የሐዋርያት ሥራ 15:1-41

  • በአንጾኪያ ግርዘትን አስመልክቶ የተነሳ ክርክር (1, 2)

  • ጥያቄው ወደ ኢየሩሳሌም ተላከ (3-5)

  • ሽማግሌዎችና ሐዋርያት ተሰበሰቡ (6-21)

  • ከበላይ አካል የተላከ ደብዳቤ (22-29)

    • ‘ከደም ራቁ’ (28, 29)

  • ጉባኤዎች በደብዳቤው ተበረታቱ (30-35)

  • ጳውሎስና በርናባስ ተለያዩ (36-41)

15  አንዳንድ ሰዎች ከይሁዳ ወደ አንጾኪያ ወርደው “በሙሴ ሥርዓት መሠረት ካልተገረዛችሁ+ በቀር ልትድኑ አትችሉም” እያሉ ወንድሞችን ያስተምሩ ጀመር።  በዚህ የተነሳ ጳውሎስና በርናባስ ከሰዎቹ ጋር የጦፈ ክርክርና ጭቅጭቅ ውስጥ ገቡ። በመሆኑም ጳውሎስና በርናባስ እንዲሁም አንዳንድ ወንድሞች ወደ ኢየሩሳሌም ወጥተው+ ጉዳዩን* በዚያ ለሚገኙት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች እንዲያቀርቡ ተወሰነ።  በዚህም መሠረት ጉባኤው የተወሰነ መንገድ ከሸኛቸው በኋላ በፊንቄና በሰማርያ በኩል በማለፍ ከአሕዛብ ወገን የሆኑ ሰዎች ተለውጠው አምላክን ማምለክ እንደጀመሩ በዝርዝር ተናገሩ፤ ወንድሞችንም ሁሉ እጅግ ደስ አሰኟቸው።  ኢየሩሳሌም ሲደርሱም በዚያ የሚገኘው ጉባኤ እንዲሁም ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ጥሩ አቀባበል አደረጉላቸው፤ የተላኩትም ወንድሞች አምላክ በእነሱ አማካኝነት ያከናወናቸውን በርካታ ነገሮች ተረኩላቸው።  ይሁንና ከፈሪሳውያን ሃይማኖታዊ ቡድን መካከል አማኞች የሆኑ አንዳንድ ሰዎች ከመቀመጫቸው ተነስተው “እነዚህን ሰዎች መግረዝና የሙሴን ሕግ እንዲጠብቁ ማዘዝ አስፈላጊ ነው” ሲሉ ተናገሩ።+  ሐዋርያትና ሽማግሌዎችም ይህን ጉዳይ ለመመርመር ተሰበሰቡ።  ከብዙ ክርክር በኋላ ጴጥሮስ ተነስቶ እንዲህ አላቸው፦ “ወንድሞች፣ አሕዛብ የምሥራቹን ቃል ከእኔ አፍ ሰምተው እንዲያምኑ አምላክ ገና ከመጀመሪያው ከእናንተ መካከል እኔን እንደመረጠኝ በሚገባ ታውቃላችሁ።+  ልብን የሚያውቀው አምላክ+ ለእኛ እንዳደረገው ሁሉ ለእነሱም መንፈስ ቅዱስን በመስጠት መሠከረላቸው።+  ደግሞም በእኛና በእነሱ መካከል ምንም ልዩነት አላደረገም፤+ ከዚህ ይልቅ በእምነታቸው የተነሳ ልባቸውን አነጻ።+ 10  ታዲያ አባቶቻችንም ሆኑ እኛ ልንሸከመው ያልቻልነውን+ ቀንበር በደቀ መዛሙርቱ ጫንቃ ላይ በመጫን+ አሁን አምላክን ለምን ትፈታተናላችሁ? 11  በአንጻሩ ግን እኛ የምንድነው በጌታ ኢየሱስ ጸጋ አማካኝነት እንደሆነ እናምናለን፤+ እነሱም ቢሆኑ ይህንኑ ያምናሉ።”+ 12  በዚህ ጊዜ የተሰበሰበው ሰው ሁሉ ጸጥ አለ፤ በርናባስና ጳውሎስ፣ አምላክ በእነሱ አማካኝነት በአሕዛብ መካከል ያከናወናቸውን በርካታ ተአምራዊ ምልክቶችና ድንቅ ነገሮች ሲናገሩም ያዳምጥ ጀመር። 