በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | በእርግጥ ሰይጣን አለ?

ሰይጣን የክፋት ባሕርይ ነው?

ሰይጣን የክፋት ባሕርይ ነው?

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸው ሰይጣን የክፋት ባሕርይ ነው ብሎ መደምደም ቀላል ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ብሎ ያስተምራል? ደግሞስ ሰይጣን ከኢየሱስ ክርስቶስና ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ ጋር እንደተነጋገረ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጽ የለ? ሰይጣን እንዲህ ያደረገባቸውን ሁለት አጋጣሚዎች እንመልከት።

ሰይጣን ከኢየሱስ ጋር ተነጋግሯል

ኢየሱስ በምድር ላይ አገልግሎቱን በጀመረበት ወቅት ዲያብሎስ ሦስት የተለያዩ ማባበያዎችን በማቅረብ ኢየሱስን ሊፈትነው ሞክሮ ነበር። በመጀመሪያ ሰይጣን፣ ኢየሱስ ረሃቡን ለማስታገሥ ሲል በራስ ወዳድነት ስሜት ተነሳስቶ አምላክ የሰጠውን ኃይል እንዲጠቀምበት ለመገፋፋት ጥረት አደረገ። ከዚያም ኢየሱስ የሰዎችን ትኩረት ለመሳብ ሲል ሕይወቱን ለአደጋ የሚያጋልጥ ነገር እንዲፈጽም ለማደፋፈር ሞከረ። በመጨረሻም ሰይጣን፣ ኢየሱስ አንድ ጊዜ ብቻ ወድቆ ቢሰግድለት የዓለምን መንግሥታት ሁሉ እንደሚሰጠው ነገረው። ኢየሱስ በሦስቱም ማባበያዎች አልተሸነፈም፤ ከዚህ ይልቅ ከቅዱሳን መጻሕፍት እየጠቀሰ ምላሽ ሰጠ።—ማቴዎስ 4:1-11፤ ሉቃስ 4:1-13

ታዲያ ኢየሱስ የተነጋገረው ከማን ጋር ነበር? በውስጡ ካለ የክፋት ባሕርይ ጋር ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን አስመልክቶ “እንደ እኛው በሁሉም ረገድ የተፈተነ ነው፤ ሆኖም ምንም ኃጢአት የለበትም” ይላል። (ዕብራውያን 4:15) በተጨማሪም “እሱ ምንም ኃጢአት አልሠራም፤ ከአንደበቱም የማታለያ ቃል አልወጣም” በማለት ይናገራል። (1 ጴጥሮስ 2:22) ኢየሱስ ንጹሕ አቋሙን ሳያጎድፍ እስከ መጨረሻው ፍጹም ሆኖ ቀጥሏል። በውስጡ ምንም ዓይነት የክፋት ባሕርይ እንዲኖር አልፈቀደም። ኢየሱስ የተነጋገረው በእውን ካለ አንድ አካል ጋር እንጂ በራሱ ውስጥ ከሚገኝ የክፋት ባሕርይ ጋር እንዳልሆነ ግልጽ ነው።

ሰይጣን ኢየሱስን እንዳነጋገረው የሚገልጸው ይህ ዘገባ ሰይጣን በእውን ያለ አካል መሆኑን የሚያሳይ ሌላም ማስረጃ ይዟል።

  • ዲያብሎስ፣ አንድ ጊዜ ብቻ ቢያመልከው የዓለምን መንግሥታት በሙሉ እንደሚሰጠው ለኢየሱስ ቃል እንደገባለት አስታውስ። (ማቴዎስ 4:8, 9) ሰይጣን በእውን ያለ አካል ባይሆን ኖሮ ያቀረበው ግብዣ ምንም ትርጉም አይኖረውም ነበር። ከዚህም በላይ ኢየሱስ ሰይጣን እንዲህ ያለ ታላቅ ሥልጣን ያለው መሆኑን አላስተባበለም።

  • ዲያብሎስ፣ ኢየሱስ ለቀረቡለት ማባበያዎች እንዳልተሸነፈ ሲያይ “ሌላ አመቺ ጊዜ እስኪያገኝ ድረስ ትቶት ሄደ።” (ሉቃስ 4:13) ታዲያ ይህ የሚያሳየው ሰይጣን የክፋት ባሕርይ መሆኑን ነው? ወይስ ተስፋ ቆርጦ የማይተው ክፉ ባለጋራ መሆኑን?

