በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ለቤተሰብ | ወጣቶች

የጽሑፍ መልእክት ስትለዋወጡ መልካም ምግባር ማሳየት

የጽሑፍ መልእክት ስትለዋወጡ መልካም ምግባር ማሳየት

ተፈታታኙ ነገር

ከጓደኛህ ጋር ቁጭ ብለህ እየተጫወትክ ሳለ የጽሑፍ መልእክት ደረሰህ። ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

  1. ከጓደኛህ ጋር ማውራትህን ሳታቆም መልእክቱን ማንበብ

  2. ጓደኛህን ይቅርታ ጠይቀህ መልእክቱን ማንበብ

  3. መልእክቱን ችላ ብለህ ጨዋታህን መቀጠል

የምትመርጠው መልስ ለውጥ ያመጣል? አዎን ያመጣል!

ማወቅ የሚኖርብህ ነገር

ከአንድ ጓደኛህ ጋር እያወራህ ለሌላ ጓደኛህ የጽሑፍ መልእክት መላክ አንድን የስፖርት ዓይነት የጨዋታውን ሕግ ሳታከብር እንደመጫወት ይቆጠራል። ‘እነዚህ እኮ ጓደኞቼ ናቸው’ ትል ይሆናል። ይህ እንዲያውም መልካም ምግባር እንድታሳይ ይበልጥ ሊያነሳሳህ ይገባል። በእርግጥ መልካም ምግባር ከማሳየት ጋር በተያያዘ በጣም ጥብቅ መሆን አለብህ ማለት አይደለም። ቢሆንም ከሚከተለው ሐቅ መሸሽ አትችልም፦ ከጓደኞችህ ጋር ስትሆን መልካም ምግባር ከሌለህ ይዋል ይደር እንጂ ጓደኝነታችሁ መቋረጡ አይቀርም።

ለምን? ማንኛውም ሰው ቢሆን በአክብሮት እንዲያዝ ስለሚፈልግ ነው። ቤቲ * የምትባል አንዲት ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “ጓደኛዬ ከእኔ ጋር እያወራች እያለ ሌላ የተሻለ ነገር እየጠበቀች ያለ ይመስል አሁንም አሁንም ስልኳን የምታይ ከሆነ ያናድደኛል!” ቤቲ፣ እንዲህ የምታደርግ ጓደኛ ብትኖራት ምን ያህል የምትታገሳት ይመስልሃል?

በሞባይል ስልክ አጠቃቀም ረገድ መልካም ምግባር ታሳይ እንደሆነ ለማወቅ “ተፈታታኙ ነገር” በሚለው ሥር የተዘረዘሩትን አማራጮች መለስ ብለህ ተመልከት። የትኛው አማራጭ የሚሻል ይመስልሃል? አማራጭ A ጨዋነት እንደማይሆን ትገነዘብ ይሆናል። ይሁንና ስለ አማራጭ B እና C ምን ይሰማሃል? የጽሑፍ መልእክትህን ለማየት ጨዋታህን ማቋረጥ ተገቢ ነው? ወይስ ጨዋታውን ላለማቋረጥ ስትል መልእክቱን ችላ ማለት ይሻላል?

መልካም ምግባር የሚባለውን ነገር መለየት አስቸጋሪ የሚሆንበት ጊዜ እንዳለ ትገነዘብ ይሆናል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ረገድ ሊረዳን ይችላል። “ልክ ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ እንደምትፈልጉት ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉላቸው” ይላል። (ሉቃስ 6:31) ይህን መመሪያ ከጽሑፍ መልእክት ጋር በተያያዘም ልትጠቀምበት ትችላለህ። እንዴት?

 ምን ማድረግ ትችላለህ?

ተገቢ ባልሆነ ሰዓት የጽሑፍ መልእክት አትላክ። ሪቻርድ የሚባል አንድ ወጣት እንዲህ ብሏል፦ “አንዳንድ ጊዜ በጣም ከመሸ በኋላ የጽሑፍ መልእክት ይደርሰኛል። መልእክቱ ያን ያህል አስፈላጊ እንኳ አይደለም፤ በዚያ ላይ ደግሞ ከእንቅልፌ ይቀሰቅሰኛል!” አንተም ‘ሰዎች በሚያርፉበት ሰዓት መልእክት እልካለሁ?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ።—የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት፦ መክብብ 3:1

