በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“የመንግሥት ካህናት” ትሆናላችሁ

“የመንግሥት ካህናት” ትሆናላችሁ

“እናንተ ለእኔ የመንግሥት ካህናት የተቀደሰ ሕዝብ ትሆናላችሁ።”ዘፀ. 19:6

1, 2. የሴቲቱ ዘር ምን ዓይነት ጥበቃ ያስፈልገው ነበር? ለምንስ?

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገበው የመጀመሪያው ትንቢት ከይሖዋ ዓላማ አፈጻጸም ጋር በተያያዘ ትልቅ ቦታ አለው። እውነተኛው አምላክ የኤደኑን ተስፋ ሲሰጥ “በአንተና [በሰይጣንና] በሴቲቱ፣ በዘርህና በዘሯ መካከል፣ ጠላትነትን አደርጋለሁ” ብሎ ነበር። ይህ ጠላትነት ምን ያህል የከረረ ይሆናል? ይሖዋ “እርሱ [የሴቲቱ ዘር] ራስህን [የሰይጣንን ራስ] ይቀጠቅጣል፤ አንተም ተረከዙን ትቀጠቅጣለህ” ብሏል። (ዘፍ. 3:15) በእባቡና በሴቲቱ መካከል ያለው ጠላትነት እጅግ የከረረ በመሆኑ ሰይጣን ዘሯን ለማጥፋት ማንኛውንም ጥረት ከማድረግ ወደኋላ አይልም።

2 ከዚህ አንጻር፣ መዝሙራዊው የአምላክን የተመረጡ ሕዝቦች በተመለከተ እንደሚከተለው በማለት መጸለዩ የሚያስገርም አይደለም፦ “ጠላቶችህ እንዴት እንደ ተነሣሡ፣ ባላንጣዎችህም እንዴት ራሳቸውን ቀና ቀና እንዳደረጉ ተመልከት። በሕዝብህ ላይ በተንኰል አሤሩ፤ በውድ ልጆችህ ላይ በአንድነት ተመካከሩ። ‘. . . ኑና ሕዝብ እንዳይሆኑ እንደምስሳቸው’ አሉ።” (መዝ. 83:2-4) በመሆኑም የሴቲቱ ዘር የሚመጣበት መስመር እንዳይጠፋና እንዳይበከል ጥበቃ ሊደረግለት ይገባ ነበር። ይሖዋ ይህን ለማከናወን ሲል ዓላማውን ለመፈጸም የሚያስችሉ ሌሎች ሕጋዊ ዝግጅቶችን አደረገ።

 ለዘሩ ጥበቃ የሚያደርግ ቃል ኪዳን

3, 4. (ሀ) የሕጉ ቃል ኪዳን የጸናው መቼ ነው? የእስራኤል ብሔር ምን ለማድረግ ተስማምቶ ነበር? (ለ) የሕጉ ቃል ኪዳን ምን ዓይነት ጥበቃ አስገኝቷል?

3 የአብርሃም፣ የይስሐቅና የያዕቆብ ዘሮች እየበዙ ሄደው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሲሆኑ ይሖዋ በብሔር መልክ እንዲደራጁ አደረጋቸው፤ ይህም የጥንቱ የእስራኤል ብሔር ነው። ይሖዋ በሙሴ አማካኝነት ለእስራኤላውያን ሕግ በመስጠት ከብሔሩ ጋር ልዩ ቃል ኪዳን አደረገ፤ የእስራኤል ብሔርም በዚህ ቃል ኪዳን መስማማቱን ገለጸ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “[ሙሴ] የኪዳኑን መጽሐፍ ወስዶ ለሕዝቡ አነበበላቸው፤ እነርሱም፣ ‘እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እናደርጋለን፤ እንታዘዛለን’ አሉ። ከዚያም ሙሴ ደሙን [መሥዋዕት የተደረጉትን ወይፈኖች ደም] ወሰደ፤ ሕዝቡም ላይ ረጭቶ፣ ‘ይህ እነዚህን ቃሎች በሰጠ ጊዜ፣ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር የገባው የቃል ኪዳኑ ደም ነው’ አላቸው።”—ዘፀ. 24:3-8

