተወሰኑ ነገሮችን ለማድረግ እቅድ አውጣ። በአንድ ቀን ውስጥ ገበያ ለመውጣት፣ መኪና ለማሠራት፣ እንግዳ ለመጋበዝ፣ ፊልም ለማየትና ለማንበብ እቅድ የምታወጣ ከሆነ ውጥረት የሚበዛብህ ከመሆኑም በላይ በአንዱም ሳትደሰት ትቀራለህ።

9 የሚያስተጓጉሉብህን ነገሮች ቀንስ። በጣም አስፈላጊ ካልሆነ በቀር ያለ ምንም መስተጓጎል ያሰብከውን ሥራ ማከናወን የምትችልበትን የተወሰነ ጊዜ መድብ። ከተቻለ በዚህ ጊዜ ስልክህን አጥፋ። በተጨማሪም ሥራህን እንዳያስተጓጉሉብህ መልእክት መላላኪያ ፕሮግራሞችን አጥፋ።

10 ይበልጥ ተፈታታኝ የሚሆንብህን ሥራ በቀኑ ውስጥ ብርታትና ንቃት በሚኖርህ ሰዓት ላይ ለመሥራት ፕሮግራም አውጣ።

11 በጣም ደስ የማይልህን ሥራ በተቻለ መጠን ቶሎ ብለህ ሥራ። ይህን ሥራ ከተገላገልክ እምብዛም ተፈታታኝ ያልሆኑ ሥራዎችን ለመሥራት የበለጠ ብርታት ታገኛለህ።

12 ላልተጠበቁ ነገሮች ጊዜ መድብ። አንድ ቦታ በ15 ደቂቃ ውስጥ መድረስ እንደምትችል ከተሰማህ በ25 ደቂቃ ውስጥ እንደምትደርስ ተናገር። አንድ ሰዓት የሚወስድ ፕሮግራም ካለህ አንድ ሰዓት ከ20 ደቂቃ ሊፈጅ እንደሚችል አድርገህ አስብ። በቀኑ ውስጥ የተወሰነውን ክፍል ምንም ፕሮግራም አትያዝበት።

13 በፕሮግራሞችህ መካከል ያለውን ጊዜ በጥሩ ሁኔታ ተጠቀምበት። ጺምህን በምትላጭበት ጊዜ ዜና ወይም የተቀዳ ነገር አዳምጥ። ትራንስፖርት ስትጠብቅ ወይም በጉዞ ላይ አንድ ነገር አንብብ። እርግጥ ነው፣ ያንን ጊዜ ለመዝናናትም ልትጠቀምበት ትችላለህ። ነገር ግን ካለፈ በኋላ እንዳይቆጭህ ጊዜህን አታባክን።

14 በተለምዶ 80/20 ተብሎ የሚጠራውን ደንብ ተከተል። * ለመሥራት በዝርዝር ከያዝካቸው 10 ነገሮች መካከል ይበልጥ ወሳኝ የሆኑት 2 ብቻ ይሆኑ? አንድን ሥራ ስታከናውን ይበልጥ ወሳኝ የሆነውን ክፍል ትኩረት ሰጥተህ ብትሠራው ሥራው በአብዛኛው እንደተጠናቀቀ ሊቆጠር ይችላል?

15 ሥራ በጣም እንደበዛብህ ከተሰማህ እያንዳንዱን ሥራ በትንሽ ወረቀት ላይ ጻፍ። ከዚያም ወረቀቶቹን “ዛሬ የሚሠራ” እና “ነገ የሚሠራ” በማለት በሁለት ክፈላቸው። በማግስቱም ያንኑ አድርግ።

16 በየመሃሉ ኃይልህን ማደስ የምትችልበትን ጊዜ መድብ። ረጅም ሰዓት ያለ እረፍት ከመሥራት ይልቅ አእምሮህና ሰውነትህ ታድሶ ወደ ሥራ መመለሱ ይበልጥ ውጤታማ ሊሆን ይችላል።

17 የከበደህን ነገር ለመፍታት ወረቀት ተጠቀም። አንድን ችግር በወረቀት ላይ አስፍር። ከዚያም ይህ ችግር የሚረብሽህ ለምን እንደሆነ ግለጽ፤ እንዲሁም ወደ አእምሮህ የመጣልህን የመፍትሔ ሐሳብ ሁሉ ዘርዝር።

18 ከራስህ ፍጽምና አትጠብቅ። የጀመርከውን ሥራ አቁመህ ቀጣዩን አስፈላጊ ሥራ መጀመር የሚኖርብህ መቼ እንደሆነ እወቅ።

19 ግዴታህ እንደሆነ አድርገህ በማሰብ ሥራ። አንድን ሥራ በቀጥታ መሥራት ጀምር እንጂ ልብህ እስኪያነሳሳህ ድረስ አትጠብቅ።

20 ምክንያታዊ ሁን። እዚህ ላይ የቀረቡት ነጥቦች የመፍትሔ ሐሳቦች እንጂ የማይለወጡ ሕጎች አይደሉም። ሞክራቸውና የትኞቹ ነጥቦች ለአንተ እንደሚሠሩ ገምግም፤ ከአንተ ሁኔታ ጋር እንዲስማሙ ለማድረግ አስፈላጊውን ማስተካከያ አድርግ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.18 ይህ ሐሳብ በአብዛኛው የተመሠረተው በ19ኛው መቶ ዘመን የኖረው ቪልፍሬዶ ፓሬቶ የተባለ ጣሊያናዊ ኢኮኖሚስት ባወጣው ደንብ ላይ ነው፤ ይህ ደንብ የፓሬቶ መመሪያ ተብሎም ይጠራል። ይህ ደንብ አንድን ሥራ ስናከናውን 20 በመቶ ለሚያህለው የሥራው ክፍል ትኩረት በመስጠት አብዛኛውን ጊዜ 80 በመቶ የሚሆን ውጤት ማግኘት እንደሚቻል የሚገልጸውን ሐሳብ የያዘ ነው። ደንቡ ለብዙ ነገሮች ይሠራል፤ ቀለል ባለ ምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ አንድን ምንጣፍ በአቧራ ማንሻ ማሽን ስናጸዳ እግር የሚበዛበትን 20 በመቶ የሚሆነውን የምንጣፉን ክፍል በማጽዳት ብቻ 80 በመቶ የሚሆነውን ቁሻሻ ማንሳት እንችላለን።