በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ግብ በወረቀት ላይ እንዳለ ንድፍ ነው፤ ያሰብከው ነገር እውን ሆኖ ለማየት ጥረት ማድረግ ይጠይቃል

ለወጣቶች

12፦ ግብ ማውጣት

12፦ ግብ ማውጣት

ምን ማለት ነው?

ግብ ማውጣት ማለት አንድን ነገር መመኘት ማለት አይደለም። ግብ ማውጣት አስቀድሞ ማቀድን፣ አስፈላጊውን ለውጥ ማድረግንና ያወጣነው ግብ ላይ ለመድረስ ጠንክሮ መሥራትን ይጠይቃል።

ግቦች የአጭር ጊዜ (የቀናት ወይም የሳምንታት)፣ የመካከለኛ ጊዜ (የወራት) እና የረጅም ጊዜ (የዓመት ወይም ከዚያ በላይ) ተብለው ሊከፈሉ ይችላሉ። የረጅም ጊዜ ግቦች ላይ ከመድረሳችን በፊት ልንደርስባቸው የሚገቡ የተለያዩ ግቦች ሊኖሩ ይችላሉ።

አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

ያወጣሃቸው ግቦች ላይ መድረስህ በራስ የመተማመን ስሜትህ ከፍ እንዲል፣ ከሌሎች ጋር ያለህ ወዳጅነት እንዲጠናከርና ይበልጥ ደስተኛ እንድትሆን ይረዳሃል።

በራስ መተማመን፦ ትናንሽ ግቦችን አውጥተህ ግቦችህ ላይ መድረስህ ሌሎች ትላልቅ ግቦች ላይም መድረስ እንደምትችል እንድትተማመን ያደርግሃል። በተጨማሪም የእኩዮችን ተጽዕኖ እንደመቋቋም ያሉ በየዕለቱ የሚያጋጥሙህን ፈተናዎች ለመጋፈጥ የሚያስችል ድፍረት ይሰጥሃል፤ ይህም ይበልጥ በራስህ እንድትተማመን ያደርግሃል።

ወዳጅነትን ማጠናከር፦ ብዙ ሰዎች ሚዛናዊ የሆነ ግብ ካላቸው ማለትም የሚፈልጉትን ነገር ከሚያውቁና ይህን ለማሳካት ጠንክረው ከሚሠሩ ሰዎች ጋር ወዳጅነት መመሥረት ይፈልጋሉ። ከዚህም በላይ የጋራ ግብ ላይ ለመድረስ አብሮ መሥራት ጓደኝነትን ይበልጥ ያጠናክራል።

ደስተኛ መሆን፦ ግብ ማውጣትህና እዚያ ግብ ላይ መድረስህ አንድ ነገር ማከናወን በመቻልህ እርካታ እንዲሰማህ ያደርጋል።

“ግብ ማውጣት እወዳለሁ። ግብ ማውጣቴ በሥራ እንድጠመድ ያደርገኛል እንዲሁም አንድ ነገር ላይ ለመድረስ ጥረት እንዳደርግ ያነሳሳኛል። ደግሞም ግብህ ላይ ከደረስክ በኋላ ‘ተሳካልኝ ማለት ነው! ያሰብኩትን አድርጌያለሁ’ ማለት መቻል በራሱ ደስ የሚል ነገር ነው።”—ክሪስቶፈር

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ነፋስን የሚጠባበቅ አይዘራም፤ ደመናትንም የሚመለከት አያጭድም።”—መክብብ 11:4

ምን ማድረግ ትችላለህ?

ግቦችን ለማውጣትና እዚያ ላይ ለመድረስ የሚከተሉትን እርምጃዎች ውሰድ።

ምን እንደምትፈልግ እወቅ። ግብ አድርገህ ልታስቀምጣቸው የምትፈልጋቸውን ነገሮች ዝርዝር ጻፍ። ከዚያም መጀመሪያ ልታደርገው ከምትፈልገው ነገር በመነሳት በቅደም ተከተል አስቀምጣቸው።

ዕቅድ አውጣ። ለእያንዳንዱ ግብ የሚከተሉትን ነገሮች አድርግ፦

  • ግብህ ላይ የምትደርስበትን ምክንያታዊ የጊዜ ገደብ አስቀምጥ።

  • ምን እርምጃ መውሰድ እንዳለብህ አስብ።

  • ሊያጋጥሙህ የሚችሉ እንቅፋቶችንና እንዴት ልትወጣቸው እንደምትችል አስቀድመህ አስብ።

እርምጃ ውሰድ። ዕቅድህን በሥራ ላይ ለማዋል እያንዳንዱ ነገር እስኪሟላልህ ድረስ አትጠብቅ። ራስህን ‘ግቤ ላይ ለመድረስ ልወስደው የምችለው የመጀመሪያ እርምጃ ምንድን ነው?’ ብለህ ጠይቅ። ከዚያም ተግባራዊ አድርገው። የምትወስደው እያንዳንዱ እርምጃ ያስገኘውን ውጤት ገምግም።

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “የትጉ ሰው ዕቅድ ለስኬት ያበቃዋል።”—ምሳሌ 21:5