4 የሕጉ ቃል ኪዳን የጸናው በ1513 ዓ.ዓ. በሲና ተራራ ነው። በዚህ ቃል ኪዳን አማካኝነት የጥንቱ የእስራኤል ብሔር ለአምላክ የተመረጠ ሕዝብ ሆኖ ተለየ። ከዚያ በኋላ ይሖዋ ‘ዳኛቸው፣ ሕግ ሰጪያቸውና ንጉሣቸው’ ሆነ። (ኢሳ. 33:22) እስራኤላውያን የአምላክን የጽድቅ መመሪያዎች ሲጠብቁ አሊያም መመሪያዎቹን ችላ ሲሉ ምን ያጋጥማቸው እንደነበር የእስራኤል ታሪክ በግልጽ ያሳየናል። ሕጉ ከአረማውያን ጋር መጋባትንና በሐሰት አምልኮ መካፈልን ስለሚከለክል የአብርሃም ዘር እንዳይበከል ጥበቃ አድርጓል።—ዘፀ. 20:4-6፤ 34:12-16

5. (ሀ) የሕጉ ቃል ኪዳን ለእስራኤላውያን ምን አጋጣሚ ከፍቶላቸው ነበር? (ለ) አምላክ እስራኤላውያንን የተዋቸው ለምንድን ነው?

5 የሕጉ ቃል ኪዳን የክህነት አገልግሎትም እንዲኖር አድርጓል፤ ይህም ወደፊት ለሚደረግ አንድ ታላቅ ዝግጅት ጥላ ነበር። (ዕብ. 7:11፤ 10:1) እንዲያውም ይህ ቃል ኪዳን፣ እስራኤላውያን የይሖዋን ሕግጋት እስከታዘዙ ድረስ “የመንግሥት ካህናት” የመሆን ልዩ አጋጣሚና መብት እንዲያገኙ መንገድ ከፍቶ ነበር። (ዘፀአት 19:5, 6ን አንብብ።) ይሁንና እስራኤላውያን የይሖዋን ሕግጋት አልታዘዙም። ብሔሩ፣ የአብርሃም ዘር ዋነኛ ክፍል የሆነው መሲሕ ሲመጣ በጉጉት ከመቀበል ይልቅ ይህን ሳያደርግ ቀረ። በመሆኑም አምላክ ብሔሩን ተወው።

እስራኤላውያን ታዛዥ አለመሆናቸው የሕጉ ቃል ኪዳን ዓላማውን ማሳካት እንዳልቻለ የሚያሳይ አይደለም (ከአንቀጽ 3-6ን ተመልከት)

6. ሕጉ ምን አከናውኗል?

6 እስራኤላውያን ለይሖዋ ታማኝ ባለመሆናቸው የመንግሥት ካህናት መሆን አልቻሉም፤ ይህ ሲባል ግን ሕጉ ዓላማውን ማሳካት አልቻለም ማለት አይደለም። የሕጉ ዓላማ ዘሩ ለሚመጣበት መስመር ጥበቃ ማድረግና የሰው ልጆች የመሲሑን ማንነት እንዲያውቁ መርዳት ነበር። ኢየሱስ ሲመጣና መሲሑ እሱ መሆኑን ሰዎች ሲገነዘቡ የሕጉ ዓላማ ተፈጽሟል። መጽሐፍ ቅዱስ “ክርስቶስ የሕግ ፍጻሜ ነው” ይላል። (ሮም 10:4) ይሁንና ‘ከዚያ በኋላ የመንግሥት ካህናት የመሆን አጋጣሚ የሚዘረጋው ለእነማን ነው?’ የሚለው ጥያቄ መልስ ያሻዋል።  ይሖዋ አምላክ አዲስ ብሔር ለማቋቋም የሚያስችል ሌላ ሕጋዊ ውል አዘጋጅቷል።

አዲስ ብሔር ተቋቋመ

7. ይሖዋ፣ አዲሱን ቃል ኪዳን በተመለከተ በነቢዩ ኤርምያስ አማካኝነት ምን ተናግሮ ነበር?

