በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የአንድ ሃይማኖት አባል መሆን የግድ አስፈላጊ ነው?

የአንድ ሃይማኖት አባል መሆን የግድ አስፈላጊ ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 አዎ፣ ምክንያቱም ሰዎች ለአምልኮ አንድ ላይ እንዲሰባሰቡ አምላክ ይፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “እርስ በርስ ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች መነቃቃት እንድንችል አንዳችን ለሌላው ትኩረት እንስጥ፤ . . . መሰብሰባችንን ቸል አንበል።”—ዕብራውያን 10:24, 25

 ኢየሱስ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ” በማለት የተናገረው ሐሳብ ደቀ መዛሙርቱ አንድ የተደራጀ ቡድን እንደሚመሠርቱ ይጠቁማል። (ዮሐንስ 13:35) የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ይህን ዓይነቱን ፍቅር ማሳየት ከሚችሉባቸው ዋነኛ መንገዶች አንዱ ከእምነት አጋሮቻቸው ጋር መሰብሰብ ነው። ዘወትር አንድ ላይ ተሰብስበው አምልኳቸውን ለመፈጸም ጉባኤዎችን ማቋቋም አለባቸው። (1 ቆሮንቶስ 16:19) እነዚህ ጉባኤዎች ደግሞ አንድ ላይ ዓለም አቀፋዊ አንድነት ያለው የወንድማማች ማኅበር ይመሠርታሉ።—1 ጴጥሮስ 2:17

የአንድ ሃይማኖት አባል ከመሆን የበለጠ ነገር ያስፈልጋል

 መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች አምላክን ለማምለክ አንድ ላይ መሰብሰብ እንዳለባቸው ሲናገር አንድ ሰው የአንድ ሃይማኖት አባል መሆኑ ብቻውን አምላክን ያስደስተዋል ማለቱ አይደለም። ግለሰቡ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ከፈለገ ሃይማኖቱ በሚያዘው መሠረት የዕለት ተዕለት ሕይወቱን መምራት አለበት። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “በአምላካችንና በአባታችን ዓይን ንጹሕና ያልረከሰ ሃይማኖት ‘ወላጅ አልባ የሆኑ ልጆችንና መበለቶችን በመከራቸው መርዳት እንዲሁም ከዓለም እድፍ ራስን መጠበቅ’ ነው።”—ያዕቆብ 1:27 የግርጌ ማስታወሻ