በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የይሖዋ ምሥክሮች ስለ ቀብር ሥነ ሥርዓት ምን አመለካከት አላቸው?

የይሖዋ ምሥክሮች ስለ ቀብር ሥነ ሥርዓት ምን አመለካከት አላቸው?

 ከቀብር ሥነ ሥርዓት ጋር በተያያዘ ያለን አመለካከትና የምናደርጋቸው ነገሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ላይ የተመሠረቱ ናቸው፤ ከእነዚህም መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦

  •   የምንወደው ሰው ሲሞት ማልቀስ ምንም ስህተት የለውም። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ወዳጆቻቸው በሞቱበት ወቅት አልቅሰዋል። (ዮሐንስ 11:33-35, 38፤ የሐዋርያት ሥራ 8:2፤ 9:39) ስለሆነም የቀብር ሥነ ሥርዓትን የፈንጠዝያ ጊዜ አድርገን አንመለከተውም። (መክብብ 3:1, 4፤ 7:1-4) ከዚህ ይልቅ ሐዘናችንን የምንገልጽበት ወቅት እንደሆነ ይሰማናል።—ሮም 12:15

  •   ሙታን ምንም አያውቁም። የአካባቢያችን ባሕል ምንም ሆነ ምን ሙታን፣ በሌላ ቦታ በሕይወት እንደሚኖሩ እንዲሁም በሕይወት ባሉ ሰዎች ላይ ተጽዕኖ ማሳደር እንደሚችሉ በሚገልጸው የተሳሳተ እምነት ላይ የተመሠረቱ ልማዶችንና ድርጊቶችን ከመከተል እንርቃለን። (መክብብ 9:5, 6, 10) ከእነዚህም መካከል ተዝካር ማውጣት፣ ሙት ዓመት ማክበር፣ ለሙታን መሥዋዕት ማቅረብ፣ ሙታንን ማነጋገር ወይም አንድ ነገር እንዲያደርጉልን መጠየቅና የመሳሰሉት ልማዶች ይገኙበታል። ከእነዚህ ሁሉ ልማዶች የምንርቀው መጽሐፍ ቅዱስ “ራሳችሁን ለዩ . . . ርኩስ የሆነውንም ነገር አትንኩ” የሚል መመሪያ ስለሚሰጥ ነው።—2 ቆሮንቶስ 6:17

  •   ሙታን ተስፋ አላቸው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ትንሣኤ እንዳለና ሞት የማይኖርበት ጊዜ እንደሚመጣ ያስተምራል። (የሐዋርያት ሥራ 24:15፤ ራእይ 21:4) ይህ ተስፋ የጥንቶቹን ክርስቲያኖች ረድቷቸዋል፤ እኛም ከመጠን ባለፉ የሐዘን መግለጫ ልማዶች ከመካፈል እንድንቆጠብ ይረዳናል።—1 ተሰሎንቄ 4:13

  •   መጽሐፍ ቅዱስ ልክን ማወቅን ያበረታታል። (ምሳሌ 11:2) የቀብር ሥነ ሥርዓት “ኑሮዬ ይታይልኝ” የሚል መንፈስ የሚንጸባረቅበትና አንድ ሰው ሀብቱን ወይም በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለውን ቦታ የሚያሳይበት አጋጣሚ መሆን እንደሌለበት እናምናለን። (1 ዮሐንስ 2:16) ከቀብር ሥነ ሥርዓት ጋር በተያያዘ ድል ያለ ድግስ አናዘጋጅም፤ ሌሎችን ለማስደመም ብለን በጣም ውድ የሆነ የሬሳ ሳጥን አንጠቀምም ወይም ለየት ያለ ልብስ አንለብስም።

  •   ከቀብር ሥነ ሥርዓት ጋር በተያያዘ ያለንን አመለካከት እንዲቀበሉ ሌሎችን አንጫንም። ከዚህ ጋር በተያያዘ “እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለአምላክ መልስ እንሰጣለን” የሚለውን መመሪያ እንከተላለን። (ሮም 14:12) ሆኖም አጋጣሚው ከተሰጠን “በገርነት መንፈስና በጥልቅ አክብሮት” ስለ እምነታችን እንናገራለን።—1 ጴጥሮስ 3:15

የይሖዋ ምሥክሮች የቀብር ሥነ ሥርዓት ምን ይመስላል?

 ቦታ፦ የሟቹ ቤተሰብ በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ስለ ሟቹ ንግግር እንዲቀርብ ከወሰነ ንግግሩ ቤተሰቡ በመረጠው በማንኛውም ቦታ፣ ይኸውም በመንግሥት አዳራሽ፣ በግለሰብ ቤት ወይም በመቃብር ቦታው ሊደረግ ይችላል።

 ሥነ ሥርዓቱ ላይ የሚከናወኑ ነገሮች፦ የሟቹን ቤተሰብና ወዳጆች ለማጽናናት፣ መጽሐፍ ቅዱስ ሞትንና የትንሣኤ ተስፋን አስመልክቶ ምን እንደሚል የሚያብራራ ንግግር ይቀርባል። (ዮሐንስ 11:25፤ ሮም 5:12፤ 2 ጴጥሮስ 3:13) በንግግሩ ላይ ሟቹ ስለነበሩት መልካም ባሕርያት እንዲሁም እሱ ከተወው የታማኝነት ምሳሌ ስለምናገኛቸው ትምህርቶች ሊጠቀስ ይችላል።—2 ሳሙኤል 1:17-27

 በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መዝሙር ሊዘመር ይችላል። (ቆላስይስ 3:16) ንግግሩ በሚያጽናና ጸሎት ይደመደማል።—ፊልጵስዩስ 4:6, 7

 ክፍያ ወይም ሙዳየ ምጽዋት፦ የቀብር ሥነ ሥርዓትን ጨምሮ ለምንሰጠው ማንኛውም ሃይማኖታዊ አገልግሎት አናስከፍልም፤ እንዲሁም በስብሰባዎቻችን ላይ ሙዳየ ምጽዋት አይዞርም።—ማቴዎስ 10:8

 ሥነ ሥርዓቱ ላይ መገኘት የሚችሉት እነማን ናቸው? የይሖዋ ምሥክሮች ያልሆኑ ሰዎችም በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ በሚካሄድ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ መገኘት ይችላሉ። እንደ ሌሎቹ ስብሰባዎቻችን ሁሉ በቀብር ንግግር ላይም ማንኛውም ሰው መገኘት ይችላል።

የይሖዋ ምሥክሮች ሌሎች ሃይማኖቶች በሚያደርጓቸው የቀብር ሥነ ሥርዓቶች ላይ ይገኛሉ?

 በዚህ ረገድ እያንዳንዱ የይሖዋ ምሥክር በመጽሐፍ ቅዱስ በሠለጠነ ኅሊናው ተጠቅሞ የራሱን ውሳኔ ያደርጋል። (1 ጢሞቴዎስ 1:19) ሆኖም ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እንደሚጋጩ በሚሰማን ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች አንካፈልም።—2 ቆሮንቶስ 6:14-17