7 የሕጉ ቃል ኪዳን ከመሻሩ ከብዙ ጊዜ በፊት ይሖዋ ከእስራኤል ብሔር ጋር “አዲስ ቃል ኪዳን” እንደሚገባ በነቢዩ ኤርምያስ አማካኝነት ተናግሮ ነበር። (ኤርምያስ 31:31-33ን አንብብ።) ይህ ቃል ኪዳን ከሕጉ ቃል ኪዳን በተለየ፣ የእንስሳት መሥዋዕት ሳይቀርብ የኃጢአት ይቅርታ እንዲገኝ ያደርጋል። እንዴት?

8, 9. (ሀ) የፈሰሰው የኢየሱስ ደም ምን አከናውኗል? (ለ) በአዲሱ ቃል ኪዳን የታቀፉት ምን አጋጣሚ ተከፍቶላቸዋል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

8 ከበርካታ ዘመናት በኋላ ማለትም ኒሳን 14, 33 ዓ.ም. ኢየሱስ የጌታ ራት በዓልን አቋቋመ። በዚህ ወቅት በጽዋ ያለውን ወይን በተመለከተ ለ11 ታማኝ ሐዋርያቱ “ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው ደሜ አማካኝነት የሚመሠረተው አዲሱ ቃል ኪዳን ማለት ነው” አላቸው። (ሉቃስ 22:20) የማቴዎስ ዘገባ ደግሞ ኢየሱስ ወይኑን አስመልክቶ “ይህ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ ‘የቃል ኪዳን ደሜ’ ማለት ነው” ብሎ እንደተናገረ ይገልጻል።—ማቴ. 26:27, 28

9 አዲሱ ቃል ኪዳን የጸናው በፈሰሰው የኢየሱስ ደም አማካኝነት ነው። ይህ ደም የሰው ልጆች ከኃጢአታቸው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይቅርታ እንዲያገኙም ያደርጋል። ኢየሱስ፣ በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ ከታቀፉት አካላት አንዱ አልነበረም። ኢየሱስ ኃጢአት ስለሌለበት የኃጢአት ይቅርታ ማግኘት አያስፈልገውም። ሆኖም አምላክ የፈሰሰውን የኢየሱስን ደም ዋጋ የአዳምን ዘሮች ለመጥቀም አውሎታል። በተጨማሪም ታማኝ የሆኑ የተወሰኑ ሰዎችን በመንፈስ ቅዱስ በመቀባት “እንደ ልጅ የመቆጠር” መብት ሰጥቷቸዋል። (ሮም 8:14-17ን አንብብ።) እነዚህ ሰዎች በአምላክ ፊት ኃጢአት እንደሌለባቸው ሆነው ስለሚቆጠሩ ኃጢአት እንደሌለበት የአምላክ ልጅ ማለትም እንደ ኢየሱስ ናቸው ሊባል ይችላል። እነዚህ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ‘ከክርስቶስ ጋር አብረው ወራሾች’ ይሆናሉ፤ እንዲሁም “የመንግሥት ካህናት” የመሆን መብት ያገኛሉ። ሕጉ ለእስራኤል ብሔር ይህን መብት ያስገኝላቸው ነበር። ሐዋርያው ጴጥሮስ ‘ከክርስቶስ ጋር አብረው ወራሾች’ ስለሆኑት ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “እናንተ . . . ከጨለማ ወደ አስደናቂ ብርሃኑ የጠራችሁን የእሱን ‘ድንቅ ባሕርያት በስፋት እንድታስታውቁ የተመረጠ ዘር፣ ንጉሣዊ ካህናት፣ ቅዱስ ብሔር፣ ልዩ ንብረት እንዲሆን የተለየ ሕዝብ’ ናችሁ።” (1 ጴጥ. 2:9) በእርግጥም አዲሱ ቃል ኪዳን በጣም አስፈላጊ ነው! የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የአብርሃም ዘር ሁለተኛ ክፍል እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።

አዲሱ ቃል ኪዳን ጸና

10. አዲሱ ቃል ኪዳን የጸናው መቼ ነው? እንዲህ የምንለውስ ለምንድን ነው?