  • ዘገባው “መላእክትም [ኢየሱስን] መጥተው ያገለግሉት ጀመር” እንደሚል ልብ በል። (ማቴዎስ 4:11) ኢየሱስን እንዲያበረታቱትና እንዲረዱት የተላኩት እነዚህ መላእክት መንፈሳዊ አካል ያላቸው ፍጥረታት ናቸው? እንደሆኑ ግልጽ ነው። ታዲያ ሰይጣንስ መንፈሳዊ አካል ያለው ፍጡር አይደለም የምንልበት ምን ምክንያት ይኖራል?

ሰይጣን ከአምላክ ጋር ተነጋግሯል

ፈሪሃ አምላክ ስለነበረው ስለ ኢዮብ ታሪክ በሚገልጸው ዘገባ ላይ ሰይጣን ከአምላክ ጋር እንደተነጋገረ የሚገልጽ ሐሳብ እናገኛለን። ይህ ታሪክ ዲያብሎስና አምላክ በሁለት የተለያዩ አጋጣሚዎች እንደተነጋገሩ ይገልጻል። በሁለቱም አጋጣሚዎች አምላክ፣ ንጹሕ አቋሙን የማያጎድፍ ሰው እንደሆነ በመግለጽ ኢዮብን አመስግኖታል። ሰይጣን ግን ኢዮብ አምላክን የሚያገለግለው ለራሱ ጥቅም ሲል እንደሆነ ተናግሯል፤ በተዘዋዋሪ ሰይጣን፣ ኢዮብ ታማኝ የሆነው አምላክ በጥቅም ስለደለለው እንደሆነ መናገሩ ነው። ዲያብሎስ ይህን ሲል ‘ከአምላክ ይበልጥ ኢዮብን የማውቀው እኔ ነኝ’ ማለቱ ነበር። ይሖዋ፣ ሰይጣን የኢዮብን ንብረት፣ ልጆችና ሌላው ቀርቶ ጤንነቱንም ጭምር እንዲነጥቅ ፈቀደ። * ከጊዜ በኋላ ይሖዋ ስለ ኢዮብ የተናገረው ነገር ትክክል እንደሆነ ሰይጣን ደግሞ ሐሰተኛ መሆኑ በግልጽ ታየ። ኢዮብ ንጹሕ አቋሙን ባለማጉደፉ አምላክ ባርኮታል።—ኢዮብ 1:6-12፤ 2:1-7

በእነዚህ ዘገባዎች ላይ ይሖዋ እየተነጋገረ የነበረው በውስጡ ካለ የክፋት ባሕርይ ጋር ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “የአምላክ መንገዱ ፍጹም ነው” ይላል። (2 ሳሙኤል 22:31) በተጨማሪም የአምላክ ቃል “ሁሉን ቻይ የሆነው ይሖዋ አምላክ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ ነው” ይላል። (ራእይ 4:8) ቅዱስ ማለት ንጹሕ ወይም ከኃጢአት የራቀ ማለት ነው። ይሖዋ ፍጹምና እንከን የለሽ ነው። ምንም ዓይነት የክፋት ባሕርይ ሊኖረው አይችልም።

ሰይጣን ከአምላክ ጋር መነጋገሩ በኢዮብ ላይ ያስከተለው ውጤት አለ

ያም ሆኖ አንዳንዶች፣ ኢዮብም እንኳ በሕይወት ኖሮ የሚያውቅ ሰው መሆኑን ይጠራጠራሉ፤ በመሆኑም አምላክና ሰይጣን እንደተነጋገሩ የሚገልጸው በኢዮብ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው ዘገባ ምሳሌያዊ ትርጉም የያዘ ሐሳብ ነው በማለት ይከራከሩ ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህ ሐሳብ ምክንያታዊ ነው? ኢዮብ በሕይወት ኖሮ የሚያውቅ ሰው እንደሆነ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ይጠቁማሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በ⁠ያዕቆብ 5:7-11 ላይ ክርስቲያኖች መከራ ሲደርስባቸው እንዲጸኑ ለማበረታታትና ይሖዋ እንዲህ ዓይነት ጽናት ለሚያሳዩ ሰዎች ወሮታ እንደሚከፍል ለማሳሰብ ኢዮብ እንደ ምሳሌ ተጠቅሷል። ኢዮብ በሕይወት ኖሮ የሚያውቅ ሰው ካልሆነና በሰይጣን የተሰነዘረበት ጥቃትም የፈጠራ ታሪክ ብቻ ከሆነ እሱ እንደ ምሳሌ ተደርጎ መጠቀሱ ምን ትርጉም ይኖረዋል? ከዚህም በላይ በ⁠ሕዝቅኤል 14:14, 20 ላይ ሦስቱ ጻድቃን ሰዎች ተብለው ከተዘረዘሩት መካከል አንዱ ኢዮብ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ኖኅና ዳንኤል ናቸው። እንደ ኖኅና እንደ ዳንኤል ሁሉ ኢዮብም በሕይወት ኖሮ የሚያውቅ ታላቅ የእምነት ሰው ነበር። ኢዮብ በሕይወት ኖሮ የሚያውቅ ሰው ከሆነ ደግሞ በእሱ ላይ ጥቃት የሰነዘረበትና ስደት ያደረሰበትም በእውን ያለ አካል ነው ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ አይሆንም?

መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣንን መንፈሳዊ አካል ያለው ፍጡር አድርጎ እንደሚገልጸው ከዚህ መረዳት ይቻላል። ይሁንና ‘ሰይጣን በዚህ ዘመናዊ ዓለምም ጭምር በእኔና በቤተሰቤ ላይ ጉዳት ሊያደርስብን ይችላል?’ የሚል ጥያቄ ወደ አእምሮህ ይመጣ ይሆናል።

ሰይጣን በዚህ ዘመን ሰዎችን ሊጎዳ ይችላል?

የምትኖርበት ከተማ በድንገት በወንጀለኞች ተጥለቀለቀ እንበል። በዚህ የተነሳ የምትኖርበት አካባቢ ለደኅንነትህ አስጊ እንደሚሆን እንዲሁም የነዋሪዎቹ ሥነ ምግባር እያሽቆለቆለ እንደሚሄድ ግልጽ ነው። እስቲ ከዚህ ጋር የሚመሳሰል አንድ ሌላ ሁኔታ እንመልከት፦ ሰይጣንና አጋንንቱ ማለትም እንደ እሱ በአምላክ ላይ ያመፁ መንፈሳዊ አካላት በድንገት በምድር አካባቢ ብቻ እንዲንቀሳቀሱ ተደረገ። ይህስ ምን ውጤት አስከተለ? በአካባቢህም ሆነ በዓለም ዙሪያ በዜና ማሰራጫዎች ስለሚተላለፉት ነገሮች እስቲ ለማሰብ ሞክር።

  • በዓለም ዙሪያ ብዙ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም በጭካኔ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ እንደሆነ ልብ አላልክም?

  • ብዙ ወላጆች ጉዳዩ ቢያሳስባቸውም በመዝናኛው ዓለም መናፍስታዊ ነገሮች የሚታዩባቸው መዝናኛዎች እየበዙ እንደመጡ አላስተዋልክም?

  • ምድርን ከጥፋት ለመታደግ ብዙ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም በምድራችን ላይ የሚደርሰው ጉዳት እየጨመረ እንደሆነ ልብ አላልክም?

  • መላውን የሰው ዘር ወደ ጥፋት እየገፋ ያለ አንድ ኃይል እንዳለ ተሰምቶህ አያውቅም?

መጽሐፍ ቅዱስ በዛሬው ጊዜ ላሉ ችግሮች መንስኤው ማን እንደሆነ ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “ታላቁ ዘንዶ ይኸውም መላውን ዓለም እያሳሳተ ያለው ዲያብሎስና ሰይጣን ተብሎ የሚጠራው የመጀመሪያው እባብ ወደ ታች ተወረወረ፤ ወደ ምድር ተወረወረ፤ መላእክቱም ከእሱ ጋር ተወረወሩ። . . . ምድርና ባሕር . . . ወዮላችሁ! ምክንያቱም ዲያብሎስ ጥቂት ጊዜ እንደቀረው ስላወቀ በታላቅ ቁጣ ተሞልቶ ወደ እናንተ ወርዷል።” (ራእይ 12:9, 12) ብዙ ሰዎች ማስረጃውን ከመረመሩ በኋላ፣ ሰይጣን በዓለም ላይ ትልቅ ተጽዕኖ እያሳደረ ያለ አደገኛ መንፈሳዊ አካል ነው የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል።

ከሰይጣን ጥቃት ጥበቃ ማግኘት የምትችለው እንዴት እንደሆነ ያሳስብህ ይሆናል። ይህ ጉዳይ ቢያሳስብህ አያስገርምም። ቀጣዩ ርዕስ በዚህ ረገድ ምን ማድረግ እንደምትችል ይጠቁምሃል።

^ አን.12 መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው የአምላክ የግል ስም ይሖዋ ነው።