በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጊዜህን በጥሩ ሁኔታ ተጠቀምበት

ጊዜህን በጥሩ ሁኔታ ተጠቀምበት

ጊዜህን በጥሩ ሁኔታ ተጠቀምበት

“ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው።”—መክብብ 3:1

ይበልጥ አስፈላጊ ለሆኑ ነገሮች ጊዜ ለማግኘት በመጀመሪያ እነዚህን ነገሮች ለይተህ ማወቅ ያስፈልግሃል። ከፍ ያለ ግምት የምትሰጣቸውን ነገሮች፣ ግቦችህንና እነዚህ ግቦች ላይ ለመድረስ ማድረግ ያለብህን ነገር የምታውቅ ከሆነ ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ማወቅ አይሳንህም።

እንግዲያው በመጀመሪያ ከፍ ያለ ግምት የምትሰጣቸውን ነገሮች ለይተህ እወቅ። ቶሎ ወደ አእምሮህ የሚመጡልህን ለምሳሌ እንደ ቤተሰብ፣ ወዳጅነት፣ ሥራ፣ ትምህርት፣ ስኬት፣ ጥሩ ቁመና፣ ገንዘብ፣ ደስታ፣ ትዳር፣ ልግስና፣ ጤንነት፣ ሃይማኖት ያሉትን ከፍ ያለ ግምት የምትሰጣቸውን ነገሮች በዝርዝር ለመጻፍ ሞክር። ከዚያም ‘ከእነዚህ መካከል ለእኔ ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑት የትኞቹ ናቸው?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ።

ከዚያም በሕይወትህ ውስጥ ልትደርስባቸው የምትፈልጋቸውን ግቦች በሙሉ አስብ። ከፍ ያለ ግምት በሚሰጣቸው ነገሮችና በግቦች መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? ከምንነጋገርበት ርዕሰ ጉዳይ አንጻር ከፍ ያለ ግምት የሚሰጣቸው ነገሮች የሚባሉት ቀጣይነት ያላቸው ሲሆኑ ግቦች ደግሞ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የሚደረስባቸው ነገሮች ናቸው ብለን መናገር እንችላለን።

ለራስህ ምን ግብ ልታወጣ ትችላለህ? የምትፈልገው ምንድን ነው? ከቤተሰብህ ጋር የበለጠ ጊዜ ማሳለፍ? ይበልጥ ተስማሚ የሆነ ሥራ ማግኘት? በትርፍ ጊዜ በምትሠራቸው ነገሮች ረገድ ያለህን ችሎታ ማሻሻል? ሌላ የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያ ማግኘት? አንድን ባሕርይ ማዳበር? ለእረፍት ወጣ ማለት? መጽሐፍ ማንበብ ወይስ መጻፍ?

ቀጥሎ ከእነዚህ ግቦች መካከል ይበልጥ ያስፈልጉኛል የምትላቸውን ወስን። እነዚህ ግቦች ከፍ ያለ ግምት ከምትሰጣቸው ነገሮች ጋር የማይጋጩ መሆናቸውን አረጋግጥ። ለምሳሌ ያህል፣ የናጠጠ ሀብታም ለመሆን ግብ ብታወጣ ጣጣ ውስጥ ልትገባ ትችላለህ።

ከዚያም በመረጥከው በእያንዳንዱ ግብ ላይ ለመድረስ ምን እርምጃዎችን መውሰድ እንደምትችል አስብ። ለምሳሌ ያህል፣ የተወሰነ ክብደት የመቀነስ ግብ ካለህ እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ ከሚረዱህ እርምጃዎች አንዱ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ነው።

በዝርዝር መጻፍህ የሚረዳህ እንዴት ነው?

