በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ተጠያቂው ሃይማኖት ነው?

ተጠያቂው ሃይማኖት ነው?

ተጠያቂው ሃይማኖት ነው?

በ18ኛው መቶ ዘመን ደራሲ የነበሩት ቄስ ጆናታን ስዊፍት “እርስ በርስ እንድንጠላላ እንጂ እንድንዋደድ የሚያደርግ ሃይማኖት የለንም” በማለት ጽፈዋል። ብዙ ሰዎች ሃይማኖት አንድነት የሚያመጣ ኃይል ሳይሆን የመከፋፈል ምክንያት እንደሆነ በመግለጽ ይከራከራሉ። ይሁን እንጂ በዚህ አባባል የሚስማሙት ሁሉም አይደሉም።

ለምሳሌ ያህል፣ በዩናይትድ ኪንግደም በሚገኝ ብራድፎርድ በተባለ አንድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ስለ ሰላም ጥናት በሚያደርግ ዲፓርትመንት ውስጥ የሚሠራው የተመራማሪዎች ቡድን የደረሰበትን መደምደሚያ ተመልከት። ይህ ቡድን ‘ሃይማኖት ለሰላም የቆመ ኃይል ነው ወይስ ለጦርነት?’ ለሚለው ጥያቄ ትክክለኛ መልስ እንዲያገኝ በቢቢሲ የዜና ኮርፖሬሽን ተልእኮ ተሰጥቶት ነበር።

ተመራማሪዎቹ ለኅትመት ባበቁት ሪፖርት ላይ እንዲህ ብለዋል፦ “የተለያዩ ባለሙያዎች ያቀረቧቸውን ታሪካዊ ትንተናዎች ከመረመርን በኋላ ባለፉት 100 ዓመታት ውስጥ በሃይማኖት ምክንያት የተደረጉት ጦርነቶች ጥቂት እንደሆኑ ስምምነት ላይ ደርሰናል።” የተመራማሪዎቹ ቡድን እንደገለጸው “መገናኛ ብዙኃንና ሌሎች ወገኖች [አንዳንድ ጦርነቶችን] የሃይማኖት ጦርነት ወይም በሃይማኖት ልዩነት ምክንያት የተቀሰቀሱ ጦርነቶች እንደሆኑ አድርገው ቢገልጿቸውም ሐቁ የሚያሳየው ግን ጦርነቶቹ በብሔራዊ ስሜት እንዲሁም ድንበርን ለማስከበር ወይም ራስን ለመከላከል በሚል ሰበብ የተደረጉ ናቸው።”

ይሁን እንጂ ከዚህ በታች የቀረቡት አስተያየቶች እንደሚጠቁሙት ሌሎች ብዙ ሰዎች ደግሞ ቀሳውስት በጦር መሣሪያ የተካሄዱ በርካታ ጦርነቶችን እንደፈቀዱና ሙሉ ድጋፋቸውን እንደሰጡ በመጥቀስ ይከራከራሉ፤ ቀሳውስቱ ድጋፍ የሰጡት በተግባር ወይም ጦርነቱን ባለመቃወም ነው።

● “ሃይማኖት በየቦታው ከሚካሄደው ግጭት ጋር ግንኙነት ያለው ይመስላል። . . . ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ባሉ ወግ አጥባቂ ክርስቲያኖች፣ በመካከለኛው ምሥራቅ በቁጣ በገነፈሉ ሙስሊሞችና አይሁዶች፣ በደቡብ እስያ ምንጊዜም በማይስማሙት ሂንዱዎችና ሙስሊሞች፣ በአፍሪካና በኢንዶኔዥያ ደግሞ በአካባቢው ባሉ ባሕላዊ ሃይማኖቶች መካከል ግጭት ተቀስቅሶ ነበር። . . . በእነዚህ ግጭቶች ውስጥ ተካፋይ የሆኑት ግለሰቦች ፖለቲካዊ ዓላማቸውን ለማራመድ ብሎም በቀልን መርህ ያደረገው አስተሳሰባቸው እውቅና እንዲያገኝ ለማድረግ ሃይማኖትን መሣሪያ አድርገው ተጠቅመዋል።”—ቴረር ኢን ዘ ማይንድ ኦቭ ጎድ—ዘ ግሎባል ራይዝ ኦቭ ሪሊጂየስ ቫዮለንስ

