በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ተባብረው የሚሠሩ ባለትዳሮች አንድን አውሮፕላን ከሚያበሩ አብራሪና ረዳት አብራሪ ጋር ይመሳሰላሉ

ለባለትዳሮች

2፦ ተባብሮ መሥራት

2፦ ተባብሮ መሥራት

ምን ማለት ነው?

ተባብረው የሚሠሩ ባለትዳሮች አንድን አውሮፕላን ከሚያበሩ አብራሪና ረዳት አብራሪ ጋር ሊመሳሰሉ ይችላሉ። እንዲህ ያሉ ባለትዳሮች ችግሮች በሚነሱበት ጊዜም እንኳ የሚያስቡት “እኔ” እያሉ ሳይሆን “እኛ” እያሉ ይሆናል።

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ከዚህ በኋላ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም።”—ማቴዎስ 19:6

“ትዳር አንድ ሰው ብቻውን የሚተውንበት መድረክ አይደለም። ትዳርን የተሳካ ለማድረግ ባልና ሚስት ተባብረው መሥራት አለባቸው።”—ክሪስተፈር

አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

ተባብረው የማይሠሩ ባልና ሚስት ጭቅጭቅ ሲነሳ ችግሩን ለመፍታት ጥረት ከማድረግ ይልቅ አንዳቸው ሌላውን የማጥቃት አዝማሚያ ይታይባቸዋል። ጥቃቅን አለመግባባቶች ወደ ከፍተኛ ግጭት ሊያመሩ ይችላሉ።

“ተባብሮ መሥራት ትዳርን ስኬታማ ለማድረግ የሚያስፈልግ መሠረታዊ ነገር ነው። እኔና ባለቤቴ ተባብረን የማንሠራ ብንሆን ኖሮ ባለትዳር መሆናችን ቀርቶ ደባል እንሆን ነበር። ደባል የሆኑ ሰዎች አብረው ቢኖሩም ውሳኔ በሚጠይቁ አስፈላጊ ጉዳዮች ላይ የየራሳቸውን አቋም ይወስዳሉ።”—አሊግዛንድራ

ምን ማድረግ ትችላለህ?

ራስህን ፈትሽ

  • ሠርቼ የማገኘውን ገንዘብ የምመለከተው “የራሴ ብቻ” እንደሆነ አድርጌ ነው?

  • በደንብ ዘና እንዳልኩ የሚሰማኝ የትዳር ጓደኛዬ አብራኝ ከሌለች ነው?

  • የትዳር ጓደኛዬ ከዘመዶቿ ጋር የምትቀራረብ ብትሆንም እኔ ከእነሱ ለመራቅ እሞክራለሁ?

የሚከተሉትን ጥያቄዎች ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ተወያዩባቸው

  • በጥሩ ሁኔታ ተባብረን የምንሠራው በየትኞቹ አጋጣሚዎች ነው?

  • ማሻሻያ ማድረግ የሚያስፈልገንስ በየትኞቹ ዘርፎች ነው?

  • ይበልጥ ተባብረን ለመሥራት ምን ማድረግ እንችላለን?

ጠቃሚ ምክሮች

  • እስቲ ቴኒስ እየተጫወታችሁ እንደሆነ አድርጋችሁ አስቡ። የትዳር ጓደኛችሁ ያለው በተቃራኒ አቅጣጫ ባለው ቡድን ውስጥ ነው እንበል። ታዲያ ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር በአንድ ቡድን ውስጥ ሆናችሁ ለመጫወት ምን እርምጃዎችን መውሰድ ትችላላችሁ?

  • ‘ማሸነፍ የምችለው እንዴት ነው?’ ብሎ ከማሰብ ይልቅ ‘ማሸነፍ የምንችለው እንዴት ነው?’ ብላችሁ አስቡ።

“‘ትክክል የሆነው ማን ነው?’ የሚለው ጉዳይ ያን ያህል ሊያሳስባችሁ አይገባም። በትዳራችሁ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ሰላምና አንድነት መስፈኑ ነው።”—ኤታን

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ስለ ራሳችሁ ፍላጎት ብቻ ከማሰብ ይልቅ እያንዳንዳችሁ ለሌሎች ሰዎች ፍላጎትም ትኩረት ስጡ።”—ፊልጵስዩስ 2:3, 4