መልእክትህ ትሕትና የሚንጸባረቅበት ይሁን። ሰዎች እርስ በርስ በሚነጋገሩበት ጊዜ የሚጠቀሙባቸው ቃላት ብቻ ሳይሆኑ የድምፃቸው ቃና፣ ፊታቸው ላይ የሚነበበው ስሜት እንዲሁም የሚጠቀሙባቸው አካላዊ መግለጫዎች ሐሳባቸውን ያስተላልፋሉ። የጽሑፍ መልእክት በምትልክበት ጊዜ ግን እነዚህ ነገሮች አይኖሩም። ታዲያ ሐሳብህን በሚገባ ለማስተላለፍ ምን ማድረግ ትችላለህ? ጃዝመን የምትባል አንዲት ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “በተለመዱ የአክብሮት ቃላት ተጠቀሙ። ‘እንደምን ነህ?’ ብላችሁ ጠይቁ። እንዲሁም ‘እባክህ’ እና ‘አመሰግናለሁ’ እንደሚሉት ያሉ ቃላትን መልእክታችሁ ውስጥ አካትቱ።”—የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት፦ ቆላስይስ 4:6

አስተዋይ ሁን። “ተፈታታኙ ነገር” በሚለው ሥር የተሰጡትን አማራጮች እንደገና መለስ ብለህ ተመልከት። አንድ አስፈላጊ የሆነ መልእክት የምትጠብቅ ከሆነ ይቅርታ ጠይቀህ ጭውውቱን ማቋረጥ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ ግን መልእክቱ ሊቆይ ይችል ይሆናል። ኤሚ የተባለች የ17 ዓመት ወጣት “ጓደኛህ የሚናገረውን ነገር ከጨረሰ በኋላ መልእክቱን ማየት ትችላለህ፤ ጭውውታችሁን አቋርጠህ መልእክት መላክ ብትጀምር ግን እስክትጨርስ ድረስ ጓደኛህ ላይጠብቅህ ይችላል” በማለት ተናግራለች። ከሰዎች ጋር ሰብሰብ ብለህ በምትጨዋወትበት ጊዜም እንዲሁ አስተዋይ መሆን ያስፈልግሃል። የ18 ዓመቷ ጄን እንዲህ ብላለች፦ “ሙሉውን ጊዜ መልእክት በመላክ አታሳልፉ። እንዲህ የምታደርጉ ከሆነ አብረዋችሁ ላሉት ሰዎች ‘ስለ እናንተ ግድ የለኝም፤ ከሌሎች ጋር ብሆን ይሻለኝ ነበር’ የማለት ያህል ነው።”

‘ላክ’ የሚለውን ቁልፍ ከመጫንህ በፊት ቆም ብለህ አስብ። መልእክትህን ሰዎች በተሳሳተ መንገድ ሊረዱት ይችሉ ይሆን? ስሜትን ለመግለጽ የሚያስችሉ ምልክቶችን መጠቀምህ ሐሳብህን በደንብ ለማስተላለፍ ይረዳህ ይሆን? የ21 ዓመቷ አምበር እንዲህ ብላለች፦ “ስለ አንድ ነገር እየቀለድክ ከሆነ መልእክትህ ቀልድ መሆኑን የሚያሳየውን ምልክት [:-)] አክልበት። ሰዎች ለቀልድ የተነገረውን ነገር ባለመረዳታቸው ሊጎዱ አልፎ ተርፎም ግጭት ሊፈጠር ይችላል።”—የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት፦ ምሳሌ 12:18

በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው በሞባይል ስልክ አጠቃቀም ረገድ የምታሳየው ምግባር ትልቅ ለውጥ ያመጣል!

ልታስብባቸው የሚገቡ ነጥቦች፦ መልካም ምግባር የሚመጣው ከፍቅር ነው። ታዲያ ይህ ባሕርይ የሚገለጸው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ፍቅር ታጋሽና ደግ ነው። ፍቅር አይቀናም፣ ጉራ አይነዛም፣ አይታበይም፣ ተገቢ ያልሆነ ምግባር አያሳይም፣ የራሱን ፍላጎት አያስቀድምም፣ አይበሳጭም።” (1 ቆሮንቶስ 13:4, 5) በዚህ ረገድ አንተ ልትሠራበት የሚገባው አቅጣጫ የትኛው ነው?

^ አን.11 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።