10 አዲሱ ቃል ኪዳን የጸናው መቼ ነው? ይህ የሆነው ኢየሱስ በምድር ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት ላይ ስለዚህ ቃል ኪዳን በተናገረበት ወቅት አልነበረም። ይህ ቃል ኪዳን ሥራ ላይ እንዲውል የኢየሱስ ደም መፍሰስ እና የደሙ ዋጋ በሰማይ ለይሖዋ መቅረብ ነበረበት። በተጨማሪም ‘ከክርስቶስ ጋር አብረው ወራሾች’ በሚሆኑት ላይ መንፈስ ቅዱስ መፍሰስ ነበረበት። በመሆኑም አዲሱ ቃል ኪዳን የጸናው በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት የኢየሱስ ታማኝ ደቀ መዛሙርት በመንፈስ ቅዱስ ሲቀቡ ነው።

11. አዲሱ ቃል ኪዳን አይሁዳውያንም ሆኑ አሕዛብ የመንፈሳዊ እስራኤል አባላት እንዲሆኑ የሚያደርገው እንዴት ነው? በአዲሱ ቃል ኪዳን የታቀፉትስ ቁጥራቸው ምን ያህል ነው?

11 ይሖዋ ከእስራኤል ብሔር ጋር አዲስ ቃል ኪዳን እንደሚገባ በኤርምያስ በኩል በተናገረበት ወቅት የሕጉ ቃል ኪዳን “ጊዜ ያለፈበት” ቢሆንም አዲሱ ቃል ኪዳን እስኪጸና ድረስ የቀድሞው ቃል ኪዳን ወደ ፍጻሜው አልመጣም። (ዕብ. 8:13) አዲሱ ቃል ኪዳን ሲጸና፣ ክርስቲያን የሆኑ አይሁዳውያንም ሆነ ያልተገረዙ አሕዛብ የአምላክን መንግሥት ለመውረስ እኩል አጋጣሚ አግኝተዋል፤ ምክንያቱም “[ግርዘታቸው]  በተጻፈ ሕግ ሳይሆን በመንፈስ የሆነ የልብ ግርዘት ነው።” (ሮም 2:29) አምላክ ከእነሱ ጋር አዲሱን ቃል ኪዳን ሲገባ ሕግጋቱን ‘በአእምሯቸው ውስጥ አኑሯል፤ በልባቸውም ላይ ጽፎታል።’ (ዕብ. 8:10) በአዲሱ ቃል ኪዳን የታቀፉት ሰዎች አጠቃላይ ቁጥር 144,000 ሲሆን እነሱም አዲስ ብሔር ይኸውም ‘የአምላክ እስራኤል’ የተባለውን መንፈሳዊ እስራኤል መሥርተዋል።—ገላ. 6:16፤ ራእይ 14:1, 4

12. የሕጉ ቃል ኪዳን ከአዲሱ ቃል ኪዳን ጋር ሲወዳደር ምን ይመስላል?

