በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እምነት ልትጥልበት የምትችል መጽሐፍ​—ክፍል 3

ባቢሎን በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ

እምነት ልትጥልበት የምትችል መጽሐፍ​—ክፍል 3

ይህ ርዕስ በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ የተገለጹትን ሰባት የዓለም ኃያላን መንግሥታት በተመለከተ “ንቁ!” መጽሔት ላይ ከሚወጡት ሰባት ተከታታይ ርዕሶች መካከል ሦስተኛው ነው። ዓላማውም መጽሐፍ ቅዱስ እምነት የሚጣልበትና በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ መጽሐፍ እንደሆነ እንዲሁም ተስፋ የሚፈነጥቅ መልእክት እንደያዘ ማሳየት ነው፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ተስፋ፣ ጭካኔ የተሞላበት የሰው ልጆች አገዛዝ ያስከተለው መከራና ሥቃይ እንደሚያከትም ይገልጻል።

የጥንቷ የባቢሎን ከተማ አንድ ሠዓሊ እንዳስቀመጠው

ከአሁኗ ባግዳድ በስተደቡብ 80 ኪሎ ሜትር ያህል ርቀት ላይ ለም በሆነ አካባቢ የምትገኘው የጥንቷ ባቢሎን እጅግ አስደናቂ ከተማ ነበረች። ግዙፍ በሆነ ድርብ ግንብ የታጠረችውና ዙሪያዋን በውኃ የተከበበችው ባቢሎን ጨርሶ የምትደፈር አትመስልም ነበር። ከተማይቱ ግርማ ሞገስ በተላበሱ ቤተ መቅደሶቿ፣ ገደላማ በሆነ ቦታ ላይ እንዳሉ ሆነው በተሠሩ የአትክልት ቦታዎቿ እንዲሁም አናታቸው ላይ ቤተ መቅደሶች ባሏቸው ግዙፍ ፒራሚዶቿ ትታወቅ ነበር። ባቢሎን ከጥንቱ ዓለም ታላላቅ ከተሞች አንዷ በመሆኗ በቅርቡ አስደናቂ ከተማ የሚል ስያሜ ተሰጥቷታል።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባቢሎን “የመንግሥታት እመቤት” ተብላ ተጠርታለች፤ ይህች ከተማ በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ ከተገለጹት የዓለም ኃያላን መንግሥታት መካከል የሦስተኛው መንግሥት ዋና ከተማ ነበረች። (ኢሳይያስ 47:5) ከዚያ ቀደም እንደነበሩት እንደ ግብፅና አሦር ሁሉ የባቢሎን መንግሥትም በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ ጎላ ያለ ድርሻ የነበረው በመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ መንግሥት የያዘውን ዘገባ ከዓለማዊ የታሪክ ምንጮች ጋር ማነጻጸር እንችላለን።

እምነት የሚጣልበት ታሪክ

የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የዳንኤል መጽሐፍ በአንድ ወቅት፣ ቤልሻዛር የተባለ ንጉሥ በባቢሎን ይገዛ እንደነበረ ይነግረናል። (ዳንኤል 5:1) ይሁንና ቀደም ባሉት ዘመናት አንዳንድ ዓለማዊ ምንጮች ቤልሻዛር ኃያል ሰው ቢሆንም ንጉሥ ሆኖ እንደማያውቅ ይገልጹ ነበር። ታዲያ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ስህተት ነው? የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች በመስጴጦምያ በምትገኘው በዑር ፍርስራሾች ውስጥ ሞላላ ቅርጽ ባላቸው በርካታ ሸክላዎች ላይ የሰፈሩ ጽሑፎችን አግኝተዋል። የሽብልቅ ቅርጽ ባላቸው ምልክቶች በተጻፈበት በአንዱ ሸክላ ላይ የባቢሎኑ ንጉሥ ናቦኒደስ “ታላቁ ልጄ ብልሳርሱር” በማለት ለቤልሻዛር ያቀረበው ጸሎት ይገኛል። ኒው ባይብል ዲክሽነሪ እንደሚገልጸው ቤልሻዛር “ከአባቱ የግዛት ዘመን ከግማሽ የሚበልጠውን እንደራሴ ሆኖ የገዛ ሲሆን በዚህ ጊዜ ከንጉሥ የማይተናነስ ሥልጣን” እንደነበረው ቆየት ብለው የተገኙ መረጃዎች አረጋግጠዋል።