13  እነሱ ተናግረው ካበቁ በኋላ ያዕቆብ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ወንድሞች፣ ስሙኝ። 14  አምላክ ከአሕዛብ መካከል ለስሙ የሚሆኑ ሰዎችን ለመውሰድ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዴት ለእነሱ ትኩረት እንደሰጠ ሲምዖን*+ በሚገባ ተርኳል።+ 15  እንዲህ ተብሎ የተጻፈው የነቢያት ቃልም ከዚህ ጋር ይስማማል፦ 16  ‘ከዚህ በኋላ ተመልሼ የፈረሰውን የዳዊትን ድንኳን* ዳግመኛ አቆማለሁ፤ ፍርስራሹንም አድሼ ዳግም እገነባዋለሁ፤ 17  ይህን የማደርገው የቀሩት ሰዎች፣ ከብሔራት ከመጡት በስሜ የተጠሩ ሰዎች ጋር አንድ ላይ ሆነው ይሖዋን* ከልብ እንዲፈልጉ ነው በማለት እነዚህን ነገሮች የሚያደርገው ይሖዋ* ተናግሯል፤+ 18  እነዚህም ነገሮች ከጥንት ዘመን ጀምሮ ይታወቃሉ።’+ 19  ስለዚህ እንደ እኔ ሐሳብ ከሆነ፣* ተለውጠው አምላክን ማምለክ የጀመሩትን አሕዛብ ባናስቸግራቸው ይሻላል፤+ 20  ከዚህ ይልቅ በጣዖት+ ከረከሱ ነገሮች፣ ከፆታ ብልግና፣*+ ታንቆ ከሞተ* እንስሳ ሥጋ እንዲሁም ከደም እንዲርቁ+ እንጻፍላቸው። 21  ምክንያቱም ከጥንት ዘመን ጀምሮ በየከተማው በሰንበት ቀናት ሁሉ በምኩራቦች ውስጥ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ከሙሴ መጻሕፍት በማንበብ በውስጡ የሰፈረውን ቃል የሚሰብኩ ሰዎች ነበሩ።”+ 22  ከዚያም ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ከመላው ጉባኤ ጋር ሆነው ከመካከላቸው የተመረጡ ሰዎችን ከጳውሎስና ከበርናባስ ጋር ወደ አንጾኪያ ለመላክ ወሰኑ፤ በወንድሞች መካከል ግንባር ቀደም የሆኑትን በርስያን የሚባለውን ይሁዳንና ሲላስን+ ላኩ። 23  ደግሞም የሚከተለውን ደብዳቤ ጽፈው በእነሱ እጅ ላኩላቸው፦ “ከወንድሞቻችሁ ከሐዋርያትና ከሽማግሌዎች፣ በአንጾኪያ፣+ በሶርያና በኪልቅያ ለምትኖሩ ከአሕዛብ ወገን ለሆናችሁ ወንድሞች፤ ሰላምታችን ይድረሳችሁ! 24  ከእኛ መካከል አንዳንዶች ወጥተው እኛ ምንም ሳናዛቸው በሚናገሩት ነገር እንዳስቸገሯችሁና+ ሊያውኳችሁ* እንደሞከሩ ስለሰማን 25  ሰዎች መርጠን ከተወደዱት ወንድሞቻችን ከበርናባስና ከጳውሎስ ጋር ወደ እናንተ ለመላክ በአንድ ልብ ወሰንን፤ 26  በርናባስና ጳውሎስ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ስም ሕይወታቸውን* አሳልፈው የሰጡ ናቸው።+ 27  ስለዚህ ይህንኑ ነገር በቃልም እንዲነግሯችሁ ይሁዳንና ሲላስን ልከናል።+ 28  ከሚከተሉት አስፈላጊ ነገሮች በስተቀር፣ ሌላ ተጨማሪ ሸክም እንዳንጭንባችሁ መንፈስ ቅዱስና+ እኛ ወስነናል፦ 29  ለጣዖት ከተሠዉ ነገሮች፣+ ከደም፣+ ታንቆ ከሞተ እንስሳ* ሥጋና+ ከፆታ ብልግና* ራቁ።