በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

ስለ ፆታ ግንኙነት ያለኝን አቋም ማስረዳት የምችለው እንዴት ነው?

ስለ ፆታ ግንኙነት ያለኝን አቋም ማስረዳት የምችለው እንዴት ነው?

“እንዴ! እስካሁን ድንግል ነሽ?”

እንዲህ የሚል ጥያቄ ቀረበልሽ እንበል፤ ለጥያቄው መልስ መስጠት የምትፈልጊ ከሆነና መልስሽም አዎ የሚል ከሆነ፣ አቋምሽን በድፍረት መናገር የምትችዪው እንዴት ነው? ይህ ርዕስ በዚህ ረገድ ይረዳሻል!

 ድንግልና ምንድን ነው?

 ድንግል የሚባለው ወሲባዊ ድርጊቶችን ፈጽሞ የማያውቅ ሰው ነው።

 ይሁን እንጂ እነዚህ ወሲባዊ ድርጊቶች ምንን ያጠቃልላሉ? የፆታ ግንኙነት መፈጸም አንዱ ቢሆንም ከዚህ ጋር የተያያዙ ሌሎች ወሲባዊ ድርጊቶችም አሉ። አንዳንዶች የፆታ ግንኙነት እስካላደረጉ ድረስ የትኛውንም ወሲባዊ ድርጊት ቢፈጽሙ ድንግል ሊባሉ እንደሚችሉ ይሰማቸዋል።

 ይሁን እንጂ ወሲባዊ ድርጊት በአፍና በፊንጢጣ የሚደረግ የፆታ ግንኙነትን እንዲሁም የሌላን ሰው የፆታ ብልት ማሻሸትን ሊጨምር ይችላል።

 ዋናው ነጥብ፦ አንድ ሰው፣ በአፍና በፊንጢጣ የሚደረግ የፆታ ግንኙነትን እንዲሁም የሌላን ሰው የፆታ ብልት ማሻሸትን ጨምሮ የትኛውንም ወሲባዊ ድርጊት ቢፈጽም ድንግል ሊባል አይችልም።

 መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፆታ ግንኙነት ምን ይላል?

 የፆታ ግንኙነት መፈጸም ተገቢ የሚሆነው በተጋቡ ወንድና ሴት መካከል ብቻ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ምሳሌ 5:18) በመሆኑም አንድ ሰው አምላክን ማስደሰት የሚፈልግ ከሆነ ትዳር ከመመሥረቱ በፊት የፆታ ግንኙነት አይፈጽምም።—1 ተሰሎንቄ 4:3-5

 መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ረገድ ያለው አቋም ጊዜ ያለፈበት እንዲሁም ለዘመናችን የማይሠራ እንደሆነ የሚሰማቸው ሰዎች አሉ። ይሁን እንጂ በዓለማችን ፍቺ፣ ያልተፈለገ እርግዝና እንዲሁም የአባለዘር በሽታዎች የተለመዱ ነገሮች እየሆኑ መምጣታቸውን ልብ ማለት ያስፈልጋል። በእርግጥም አሁን ያለው ዓለም ከሥነ ምግባር አንጻር መሥፈርት ሊሆነን አይችልም!—1 ዮሐንስ 2:15-17

 እስቲ ቆም ብለሽ ለማሰብ ሞክሪ፤ መጽሐፍ ቅዱስ ሥነ ምግባርን አስመልክቶ የሚሰጠው መመሪያ ምክንያታዊ ነው። አንድ ምሳሌ እንመልከት፤ አንድ ሰው 1,000 ብር ስጦታ ሰጠሽ እንበል። አላፊ አግዳሚ እንዲያነሳው ከፎቅ ላይ ሆነሽ ገንዘቡን ትበትኚዋለሽ?

 ከፆታ ግንኙነት ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። የ14 ዓመቷ ሲዬራ እንዲህ ብላለች፦ “ከዓመታት በኋላ ስሙን እንኳ ለማላስታውሰው ሰው ድንግልናዬን አሳልፌ አልሰጥም።” የ17 ዓመቷ ታሚም “የፆታ ግንኙነት ልዩ ስጦታ በመሆኑ ከማንኛውም ሰው ጋር በመተኛት ላቃልለው አልፈልግም” ብላለች።

 ዋናው ነጥብ፦ ያላገቡ ሰዎች ድንግልናቸውንና ንጽሕናቸውን ጠብቀው እንዲኖሩ መጽሐፍ ቅዱስ ያበረታታል።—1 ቆሮንቶስ 6:18፤ 7:8, 9

 የአንቺ አቋም ምንድን ነው?

