በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ንድፍ አውጪ አለው?

የሰው አካል ያለው ቁስልን የመጠገን ችሎታ

የሰው አካል ያለው ቁስልን የመጠገን ችሎታ

የሰው ልጅ በሕይወት እንዲቀጥል ከሚያስችሉት በርካታ ሂደቶች መካከል አንዱ የሰውነታችን ቁስልን የመጠገን እንዲሁም የተጎዳን ሕብረ ሕዋስ የማደስ ችሎታ ነው። ይህ ሂደት የሚጀምረው በሰውነት ላይ ጉዳት በደረሰበት ቅጽበት ነው።

እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ ቁስልን የመጠገኑ ሂደት የሚከናወነው ሴሎች በሚያካሂዱት በርካታ ውስብስብ ተግባር አማካኝነት ነው።

  • ፕሌትሌቶች ቁስሉ ዙሪያ በሚገኙ ሕብረ ሕዋሳት ላይ በመጣበቅ ደሙ እንዲረጋና ጉዳት የደረሰባቸው የደም ቧንቧዎች እንዲደፈኑ ያደርጋሉ።

  • ጉዳት የደረሰበት አካባቢ መቆጣቱ ኢንፌክሽንን የሚከላከል ከመሆኑም ሌላ በተጎዳው ቦታ ላይ የሚገኙ አላስፈላጊ ነገሮች እንዲወገዱ ያደርጋል።

  • በጥቂት ቀናት ውስጥ ሰውነታችን የተጎዳውን ሕብረ ሕዋስ መተካት፣ ቁስሉ እንዲጠብ ማድረግና ጉዳት የደረሰባቸውን የደም ሥሮች መጠገን ይጀምራል።

  • በመጨረሻም ጉዳት በደረሰበት ቦታ ላይ የሚፈጠረው ጠባሳ የተጎዳው የአካል ክፍል ሙሉ በሙሉ እንዲታደስና እንዲጠናከር ያደርጋል።

ተመራማሪዎች የደም መርጋትን ሂደት በመመልከት፣ የደረሰባቸውን ጉዳት በራሳቸው መጠገን የሚችሉ ፕላስቲኮችን በመሥራት ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ራሳቸውን የሚያድሱ የፕላስቲክ ዕቃዎች ጉዳት ሲደርስባቸው “የሚደሙ” ቀጫጭን ቱቦዎች አሏቸው፤ እነዚህ ጎን ለጎን ያሉ ቱቦዎች ሁለት ዓይነት ኬሚካሎችን ይዘዋል። ሁለቱ ኬሚካሎች በሚቀላቀሉበት ጊዜ ጉዳት በደረሰበት አካባቢ በመፍሰስ ስንጥቆችንና ቀዳዳዎችን ለመድፈን የሚያስችል ዝልግልግ ፈሳሽ ይፈጥራሉ። ፈሳሹ ሲረጋ ዕቃው መጀመሪያ ላይ የነበረውን ጥንካሬ መልሶ እንዲያገኝ የሚያደርግ ጠንካራ ንጥረ ነገር ይፈጥራል። አንድ ተመራማሪ በእነዚህ ዕቃዎች ላይ እየተሞከረ ያለው ሰው ሠራሽ የሆነ ራስን በራስ የመጠገን ሂደት አዲስ ነገር ሳይሆን ቀድሞውኑም በፍጥረታት ላይ የነበረ መሆኑን በሐቀኝነት ተናግረዋል።

ታዲያ ምን ይመስልሃል? የሰው አካል ያለው ቁስልን የመጠገን ችሎታ በዝግመተ ለውጥ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?