በተጨማሪም የጥንቷ ባቢሎን የኮከብ ቆጠራና የጥንቆላ ሥራ የተስፋፋባት ሃይማኖታዊ ከተማ እንደነበረች ታሪክ ያመለክታል። ለምሳሌ ሕዝቅኤል 21:21 የባቢሎን ንጉሥ ወደ ኢየሩሳሌም መዝመት ይኖርበት እንደሆነና እንዳልሆነ ለመወሰን በጥንቆላ እንደተጠቀመ ይገልጻል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ንጉሡ “ጕበትንም ይመረምራል” ይላል። ጕበት መመርመር ያስፈለገው ለምን ነበር? ባቢሎናውያን ዕድላቸውን ለማወቅ በዚህ የእንስሳ አካል ይጠቀሙ ነበር። ሜሶፖታምያን አስትሮሎጂ የተባለው መጽሐፍ በጥንቷ ባቢሎን በሚገኝ አንድ ቦታ ላይ ብቻ የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች ዕጣ ፈንታን ለማወቅ የሚረዱ ምልክቶች “የተቀረጹባቸው በጕበት ቅርጽ የተሠሩ 32 [ሸክላዎችን]” እንዳገኙ ይናገራል።

ኔልሰን ግሉክ የተባሉት እውቅ የአርኪኦሎጂ ባለሙያ በአንድ ወቅት እንዲህ ብለው ነበር፦ “ለሠላሳ ዓመታት ያህል በአንድ እጄ መጽሐፍ ቅዱስ በሌላኛው እጄ ደግሞ መቆፈሪያ ይዤ ጥናት ሳካሂድ ቆይቻለሁ፤ ከታሪክ ጋር በተያያዘ መጽሐፍ ቅዱስን አንድም ጊዜ ቢሆን ስህተት ሆኖ አላገኘሁትም።”

ለሠላሳ ዓመታት ያህል . . . ጥናት ሳካሂድ ቆይቻለሁ፤ ከታሪክ ጋር በተያያዘ መጽሐፍ ቅዱስን አንድም ጊዜ ቢሆን ስህተት ሆኖ አላገኘሁትም።”—ኔልሰን ግሉክ

እምነት የሚጣልበት ትንቢት

አንድ ሰው እንደ ሞስኮ፣ ቤይጂንግ ወይም ዋሽንግተን ዲሲ ያሉ ታላላቅ ዋና ከተሞች ሰው የማይኖርባቸው ባድማ ይሆናሉ ብሎ ቢነግርህ ምን ትላለህ? ለማመን እንደምትቸገር የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ የጥንቷ ባቢሎን እንዲህ ያለ ነገር ደርሶባታል። ይሖዋ አምላክ፣ ኢሳይያስ የተባለውን ዕብራዊ ነቢይ ስለ ኃያሏ ባቢሎን ውድቀት የሚናገር ትንቢት እንዲጽፍ በመንፈሱ መርቶት ነበር፤ ባቢሎን ከመውደቋ ከ200 ዓመታት ገደማ በፊት ማለትም በ732 ዓ.ዓ. አካባቢ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ጽፎ ነበር፦ “የመንግሥታት ዕንቍ፣ . . . የሆነችውን ባቢሎንን፣ እግዚአብሔር እንደ ሰዶምና እንደ ገሞራ ይገለብጣታል። በዘመናት ሁሉ የሚቀመጥባት አይኖርም፤ የሚቀመጥባትም የለም።”—ኢሳይያስ 13:19, 20

ሆኖም አምላክ ባቢሎን እንደምትወድቅ አስቀድሞ የተናገረው ለምን ነበር? በ607 ዓ.ዓ የባቢሎናውያን ሠራዊት ኢየሩሳሌምን ያጠፋ ሲሆን ከጥፋቱ የተረፉትን አይሁዳውያንም በግዞት ወደ ባቢሎን ወስዷቸው ነበር፤ በዚያም አይሁዳውያኑ ብዙ መከራ ደርሶባቸዋል። (መዝሙር 137:8, 9) የአምላክ ሕዝቦች በፈጸሙት መጥፎ ድርጊት የተነሳ ለ70 ዓመት መከራ እንደሚደርስባቸው አምላክ አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። ከዚያ በኋላ ግን አምላክ ሕዝቦቹን ነፃ አውጥቶ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ያደርጋቸዋል።—ኤርምያስ 25:11፤ 29:10

