የጴጥሮስ የመጀመሪያው ደብዳቤ 2:1-25

  • ለአምላክ ቃል ጉጉት አዳብሩ (1-3)

  • “እንደ ሕያዋን ድንጋዮች መንፈሳዊ ቤት ለመሆን እየተገነባችሁ ነው” (4-10)

  • በዓለም ውስጥ እንደ ባዕድ አገር ሰዎች መኖር (11, 12)

  • ተገቢ የሆነ ተገዢነት ማሳየት (13-25)

    • አርዓያችን የሆነው ክርስቶስ (21)

2  እንግዲህ ክፋትን ሁሉ፣ ማታለልን፣ ግብዝነትን፣ ቅናትንና ሐሜትን ሁሉ አስወግዱ።+  ገና እንደተወለዱ ሕፃናት+ በአምላክ ቃል ውስጥ ለሚገኘው ያልተበረዘ* ወተት ጉጉት አዳብሩ፤ ይህም በእሱ አማካኝነት ወደ መዳን ማደግ እንድትችሉ ነው፤+  ጌታ ደግ መሆኑን ቀምሳችኋልና።*  በሰዎች ወደተናቀው+ በአምላክ ግን ወደተመረጠውና በፊቱ ክቡር ወደሆነው ወደ እሱ ይኸውም ሕያው ወደሆነው ድንጋይ+ በመምጣት  እናንተ ራሳችሁ ቅዱሳን ካህናት ለመሆን እንደ ሕያዋን ድንጋዮች መንፈሳዊ ቤት ለመሆን እየተገነባችሁ ነው፤+ ይህም በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መንፈሳዊ መሥዋዕት ማቅረብ ትችሉ ዘንድ ነው።+  ምክንያቱም ቅዱስ መጽሐፉ እንዲህ ይላል፦ “እነሆ፣ በጽዮን የተመረጠ ድንጋይ ይኸውም ክቡር የሆነ የማዕዘን የመሠረት ድንጋይ አኖራለሁ፤ ደግሞም በእሱ የሚያምን ሁሉ ፈጽሞ አያፍርም።”+  በመሆኑም እናንተ አማኞች ስለሆናችሁ እሱ ለእናንተ ክቡር ነው፤ የማያምኑትን በተመለከተ ግን እንዲህ ተብሎ ተጽፏል፦ “ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፣+ እሱ የማዕዘን ራስ ድንጋይ* ሆነ”፤+  እንዲሁም “የሚያደናቅፍ ድንጋይና የሚያሰናክል ዓለት ሆነ።”+ እነሱ የሚሰናከሉት ለቃሉ ስለማይታዘዙ ነው። እነዚህ ሰዎች የሚጠብቃቸው ነገር ይኸው ነው።  እናንተ ግን ከጨለማ ወደ አስደናቂ ብርሃኑ የጠራችሁን+ የእሱን “ድንቅ ባሕርያት* በየቦታው እንድታውጁ+ የተመረጠ ዘር፣ ንጉሣዊ ካህናት፣ ቅዱስ ብሔር፣+ ልዩ ንብረት እንዲሆን የተለየ ሕዝብ”+ ናችሁ። 10  እናንተ በአንድ ወቅት የአምላክ ሕዝብ አልነበራችሁም፤ አሁን ግን የአምላክ ሕዝብ ናችሁ፤+ ቀደም ሲል ምሕረት አልተደረገላችሁም ነበር፤ አሁን ግን ምሕረት አግኝታችኋል።+ 11  የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ የባዕድ አገር ሰዎችና ጊዜያዊ ነዋሪዎች+ እንደመሆናችሁ መጠን እናንተን ከሚዋጉት* ሥጋዊ ፍላጎቶች+ ምንጊዜም እንድትርቁ አሳስባችኋለሁ።+ 12  ክፉ አድራጊዎች እንደሆናችሁ አድርገው ሲከሷችሁ መልካም ሥራችሁን በዓይናቸው ማየት እንዲችሉ+ ብሎም አምላክ ለመመርመር በሚመጣበት ቀን እሱን እንዲያከብሩ በዓለም ባሉ ሰዎች መካከል መልካም ምግባር ይኑራችሁ።