በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ሚላን፣ ጣሊያን ውስጥ የሚገኘው ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት

ኅዳር 12, 2020
ጣሊያን

የጣሊያን ፍርድ ቤት፣ የይሖዋ ምሥክር ወላጆች ለልጆቻቸው የሚሰጠውን የሕክምና ዓይነት የመምረጥ መብታቸውን የሚያስከብር ውሳኔ አስተላለፈ

የጣሊያን ፍርድ ቤት፣ የይሖዋ ምሥክር ወላጆች ለልጆቻቸው የሚሰጠውን የሕክምና ዓይነት የመምረጥ መብታቸውን የሚያስከብር ውሳኔ አስተላለፈ

በሚላን፣ ጣሊያን የሚገኘው ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ለአንድ የይሖዋ ምሥክር ባልና ሚስት ፈርዶላቸዋል፤ እነዚህ ባልና ሚስት ለልጃቸው የሚሰጠውን የሕክምና ዓይነት ከመምረጥ መብት ጋር በተያያዘ ክስ ቀርቦባቸው ነበር። የተላለፈው ብይን፣ ወላጆች በሃይማኖታዊ አቋማቸው የተነሳ ልጃቸው ያለደም የሚሰጥ የሕክምና ዓይነት እንዲደረግለት ስለጠየቁ ብቻ ፍርድ ቤቶች በወላጆቹ የአሳዳጊነት ብቃት ላይ ጥያቄ ማንሳት እንደማይኖርባቸው ያረጋግጣል።

መስከረም 2019፣ አንድ የይሖዋ ምሥክር ባልና ሚስት የአሥር ወር ልጃቸው ወድቃ ጉዳት ስለደረሰባት ወደ ሆስፒታል ይዘዋት ሄዱ። ሐኪሞቹ፣ ልጅቷ ጭንቅላቷ ላይ ጉዳት ስለደረሰባት ቀዶ ሕክምና እንደሚያስፈልጋት ገለጹ። ሐኪሞቹ ቀዶ ሕክምናውን ያለደም በተሳካ ሁኔታ ማከናወን ቻሉ።

በኋላ ላይ ልጅቷ በጥሩ ሁኔታ እያገገመች ሳለ፣ አንድ ሐኪም “አጋዥ ሕክምና” ያስፈልጋታል በሚል ለልጅቷ ደም እንዲሰጣት ወላጆቿን ጠየቃቸው። ወላጆቹ ግን በስፋት ተቀባይነት ያገኙ ያለደም የሚሰጡ የሕክምና አማራጮችን እንዲጠቀም ጥያቄ አቀረቡ።

ሐኪሙ የወላጆቹን ጥያቄ ከመቀበል ይልቅ ጉዳዩን ለፖሊስና ለአቃቤ ሕግ ቢሮ አሳወቀ። አቃቤ ሕጉ፣ የቤተሰብ ጉዳዮችን ከሚመለከት ፍርድ ቤት የፍርድ ቤት ማዘዣ አወጣ። የፍርድ ቤት ማዘዣው፣ ለልጅቷ የሚሰጠውን የሕክምና ዓይነት የመምረጡን ሕጋዊ መብት ከወላጆቹ ወስዶ ለሆስፒታሉ ዳይሬክተር እንዲሰጥ አደረገ። የሆነው ሆኖ፣ ሐኪሞቹ አስፈላጊ እንደሆነ ስላልተሰማቸው ለልጅቷ ደም አልተሰጣትም።

ይህ ሁኔታ በአገሪቱ ያሉ የብዙ መገናኛ ብዙኃንን ትኩረት ስቦ ነበር። በርካታ የጣሊያን መገናኛ ብዙኃን፣ ደም እንዲሰጥ የሚያዝ የፍርድ ቤት ማዘዣ የአንድን ትንሽ ልጅ ሕይወት እንደታደገ የሚገልጽ የተሳሳተ ዘገባ አወጡ።

መስከረም 10, 2020 ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቱ፣ የወላጆቹ መብት እንዲገደብ የሚያደርገውን ቀደም ሲል የቤተሰብ ፍርድ ቤት ያስተላለፈውን ውሳኔ ውድቅ አደረገ። ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቱ፣ የቤተሰብ ፍርድ ቤቱ እንዲህ ዓይነት ማዘዣ ማውጣት እንዳልነበረበት እንዲሁም ጉዳዩን የመመልከት መብትም እንዳልነበረው ገልጿል።

የሚላን ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “ወላጆቹ በሃይማኖታዊ አቋማቸው የተነሳ በደም የሚሰጥ ሕክምናን ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆናቸው ብቻ በአሳዳጊነት መብታቸው ላይ ጥያቄ እንዲነሳ መሠረት አይሆንም።” ባለፈው ዓመት ብቻ በጣሊያን የሚገኙ ሦስት ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቶች፣ የይሖዋ ምሥክር ወላጆች ለልጆቻቸው ያለደም የሚሰጥ የሕክምና ዓይነት የመምረጥ መብታቸውን የሚያስከብር ውሳኔ አስተላልፈዋል።

የሕግ አካላትም ሆኑ የሕክምና ባለሙያዎች፣ የይሖዋ ምሥክሮች ተአምራዊ ፈውስ እንደማያካሂዱና ፀረ ሕክምና እንዳልሆኑ ሊያውቁ ይገባል። እንዲያውም የይሖዋ ምሥክሮች ከሃይማኖታዊ አቋማቸው ጋር እስካልተጋጨ ድረስ በቂ ተሞክሮና የሕክምና መሣሪያዎች ባሏቸው ዘመናዊ ሆስፒታሎች ውስጥ ጥሩ ሕክምና ለማግኘት ጥረት ያደርጋሉ። እነሱ የማይቀበሉት፣ ደም መስጠትን የሚጠይቅ የሕክምና ዓይነት ብቻ ነው። በዓለም ዙሪያ በትላልቅ ሆስፒታሎች ውስጥ የሚሠሩ ስመጥር ሐኪሞች፣ ይህን ሁኔታ ተረድተው ያለደም ጥሩ ሕክምና መስጠት ችለዋል።

እነዚህ ፍርድ ቤቶች ላስተላለፏቸው ውሳኔዎች አመስጋኞች ነን፤ ምክንያቱም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ለልጆቻቸው ተቀባይነት ያለው የሕክምና ዓይነት ለመምረጥ ያደረጉትን ቁርጥ ውሳኔ ያጠናክሩላቸዋል።—የሐዋርያት ሥራ 15:29