● “የሚገርመው ነገር፣ ብዙውን ጊዜ ዘግናኝ የሆነ የክፋት ድርጊት ሲፈጸም የሚታየው ቀናዒ ሃይማኖተኞች በበዙባቸው አገሮች ውስጥ ነው። . . . ሃይማኖት መብዛቱ የሚፈጸመውን ከባድ ወንጀል መጠን ለመቀነስ አላስቻለም። . . . ነጥቡ ግልጽ ነው፦ ደኅንነቱ በተጠበቀ፣ ክቡርና ሥርዓታማ በሆነ እንዲሁም ‘በሠለጠነ’ አካባቢ መኖር የምትፈልግ ከሆነ አጥባቂ ሃይማኖተኝነት ከሚንጸባረቅበት ስፍራ ራቅ።”—ሆሊ ሄትረድ

● “ባፕቲስቶች በአብዛኛው የሚታወቁት ሰላም በመፍጠር ሳይሆን በተዋጊነታቸው ነው። . . . በአሥራ ዘጠነኛው መቶ ዘመን የተለያዩ ሃይማኖቶች ብሎም በአገሪቱ [በአሜሪካ] በነበረው ባርነትና በሌሎች ሁኔታዎች የተነሳ ክፍፍል በተፈጠረበት ጊዜ በሰሜንም ሆነ በደቡብ የነበሩ ባፕቲስቶች ጦርነቱ ቅዱስ የመስቀል ጦርነት እንደሆነ አድርገው በመግለጽ ድጋፍ ከመስጠታቸውም በላይ አምላክ ከእነሱ ጎን እንደሆነ ይሰማቸው ነበር። በተጨማሪም ባፕቲስቶች ከእንግሊዝ (በ1812)፣ ከሜክሲኮ (በ1845) እና ከስፔን ጋር (1898) ጦርነት በተደረገ ጊዜ አገራቸውን እንደሚደግፉ ያሳወቁ ሲሆን በተለይ ከሜክሲኮና ከስፔን ጋር ጦርነት የተደረገው ‘በዋነኝነት ለጭቁን ሕዝቦች ሃይማኖታዊ ነፃነት ለማጎናጸፍና ለሚስዮናዊ ሥራ አዳዲስ መስኮችን ለመክፈት’ እንደሆነ በመግለጽ ጦርነቱ ትክክል እንደነበረ ለማሳመን ሞክረዋል። ይህ ሲባል ግን ባፕቲስቶች ከሰላም ይልቅ ጦርነትን ይፈልጉ ነበር ማለት አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ አብዛኛውን ጊዜ ጦርነት የማይቀር ከሆነ ድጋፍ ይሰጡ ብሎም በጦርነቱ ይካፈሉ ነበር ማለት ነው።”—ሪቪው ኤንድ ኤክስፖዚተር—ኤ ባፕቲስት ቲኦሎጂካል ጆርናል

● “በታሪክ ዘመናት፣ በዓለም ላይ በነበሩ የተለያዩ ሕዝቦችና ባሕሎች ውስጥ ጦርነቶች በተነሱበት ወቅት ብዙውን ጊዜ ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች እንዲዋጉ ሃይማኖታዊ ማበረታቻ ይሰጣቸው እንደነበረ ታሪክ ጸሐፊዎች ገልጸዋል። ሰዎችን ለጦርነት ለማነሳሳት ጥቅም ላይ ይውሉ ከነበሩት መፈክሮች መካከል በጣም ጥንታዊውና ከፍተኛ የመቀስቀስ ኃይል የነበረው ‘አማልክት ከእኛ ጋር ናቸው’ የሚለው አባባል ነው።”—ዚ ኤጅ ኦቭ ዎርስ ኦቭ ሪሊጂን፣ 1000-1650—አን ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ግሎባል ዋርፌር ኤንድ ሲቪላይዜሽን