በአምላክ ቃል ላይ በትንቢት እንደተነገረው የአይሁዳውያን የ70 ዓመት የግዞት ዘመን ሊያልቅ በተቃረበበት ወቅት ይኸውም በ539 ዓ.ዓ. የማትበገር ትመስል የነበረችው የባቢሎን ከተማ በሜዶ ፋርስ ሠራዊት ድል ሆነች። ውሎ አድሮም በትንቢት እንደተነገረው ከተማይቱ የፍርስራሽ ክምር ሆነች። እንዲህ ያለውን አስገራሚ ፍጻሜ ያገኘ ክንውን በቅድሚያ ሊተነብይ የሚችል ማንም ሰው የለም። ወደፊት የሚፈጸሙ ክንውኖችን የመተንበይ ወይም አስቀድሞ የመናገር ችሎታ የመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤት የሆነውን እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን ከሌላ ከማንኛውም አምላክ የተለየ እንደሚያደርገው ምንም ጥርጥር የለውም።—ኢሳይያስ 46:9, 10

እምነት ልትጥልበት የምትችል ተስፋ

በዘመናችን በመፈጸም ላይ የሚገኝ ሌላም አስደናቂ ትንቢት አለ። ትንቢቱ ከባቢሎኑ ንጉሥ ከናቡከደነፆርና እሱ በሕልሙ ከተመለከተው አንድ ግዙፍ ምስል ጋር የተያያዘ ነው። የምስሉ ራስ፣ ደረትና ክንድ፣ ሆድና ጭኖች፣ ቅልጥሞች እንዲሁም እግሮች ከአምስት የተለያዩ ማዕድናት የተሠሩ ናቸው። (ዳንኤል 2:31-33) እነዚህ ማዕድናት ከባቢሎን ጀምሮ በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ ሰባተኛው ኃያል መንግሥት እስከሆነው እስከ አንግሎ አሜሪካ ድረስ በተከታታይ የሚነሱትን መንግሥታት ያመለክታሉ።—ዳንኤል 2:36-41

ዳንኤል የምስሉ እግሮችና ጣቶች በተሠሩበት ማዕድን ላይ የጎላ ለውጥ እንደሚኖር ተናግሮ ነበር። ይህ የሆነው እንዴት ነው? ንጹሕ የሆነው ብረት፣ በሸክላና በብረት ቅልቅል ተተካ። ዳንኤል ለናቡከደነፆር ሕልሙን እንዲህ በማለት አብራርቶለታል፦ “ብረትና ሸክላ ተደባልቀው እንዳየህ ሁሉ ሕዝቡም ድብልቅ ይሆናል፤ ብረትና ሸክላ እንደማይዋሃድ ሁሉ ሕዝቡም በአንድነት አይኖሩም።” (ዳንኤል 2:43) አዎን፣ የብረትና የሸክላ ቅልቅል ጥንካሬ ሊኖረው አይችልም፤ እነዚህ ነገሮች ‘ሊዋሃዱ’ አይችሉም። ይህ ትንቢት ዛሬ ያለንበትን በፖለቲካ የተከፋፈለ ዓለም በትክክል የሚገልጽ ነው።

ዳንኤል ትልቅ ግምት የሚሰጠው ሌላም ክንውን እንደሚኖር ገልጿል። ንጉሥ ናቡከደነፆር በሕልሙ ከአንድ ትልቅ ተራራ የተፈነቀለ አንድ ድንጋይ ተመልክቶ ነበር። ይህ ድንጋይ “ከብረትና ከሸክላ የተሠሩትን የምስሉን እግሮች መታቸው፤ አደቀቃቸውም” በማለት ዳንኤል ተናግሯል። (ዳንኤል 2:34) ይህ ምን ማለት ነው? ዳንኤል ራሱ እንዲህ በማለት መልሱን ይሰጠናል፦ “በነዚያ ነገሥታት ዘመን [የመጨረሻው የዓለም ኃያል መንግሥት በሚገዛበት ዘመን]፣ የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይፈርስና ለሌላም ሕዝብ የማይሰጥ መንግሥት ይመሠርታል፤ እነዚያን መንግሥታት ሁሉ ያደቃል፤ እስከ መጨረሻውም ያጠፋቸዋል፤ ይህ መንግሥት ራሱ ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።” (ዳንኤል 2:44) ይህ ትንቢት የሰው ልጅ እስከ ዛሬ ከሚያውቃቸው መንግሥታት ሁሉ የተለየ መንግሥት እንደሚመጣ ይጠቁማል። የዚህ መንግሥት ንጉሥ፣ መሲሕ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በዚህ አምድ ሥር ቀደም ሲል በወጡት ርዕሶች ላይ እንደተገለጸው ኢየሱስ ሰይጣንንና ተከታዮቹን (ሰዎችም ሆኑ መናፍስት) በሙሉ ድምጥማጣቸውን በማጥፋት በጽንፈ ዓለም ላይ ሰላምና አንድነት እንዲኖር ያደርጋል።—1 ቆሮንቶስ 15:25