12 የሕጉ ቃል ኪዳን ከአዲሱ ቃል ኪዳን ጋር ሲወዳደር ምን ይመስላል? የሕጉ ቃል ኪዳን የተደረገው በይሖዋ እና በሥጋዊ እስራኤላውያን መካከል ሲሆን አዲሱ ቃል ኪዳን የተደረገው ደግሞ በይሖዋ እና በመንፈሳዊ እስራኤላውያን መካከል ነው። የቀድሞው ቃል ኪዳን መካከለኛ ሙሴ ሲሆን የአዲሱ ቃል ኪዳን መካከለኛ ደግሞ ኢየሱስ ነው። የሕጉ ቃል ኪዳን የጸናው በእንስሳት ደም አማካኝነት ሲሆን አዲሱ ቃል ኪዳን የጸናው ግን በፈሰሰው የኢየሱስ ደም አማካኝነት ነው። በሕጉ ቃል ኪዳን ሥር የነበረው የእስራኤል ብሔር መሪ ሙሴ ነበር፤ በአዲሱ ቃል ኪዳን ሥር ላሉት ግን መሪያቸው የጉባኤው ራስ የሆነው ኢየሱስ ነው።—ኤፌ. 1:22

13, 14. (ሀ) አዲሱ ቃል ኪዳን ከመንግሥቱ ጋር ምን ግንኙነት አለው? (ለ) መንፈሳዊ እስራኤላውያን ከክርስቶስ ጋር በሰማይ አብረው መግዛት እንዲችሉ ምን ያስፈልጋል?

13 አዲሱ ቃል ኪዳን ከአምላክ መንግሥት ጋር ምን ግንኙነት አለው? ይህ ቃል ኪዳን በሰማይ ባለው መንግሥት ነገሥታትና ካህናት የመሆን መብት ያለው ቅዱስ ብሔር ያስገኛል። የዚህ ብሔር አባላት የአብርሃም ዘር ሁለተኛ ክፍል ናቸው። (ገላ. 3:29) በመሆኑም አዲሱ ቃል ኪዳን የአብርሃም ቃል ኪዳን ፍጻሜውን እንዲያገኝ አድርጓል።

14 ከአምላክ መንግሥት ጋር በተያያዘ የሚያስፈልግ ሌላም ነገር አለ። አዲሱ ቃል ኪዳን መንፈሳዊ እስራኤልን ያስገኘ ሲሆን አባላቱ ‘ከክርስቶስ ጋር አብረው ወራሾች’ እንዲሆኑ መንገድ ከፍቷል። ይሁንና እነዚህ ሰዎች በሰማይ በክርስቶስ መንግሥት ከእሱ ጋር ነገሥታትና ካህናት መሆን እንዲችሉ ሌላ ሕጋዊ ውል ያስፈልጋል።

ከክርስቶስ ጋር አብረው የሚገዙ እንዲኖሩ የሚያደርግ ቃል ኪዳን

15. ኢየሱስ ከታማኝ ሐዋርያቱ ጋር የገባው ቃል ኪዳን የትኛው ነው?

15 ኢየሱስ የጌታ ራት በዓልን ካቋቋመ በኋላ ከታማኝ ደቀ መዛሙርቱ ጋር ቃል ኪዳን ገብቷል፤ ይህ ቃል ኪዳን ብዙ ጊዜ የመንግሥት ቃል ኪዳን ተብሎ ይጠራል። (ሉቃስ 22:28-30ን አንብብ።) ይሖዋ ከሌሎች ጋር ከገባቸው ቃል ኪዳኖች በተለየ ይህ ቃል ኪዳን የተደረገው በኢየሱስና በቅቡዓን ተከታዮቹ መካከል ነው። ኢየሱስ “አባቴ ከእኔ ጋር ቃል ኪዳን እንዳደረገ” ብሎ ሲናገር ይሖዋ “በመልከጼዴቅ ሥርዓት መሠረት አንተ ለዘላለም ካህን ነህ” በማለት ከእሱ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን እየጠቀሰ መሆን አለበት።—ዕብ. 5:5, 6

16. የመንግሥቱ ቃል ኪዳን ለቅቡዓን ክርስቲያኖች ምን አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል?