+ 13  ለጌታ ብላችሁ ለሰብዓዊ ሥልጣን* ሁሉ ተገዙ፦+ የበላይ ስለሆነ ለንጉሥ ተገዙ፤+ 14  ደግሞም ክፉ አድራጊዎችን ለመቅጣት፣ መልካም የሚያደርጉትን ግን ለማመስገን በእሱ የተላኩ ስለሆኑ ለገዢዎች ተገዙ።+ 15  የአምላክ ፈቃድ፣ መልካም ነገር በማድረግ ከንቱ ንግግር የሚናገሩትን ምክንያታዊ ያልሆኑ ሰዎች አፍ ዝም እንድታሰኙ* ነውና።+ 16  እንደ ነፃ ሰዎች ኑሩ፤+ ነፃነታችሁን እንደ አምላክ ባሪያዎች+ ሆናችሁ ተጠቀሙበት እንጂ ለክፋት መሸፈኛ* አታድርጉት።+ 17  ሁሉንም ዓይነት ሰው አክብሩ፤+ ለመላው የወንድማማች ማኅበር ፍቅር ይኑራችሁ፤+ አምላክን ፍሩ፤+ ንጉሥን አክብሩ።+ 18  አገልጋዮች ጥሩና ምክንያታዊ ለሆኑት ብቻ ሳይሆን በቀላሉ ለማይደሰቱ ጌቶቻቸውም እንኳ ተገቢ ፍርሃት በማሳየት ይገዙ።+ 19  አንድ ሰው በአምላክ ፊት ንጹሕ ሕሊና እንዲኖረው ሲል መከራን* ችሎ ቢያሳልፍና ግፍ ቢደርስበት ይህ ደስ የሚያሰኝ ነውና።+ 20  ኃጢአት በመሥራታችሁ የሚደርስባችሁን ዱላ ብትቋቋሙ ምን ጥቅም አለው?+ መልካም ነገር በማድረጋችሁ መከራ ሲደርስባችሁ ችላችሁ ብታሳልፉ ግን ይህ አምላክ ደስ የሚሰኝበት ነገር ነው።+ 21  ደግሞም የተጠራችሁት በዚህ ጎዳና እንድትሄዱ ነው፤ ምክንያቱም ክርስቶስም እንኳ የእሱን ፈለግ በጥብቅ እንድትከተሉ አርዓያ ትቶላችሁ+ ስለ እናንተ መከራ ተቀብሏል።+ 22  እሱ ምንም ኃጢአት አልሠራም፤+ በአንደበቱም የማታለያ ቃል አልተገኘም።+ 23  ሲሰድቡት+ መልሶ አልተሳደበም።+ መከራ ሲደርስበት+ አልዛተም፤ ከዚህ ይልቅ በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን በአደራ ሰጠ።+ 24  ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር እሱ ራሱ በገዛ አካሉ ኃጢአታችንን በእንጨት* ላይ+ ተሸከመ።+ ደግሞም “በእሱ ቁስል እናንተ ተፈወሳችሁ።”+ 25  እናንተ እንደባዘኑ በጎች ነበራችሁና፤+ አሁን ግን ወደ ነፍሳችሁ* እረኛና+ ጠባቂ* ተመልሳችኋል።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ንጹሕ።”
ወይም “አይታችኋልና።”
ቃል በቃል “የማዕዘኑ ራስ።” ማቴ 21:42 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።
ቃል በቃል “በጎነት።” የእሱን የሚደነቁ ባሕርያትና ተግባራት ያመለክታል።
ወይም “ነፍስን ከሚዋጉት።”
ወይም “ተቋም።”
ቃል በቃል “እንድትለጉሙ።”
ወይም “ሰበብ።”
ወይም “ሐዘንን፤ ሥቃይን።”
ወይም “በዛፍ።”
ወይም “ሕይወታችሁ።”
ቃል በቃል “የበላይ ተመልካች።”