+ ከእነዚህ ነገሮች ሙሉ በሙሉ ከራቃችሁ መልካም ይሆንላችኋል። ጤና ይስጣችሁ!”* 30  የተላኩትም ሰዎች ከተሰናበቱ በኋላ ወደ አንጾኪያ ወረዱ፤ እዚያ የሚገኙትንም ደቀ መዛሙርት በአንድነት ሰብስበው ደብዳቤውን ሰጧቸው። 31  እነሱም ካነበቡት በኋላ ባገኙት ማበረታቻ እጅግ ተደሰቱ። 32  ይሁዳና ሲላስም ራሳቸው ነቢያት ስለነበሩ ብዙ ቃል በመናገር ወንድሞችን አበረታቷቸው፤ እንዲሁም አጠናከሯቸው።+ 33  በዚያም የተወሰነ ጊዜ ከቆዩ በኋላ ወደላኳቸው ሰዎች እንዲመለሱ ወንድሞች በሰላም አሰናበቷቸው። 34  *—— 35  ይሁን እንጂ ጳውሎስና በርናባስ እያስተማሩና ከሌሎች ብዙ ሰዎች ጋር ሆነው ምሥራቹን ይኸውም የይሖዋን* ቃል እየሰበኩ በአንጾኪያ ቆዩ። 36  ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ጳውሎስ በርናባስን “የይሖዋን* ቃል ባወጅንባቸው ከተሞች ሁሉ ያሉት ወንድሞች በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ተመልሰን እንጠይቃቸው”* አለው።+ 37  በርናባስ፣ ማርቆስ ተብሎ የሚጠራው ዮሐንስ+ አብሯቸው እንዲሄድ ወስኖ ነበር። 38  ጳውሎስ ግን ማርቆስ በጵንፍልያ ተለይቷቸው ስለነበረና ያከናውኑት ወደነበረው ሥራ ከእነሱ ጋር ስላልሄደ አሁን አብሯቸው እንዲሄድ አልፈለገም።+ 39  በዚህ ምክንያት በመካከላቸው ኃይለኛ ጭቅጭቅ ስለተፈጠረ ተለያዩ፤ ስለዚህ በርናባስ+ ማርቆስን ይዞ በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ሄደ። 40  ጳውሎስ ደግሞ ሲላስን መረጠ፤ ወንድሞችም ለይሖዋ* ጸጋ በአደራ ከሰጡት በኋላ ከዚያ ተነስቶ ሄደ።+ 41  ጉባኤዎችንም እያበረታታ በሶርያና በኪልቅያ በኩል አለፈ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ክርክሩን።”
የስምዖን ጴጥሮስ ስም ሌላ አጠራር ነው።
ወይም “ዳስ፤ ቤት።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “እንደ እኔ ውሳኔ ከሆነ።”
ወይም “ደሙ ሳይፈስ ከተገደለ።”
ግሪክኛ፣ ፖርኒያ። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ነፍሳችሁን ሊያውኩ።”
ወይም “ነፍሳቸውን።”
ወይም “ደህና ሁኑ።”
ግሪክኛ፣ ፖርኒያ። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ደሙ ሳይፈስ ከተገደለ እንስሳ።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ3ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
“ልንጠይቃቸው ይገባል” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።