16 ታማኝ የሆኑት 11ዱ ሐዋርያት ከኢየሱስ ጋር ‘በፈተናዎቹ ከጎኑ ሳይለዩ ቆይተዋል።’ የመንግሥቱ ቃል ኪዳን፣ ከኢየሱስ ጋር በሰማይ እንደሚሆኑ እንዲሁም በዙፋኖች ላይ ተቀምጠው ነገሥታት ሆነው እንደሚገዙና ካህናት ሆነው እንደሚያገለግሉ አረጋግጦላቸዋል። ይሁንና ይህን መብት የሚያገኙት 11ዱ ሐዋርያት ብቻ አይደሉም። ክብር የተጎናጸፈው ኢየሱስ ለሐዋርያው ዮሐንስ በራእይ ተገልጦ እንዲህ ብሎታል፦ “እኔ ድል ነስቼ ከአባቴ ጋር በዙፋኑ ላይ እንደተቀመጥኩ ሁሉ ድል የሚነሳውንም ከእኔ ጋር በዙፋኔ ላይ እንዲቀመጥ አደርገዋለሁ።” (ራእይ 3:21) ከዚህ ማየት እንደሚቻለው የመንግሥቱ ቃል ኪዳን የተደረገው በኢየሱስና በ144,000ዎቹ ቅቡዓን ክርስቲያኖች መካከል ነው። (ራእይ 5:9, 10፤ 7:4) ይህ ቃል ኪዳን ቅቡዓኑ ከኢየሱስ ጋር በሰማይ ለመግዛት የሚያስችላቸው ሕጋዊ መሠረት ጥሏል። ነጥቡን በምሳሌ ለማስረዳት  ያህል፣ ከአንድ ትልቅ ቤተሰብ የመጣች ሙሽራ በመግዛት ላይ ካለ ንጉሥ ጋር ትዳር እንደምትመሠርት አድርገን እናስብ፤ ሙሽራዋ ንጉሡን ካገባች በኋላ ከእሱ ጋር የመግዛት ሥልጣን ይኖራታል። በተመሳሳይም ቅቡዓን ክርስቲያኖች የክርስቶስ “ሙሽራ” እንዲሁም ለክርስቶስ የታጩ “ንጽሕት ድንግል” እንደሆኑ ተደርገው በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ተገልጸዋል።—ራእይ 19:7, 8፤ 21:9፤ 2 ቆሮ. 11:2

በአምላክ መንግሥት ላይ የማይናወጥ እምነት ይኑራችሁ

17, 18. (ሀ) እስካሁን የመረመርናቸውን ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ስድስት ቃል ኪዳኖች በአጭሩ ከልስ። (ለ) በመንግሥቱ ላይ የማይናወጥ እምነት ማሳደር የምንችለው ለምንድን ነው?

17 በእነዚህ ሁለት ርዕሶች ውስጥ የመረመርናቸው ቃል ኪዳኖች በሙሉ ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ አስፈላጊ ገጽታዎችን ያጎላሉ። (ከዚሀ በፊት በነበረው ርዕስ ላይ የወጣውን “አምላክ ዓላማውን የሚፈጽምበት መንገድ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) ይህም መንግሥቱ በሕጋዊ ስምምነቶች ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ያረጋግጥልናል። በመሆኑም አምላክ ለምድርና ለሰው ዘር ያለውን የመጀመሪያ ዓላማ ለመፈጸም የሚጠቀምበት መሣሪያ መሲሐዊው መንግሥት እንደሆነ ሙሉ በሙሉ እንድንተማመን የሚያደርግ በቂ ምክንያት አለን።—ራእይ 11:15

ይሖዋ መሲሐዊውን መንግሥት በመጠቀም ለምድር ያለውን ዓላማ እውን ያደርጋል (ከአንቀጽ 15-18ን ተመልከት)

18 የአምላክ መንግሥት የሚያከናውናቸው ነገሮች ለሰው ዘር ዘላቂ በረከት እንደሚያመጡ ፈጽሞ አንጠራጠርም። በመሆኑም ለሰው ዘር ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ የሚያስገኘው የአምላክ መንግሥት ብቻ መሆኑን በልበ ሙሉነት መናገር እንችላለን። እንግዲያው ይህን እውነት ለሌሎች በቅንዓት እናውጅ!—ማቴ. 24:14