ግቦችህ ከፍ ያለ ግምት ከምትሰጣቸው ነገሮች ጋር የሚስማሙ ከሆኑና ግቦችህ ላይ ለመድረስ የሚረዱህን እርምጃዎች የምትወስድ ከሆነ ሕይወትህ ወጥ ይሆናል። እንዲሁም ይበልጥ ለሚያስፈልግህ ነገር ሰፋ ያለ ጊዜ ትሰጣለህ። ይህ ሲባል ግን ለሌሎች ሰዎች ፍላጎት ደንታ ቢስ ትሆናለህ ማለት አይደለም። (ፊልጵስዩስ 2:4) ከዚህ ይልቅ ይበልጥ አስፈላጊ ከሆኑ ነገሮች ጋር ግንኙነት የሌላቸውን ነገሮች ማወቅና እነዚህን ነገሮች ከማድረግ መቆጠብ ትችላለህ ማለት ነው።

እርግጥ ነው፣ ይህን ማድረግ ተፈታታኝ ነው። አንዳንድ ሥራዎች በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታዩ እምብዛም አስፈላጊ ባይሆኑም የግድ መሠራት አለባቸው። እነዚህ ሥራዎች አንተ ይበልጥ አስፈላጊ ናቸው ለምትላቸው ነገሮች የምታውለውን ጊዜ በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ሊሻሙብህ ይችላሉ። ድንገተኛ የሆኑ ነገሮችም ሊከሰቱ ይችላሉ። እንዲሁም በሕይወትህ ውስጥ የሚያጋጥሙህ ለውጦች ሚዛንህን እንድትስትና በፕሮግራምህ መሠረት እንዳትሄድ ሊያደርጉህ ይችላሉ። ይሁንና ይበልጥ አስፈላጊ ለሆኑ ነገሮች ተጨማሪ ጊዜ ለመመደብ ተግባራዊ የሆኑ እርምጃዎችን በመውሰድ ጊዜህን ለምን ነገር ማዋል ብሎም ሕይወትህን እንዴት መምራት እንዳለብህ መወሰን ትችላለህ።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የኤሌክትሮኒክ ማስታወሻ መመዝገቢያ ጊዜ ይቆጥባል?

ለአንዳንድ ሰዎች ጊዜ ሲቆጥብ ለሌሎች ግን ጊዜ ያባክንባቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ፒ ዲ ኤ የሚባለው የግል ማስታወሻ መያዣ ከሚያካትታቸው ነገሮች ውስጥ ቀን መቁጠሪያ፣ ስልክ ቁጥሮችና አድራሻዎች፣ የሚሠሩ ነገሮች ዝርዝር፣ የወርድ ፕሮግራም፣ ማስታወሻ መጻፊያ፣ ካሜራ እንዲሁም ኢ-ሜይልና ኢንተርኔት ይገኙበታል። በዚህ መሣሪያ ላይ የምትጽፋቸው መረጃዎች ወቅታዊ ከሆኑና መሣሪያው ከአንተ የማይለይ ከሆነ ጊዜ ሊቆጥብልህ ይችላል። ይሁን እንጂ ይህን መሣሪያ ሳያስፈልግ የምትጎረጉር ወይም አላስፈላጊ መለዋወጫዎችን የምትገዛ አሊያም በዚህ መሣሪያ መጠቀምህ ሌሎችን ችላ እንድትል ወይም ኃላፊነትህን በአግባቡ እንዳትወጣ የሚያደርግህ ከሆነ ጊዜህ በቀላሉ ሊባክን ይችላል።

ተጨማሪ ምክር፦ መሣሪያውን ከመግዛትህ በፊት ምርምር አድርግ። የኤሌክትሮኒክ መሣሪያው ቶሎ ቶሎ የሚበላሽ ከሆነ መጠገኑ ብዙ ጊዜ ይወስድብሃል። በተጨማሪም ማንኛውም የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ጥሩ ጥቅም መስጠቱ የተመካው በተጠቃሚው ላይ ነው። ስለዚህ እንዲህ ዓይነት መሣሪያ ካለህ ጊዜህን ለማባከን ሳይሆን ጊዜህን ለመቆጠብ ተጠቀምበት።

[በገጽ 4, 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይበልጥ አስፈላጊ ለሆኑት ነገሮች ጊዜ ማመቻቸት ትችላለህ?