  •   መጽሐፍ ቅዱስ የፆታ ግንኙነትን አስመልክቶ የሚሰጠው መመሪያ ተገቢ እንደሆነ ይሰማሻል? ወይስ ከልክ በላይ ጥብቅ እንደሆነ ታስቢያለሽ?

  •   ያልተጋቡ ወንድና ሴት እስከተዋደዱ ድረስ የፆታ ግንኙነት ቢፈጽሙ ምንም ስህተት እንደሌለው ይሰማሻል?

 ብዙ ወጣቶች ጉዳዩን በጥልቅ ካሰቡበት በኋላ ድንግልናን ጠብቆ መኖር እንዲሁም ንጹሕ ምግባር ይዞ መቀጠል ከሁሉ የተሻለው መንገድ እንደሆነ እርግጠኛ ሆነዋል። ይህን ምርጫ በማድረጋቸው አይቆጩም ወይም የቀረባቸው ነገር እንዳለ አይሰማቸውም። አንዳንዶቹ የተናገሩትን ሐሳብ ተመልከቺ፦

  •  “ድንግል በመሆኔ ደስተኛ ነኝ! ይህን በማድረጌ የቀረብኝ ነገር ቢኖር ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት መፈጸም የሚያስከትላቸው ነገሮች ይኸውም የኅሊና፣ የአካል እንዲሁም የስሜት ሥቃይ ነው።”ኤሚሊ

  •  “የፆታ ግንኙነት ከፈጸምኩ በኋላ ያቆምኩት የፍቅር ጓደኝነት ባለመኖሩ ደስተኛ ነኝ፤ ከዚህም ሌላ ‘የአባለዘር በሽታ ይዞኝ ቢሆንስ’ የሚለው ስጋት ጨርሶ የለኝም።”ኢሌይን

  •  “በእኔ ዕድሜ ያሉና ከእኔ ከፍ የሚሉ በርካታ ሴቶች ሲናገሩ እንደሰማሁት ከሆነ የፆታ ግንኙነት በመፈጸማቸው የሚቆጩ ከመሆኑም ሌላ ታግሰው ቢቆዩ የተሻለ እንደነበር ይሰማቸዋል፤ እኔም ተመሳሳይ ስህተት መሥራት አልፈልግም።”ቬራ

  •  “ድንግልናቸውን ማጣታቸው ወይም ከተለያዩ ሰዎች ጋር የፆታ ግንኙነት መፈጸማቸው የስሜት ጠባሳ ያስከተለባቸው ብዙ ሰዎች አውቃለሁ። እንዲህ ዓይነቱ ሕይወት አሳዛኝ እንደሆነ ይሰማኛል።”ዲያን

 ዋናው ነጥብ፦ የፆታ ግንኙነትን በተመለከተ አቋምሽ ምን እንደሆነ ማሰብ ያለብሽ የፆታ ግንኙነት እንድትፈጽሚ ጥያቄ ሳይቀርብልሽ ወይም ተጽዕኖ ሳይደረግብሽ በፊት ነው።—ያዕቆብ 1:14, 15

 አቋምሽን ለሌሎች ማስረዳት የምትችዪው እንዴት ነው?

 የፆታ ግንኙነትን በተመለከተ ምን አቋም እንዳለሽ አንድ ሰው ቢጠይቅሽ ምን ብለሽ መመለስ ይኖርብሻል? ይህ እንደየሁኔታው ይለያያል።

 “አንድ ሰው እንዲህ ብሎ የጠየቀኝ ሊያሾፍብኝ ፈልጎ ብቻ ከሆነ ቆሜ በመስማት ዕድል አልሰጠውም። ‘እሱ አይመለከትህም’ ብዬ ትቼው እሄዳለሁ።”ኮሪን

 “የሚያሳዝነው ነገር፣ በትምህርት ቤት ያሉ አንዳንድ ልጆች ሌሎችን ማሾፊያ በማድረግ ይዝናናሉ። አንድ ሰው ጥያቄውን የጠየቀኝ ይህን አስቦ ከሆነ ምንም መልስ አልሰጠውም።”ዴቪድ