● “የሃይማኖት መሪዎች . . . የተሻለና ውጤታማ አመራር ለመስጠትም ሆነ የየራሳቸው እምነቶች እውነተኛ ሥነ ምግባራዊ መመሪያዎች መሆናቸውን በተግባር ለማስመሥከር በውድቀታቸው ላይ በአንክሮ ማሰብ ያስፈልጋቸዋል። . . . ሁሉም ሃይማኖቶች ሰላምን የሚመኙ መሆናቸው ምንም ጥርጥር የለውም፤ ሃይማኖት ይህን ሚና እየተጫወተ መሆኑ ግን የሚያጠራጥር ጉዳይ ነው።”—ቫዮለንስ ኢን ጎድስ ኔም—ሪሊጂን ኢን አን ኤጅ ኦቭ ኮንፍሊክት

በታሪክ ዘመናት ሁሉ የሕዝበ ክርስትና ዋና ዋና ሃይማኖቶች (የካቶሊክ፣ የኦርቶዶክስና የፕሮቴስታንት) የቀሳውስት ቡድን፣ ጦርነት በተነሳባቸው ጊዜያት በሙሉ በሁለቱም ጎራዎች የተሰለፉ ወታደሮችን ወኔ ለመቀስቀስ ብሎም በውጊያ ላይ ለሚሞቱት የፍትሐት ጸሎት ለማቅረብ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ቀሳውስትንና የነፍስ አባቶችን ሲያቀርብ ቆይቷል። በዚህ መንገድ፣ ደም መፋሰሱን የደገፉ ከመሆናቸውም በላይ ለሁሉም የጦር ሠራዊቶች ቡራኬ ሰጥተዋል።

ያም ሆኖ አንዳንዶች ለተካሄዱት ጦርነቶች ተጠያቂው ሃይማኖት ሊሆን እንደማይችል በመግለጽ ይከራከሩ ይሆናል። ይሁን እንጂ በዚህ ረገድ አንድ የሚነሳ ጥያቄ አለ፤ ‘ሃይማኖት የሰውን ዘር አንድ በማድረግ ረገድ ተሳክቶለት ያውቃል?’

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

“የማዲሰን አቨኑ ባፕቲስት ቤተ ክርስቲያን ፓስተር የሆኑት ክቡር ዶክተር ቻርለስ ኤተን በትናንትናው ዕለት ከመድረክ በተናገሩት ማስታወቂያ ላይ የቤተ ክርስቲያኗ የሰበካ ጉባኤ ቤት በምድር ጦሩም ሆነ በባሕር ኃይሉ ሠራዊት ውስጥ ለመቀጠር ለሚፈልጉ ሰዎች የምልመላ ጣቢያ ሆኖ እንደሚያገለግል አስታወቁ።

“እኚህ ሰው በከተማይቱ ውስጥ በዘወትሩ የእሁድ ጠዋት ሰበካቸው ወቅት ስለ ጦርነት ከሰበኩት እንዲሁም ወንዶችም ሆኑ ሴቶች በተቻለ ፍጥነት ለጦርነቱ ድጋፍ በመስጠት ለአገራቸውና ለዲሞክራሲ ያላቸውን ታማኝነት እንዲያረጋግጡ አጥብቀው ካሳሰቡት ከአሥር የሚበልጡ ቀሳውስት መካከል አንዱ ናቸው። በርካታ ቤተ ክርስቲያኖች በባንዲራ አሸብርቀው ነበር።”—“ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ፣” ሚያዝያ 16, 1917