 ይህን ታውቅ ነበር? ኢየሱስ ለሚያሾፉበት ሰዎች ዝም በማለት “መልስ” የሰጠበት ጊዜ አለ።—ማቴዎስ 26:62, 63

 ይሁን እንጂ ግለሰቡ ጥያቄውን ያነሳው ምክንያትሽን ለማወቅ ፈልጎ ከሆነስ? ይህ ሰው ለመጽሐፍ ቅዱስ አክብሮት ካለው፣ በ1 ቆሮንቶስ 6:18 ላይ እንደሚገኘው ያሉ ጥቅሶችን ልታሳዪው ትችያለሽ፤ ጥቅሱ ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት የሚፈጽም ሰው በራሱ አካል ላይ ኃጢአት እንደሚሠራ ወይም ራሱን እንደሚጎዳ ይገልጻል።

 ወዲያውኑ መጽሐፍ ቅዱስን ተጠቅመሽ መልስ ሰጠሽም አልሰጠሽ፣ ስለ አቋምሽ ስትናገሪ በእርግጠኝነት መናገርሽ አስፈላጊ ነው። በሥነ ምግባር ንጹሕ ለመሆን በመምረጥሽ ልትኮሪ እንደሚገባ አትዘንጊ።—1 ጴጥሮስ 3:16

 “ምላሽ ስትሰጡ በእርግጠኝነት መናገራችሁ ሰዎች፣ በምትናገሩት ነገር ላይ ጥያቄ ወይም ጥርጣሬ እንደሌላችሁ እንዲገነዘቡ ያደርጋቸዋል፤ እንዲሁም የዚህ ዓይነት አቋም የያዛችሁ ትክክል መሆኑን ስላመናችሁበት እንጂ እንዲህ እንድታደርጉ ስለተነገራችሁ እንዳልሆነ ያሳያል።”ጂል

 ዋናው ነጥብ፦ የፆታ ግንኙነትን በተመለከተ ያለሽን አቋም የምታምኚበት ከሆነ ለሌሎች ማስረዳት አይከብድሽም። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ የሚያስገርም ምላሽ ይሰጡሽ ይሆናል። ሜሊንዳ የተባለች የ21 ዓመት ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “የሥራ ባልደረቦቼ ድንግል በመሆኔ አድንቀውኛል። እንግዳ ነገር እንደሆነ አልተሰማቸውም። ከዚህ ይልቅ ራሴን የምገዛና ንጹሕ ሰው እንደሆንኩ የሚጠቁም ነገር እንደሆነ ተሰምቷቸዋል።”

 ጠቃሚ ምክር! የፆታ ግንኙነትን በተመለከተ ስላለሽ አቋም እርግጠኛ ለመሆን እንዲረዳሽ “ስለ ፆታ ግንኙነት ያለሽን አቋም ማስረዳት የምትችዪው እንዴት ነው?” የሚለውን የመልመጃ ሣጥን አውርጂ። በተጨማሪም ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች የሚለውን መጽሐፍ ተመልከቺ።

 “‘ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች’ በተባሉት መጽሐፎች ላይ የተጠቀሱት አሳማኝ ነጥቦች ደስ ይሉኛል። ለምሳሌ ያህል፣ በጥራዝ 1 ገጽ 187 ላይ ያለው ሥዕል፣ ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት መፈጸም ውድ የሆነ ሐብልን በነፃ ለማንም እንደ መስጠት እንደሆነ ያሳያል። እንዲህ ማድረግ ራስን እንደ ማራከስ ነው። በገጽ 177 ላይ ያለው ሥዕል ደግሞ ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት መፈጸም አንድን ውብ ሥዕል የበር ምንጣፍ እንደ ማድረግ እንደሆነ ያሳያል። ከሁሉ የበለጠ የምወደው ሥዕል ግን በጥራዝ 2 ገጽ 54 ላይ የሚገኘው ነው። የሥዕሉ መግለጫ እንዲህ ይላል፦ ‘ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት መፈጸም አንድ ስጦታ ሳይሰጥህ አስቀድመህ እንደ መክፈት ነው።’ ይህን ማድረግ የሌላን ሰው ይኸውም የወደፊት የትዳር ጓደኛችሁን ንብረት እንደ መስረቅ ይቆጠራል።”ቪክቶሪያ